መግቢያ
የፍትሐብሔር አቤቱታ (ክስ) አቅራቢ ወገን ፍርድ ለማስፈፀም ለፍርድ ቤት በመጀመሪያ የክስ አቤቱታዉን ሲያቀርብም ሆነ ካቀረበ በኋላ ለቀረበዉ ክስ ተመጣጣኝ የሆነ ሀብትና ንብረት ማስያዝ ወይም ማስከበር ይኖርበታል፡፡ ምክንያቱም ንብረቱ ሳይታገድ ቀርቶ ተከሳሽ (ተጠሪ) ሀብትና ንብረቱን ቢያሸሸዉ ያስፈረደዉ ፍርድ ሳይፈፀም መቅረቱ የፍርድ ባለመብትን መብትና ጥቅም የሚሳጣ በመሆኑ ነዉ፡፡ በዚህ አጭር ጽሁፍ በፍርድ ማስፈፀም ሂደት ሀብትና ንብረት ስለማስከበር እና ስለማይከበሩና በፍርድ ምክንያት ስለማይወሰዱ ሀብትና ንብረቶች እንመለከታለን፡፡
በፍርድ ማስፈፀም ሂደት ሀብትና ንብረት ስለማስከበር
ፍርድ የተፈረደበት ወገን በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 386 እንደተደነገገዉ እንደ ፍርዱ የማይፈፀምበትን ምክንያት ካላስረዳ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 386 እና 392(1) መሠረት ፍርዱ እንዲፈፀም ወዲያዉኑ ትዕዘዝ ይሰጣል፡፡ ፍርድ የሚፈፀመዉ የፍርድ ባለዕዳዉን ንብረት በማስከበርና በመሸጥ ነዉ፡፡ የፍርድ ባለመብቱም በዚህ አኳኋን ይፈፀምለት ዘንድ ከፍርዱ በፊት ያሳገደዉንም ሆነ ለፍርድ አፈፃፀም ሊዉል ይችላል የሚለዉን የፍርድ ባለዕዳ ሀብትና ንብረት ዝርዝር ያቀርባል፡፡ በፍርድ አፈፃፀም ሂደት መጓተት እንዳያስከትል እንዲያዝና እንዲሸጥ ተብሎ የቀረበዉ የንብረት ዝርዝር በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 404 ከተመለከቱት ዉጭ መሆናቸዉንና በእርግጥም በፍርድ ባለዕዳዉ ባለቤትነት የሚገኙ ስለመሆናቸዉ በሚቻለዉ መንገድ ሁሉ መረጋገጥ ይኖርበታል፡፡ በፍርድ አፈፃፀም ምክንያት ንብረት እንዲያዝና እንዲከበር የማድረጉ ተግባር አፈፃፀሙን በያዘዉ ፍርድ ቤት ብቻ ሳይሆን በሌሎች ፍርድ ቤቶችም ተይዞ እና ተከብሮ የተገኘ እንደሆነ ጉዳዩ በምን አኳኋን እንደሚታይ በፍ/ብ /ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 413 ተደንግጓል፡፡ ይኸዉም “… ንብረቱ የተያዘዉ በፍርድ ቤት የሆነ እንደሆነ ሌሎች ሦስተኛ ወገኖች ይህንኑ ንብረት አስቀድመን አስይዘናል፣ አስረክበናል በማለት የቀዳሚነት መብት አለን በማለት ክርክር ያነሱ እንደሆነ ክርክሩ የሚወሰነዉ ንብረቱን ይዞ በሚገኘዉ ፍርድ ቤት ነዉ፡፡” የሚል ነዉ፡፡
አንድ ንብረት አስቀድሞ በፍርድ ቤት በመከበሩ ምክንያት የተፈረደ ፍርድ ሳይፈፀም ይቀራል ማለት እንዳልሆነ ይኸዉ ድንጋጌ አስረጅ ቢሆንም ክርክሩ በየትኛዉ ፍርድ ቤት ይታያል ለሚለዉ ግን ሁሉንም ጉዳይ የሸፈነ አይደለም፡፡ በመጀመሪያ ንብረቱን የያዘዉ የከፍተኛዉ ፍርድ ቤት ሆኖ በተለያየ ምክንያት አፈፃፀሙ በመጓተቱ የተነሣ በወረዳዉ ፍርድ ቤት ዉሳኔ መሠረት እንዲፈፀም የተከበረ መሆኑ ቢታወቅ እንደ ፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 413 ድንጋጌ ይዘት በባለገንዘቦች መካከል የሚነሳዉ የቀዳሚነት መብት ክርክር በወረዳዉ ፍርድ ቤት ይታያል እንደ ማለት ነዉ፡፡ በእርግጥ ይህ ዓይነቱ ክርክር እንዳይከሰት በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 378 ( 3 ) ( መ ) መሠረት አፈፃፀሙን ለከፍተኛዉ ፍርድ ቤት ቢመራዉ የተመረጠ ይሆናል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ድንጋጌዉ ቀጥተኛ ምላሽ አይሰጥም፡፡ ፍርድ ቤቶቹ አቻ ከሆኑ ችግር የሚያስከትል መስሎ አይታይም፡፡ ላይና ታች ከሆኑ ግን ድንጋጌዉ ትርጉም ያሻዋል፡፡ ይኸዉ ድንጋጌ የተወሰደዉ ከህንድ ፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 63 እንደሆነ ከይዘቱ መረዳት ይቻላል፡፡ በዚሁ የሕግ ድንጋጌ የአቻነት ሥልጣን ባላቸዉ ፍርድ ቤቶች ንብረቱ ተከብሮ በሚገኝበት ጊዜ ቀድሞ ንብረቱን ባስከበረዉ ፍርድ ቤት የሥልጣን ደረጃቸዉ እኩል ባልሆነ ፍርድ ቤቶች ንብረቱ ተከብሮ በሚገኝበት ጊዜ ደግሞ ሥልጣኑ ከሁሉም ከፍ ብሎ በሚገኘዉ ፍርድ ቤት ክርክራቸዉ ታይቶ እንደሚወሰን ተመልክቷ፡፡
ስለማይከበሩና በፍርድ ምክንያት ስለማይወሰዱ ሀብትና ንብረቶች
ፍርድን ለማስፈፀም ሲባል የማይከበሩና በፍርድ አፈፃፀም ምክንያት ሊወሰዱ ስለማይችሉ ንብረቶች ዓይነትና መጠን በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 404 ስር ተዘርዝሯል ከሚከተሉት ሁለቱን ንዑስ አንቀጾች በስተቀር ድንጋጌው በራሱ ግልጽ በመሆኑ ማብራሪያ የሚያስፈልገው አይመስልም፡፤
- በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 404 (ለ) “ለዕለት ሞያ ስራዎቹ አገልግሎት ለንግድ ስራው ማከናወኛ ተገቢ የሆኑ ዕቃዎች ከሚለው ድንጋጌ “ዕቃዎች“ የሚለው ቃል ሰፊ ትርጉም ሊየሰጥ በሚችል አኳኋን ይጠቀስ እንጂ የዚሁ ግልባጭ ከሆነው የአገልግሎት ንባብ ጋር አጣቅሰን ካየነው ተገቢ የሆኑ የመገልገያ መሳሪያዎች ለማለት ተፈልጎ እንደሆነ መረዳት ይቻላል፡፡
- በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 404 ንዑስ ፊደል (ሠ) “ለጡረታው የሚከፈለው ገንዘብ….“ የሚለውን ድንጋጌ ስለ ጡረታ ጉዳይ ከደነገገው የጡረታ ሕግ አዋጅ ቁጥር 1267/14 አንቀጽ 51 ጋር ተገናዝቦ ሊታይ የሚገባው ነው፡፡ ለጡረታው የሚከፈለው ገንዘብ እንደማይከበር በፍርድ አፈፃፀም ምክንያት እንዳይያዝ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 404 የተገለፀ ቢሆንም በመንግሥት ሰራተኞች ጡረታ አዋጅ ቁጥር 1267/14 አንቀጽ 51 ላይ ከዚህ በተለየ ሁኔታ ተደንግጓል፡፡ ይኸውም በአንቀጽ 51 ከጡረታ አባል እንዲከፈል የተጠየቀው ዕዳ ለመንግሥት ገቢ የሚሆን መቀጮ፣ ግብር ወይም ቀረጥ ለመክፈል ወይም አግባብ ባላቸው የፍትሐብሔር ድንጋጌዎች መሠረት የተወሰነ ቀልብ የመስጠት ግዴታ ለመወጣት በፍ/ቤት የታዘዘ እንደሆነ የጡረታ አባሉ ሊከበር እንደሚችል ተደንግጓል፡፡ የጡረታ አበል በዕዳ ምክንያት ሊከበርና ሊያዝ የሚችል የመሆኑና የአለመሆኑ ጉዳይ በተለያዩ ህጎች በተለያዩ ሁኔታ ተደንግጎ ከተገኘ በሕግ አተረጓጎም ዘዴ መሠረት ስለ ጡረታ ጉዳይ በተለይ የሚደነግገው የጡረታ አዋጅ በመሆኑ ከፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህጉ ይልቅ ተፈፃሚነት ሊኖረው የሚችል ከመሆኑም በላይ በኋላ የወጣ እንደመሆኑ ተፈፃሚነት የሚኖረው ይኸው የጡረታ ሕግ ነው፡፡ (the latest prevails over the previous) ወደሚለው መደምደሚያ ሊያደርሰን ይችላል፡፡
የጡረታ አበል በፍርድ ምክንያት ሊያዝ አይገባውም የተባለው መተዳደሪያው በመሆኑ ነው፡፡ ለመተዳደሪያው ሲል ለህይወቱ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ለማግኘት ሲል በመጣው ዕዳ ምክንያት ፍርድ አርፎበት ከተገኘ ይህንኑ ዕዳ ለማስፈፀም የጡረታ አበልን ማስከበር ምን ይከለክላል? የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 404 (ሠ) ድንጋጌ ይህን ጉዳይ ሊሸፍን የሚችል አይደለም የሚል ክርክር ሊነሳ ይችላል፡፡ በተለይም ይህንን ጥያቄ ለአብነት ያህል ከተሻሻለው የፌዴራል የቤተሰብ ሕግ አዋጁ ቁጥር 213/92 አንቀጽ 205 (3) ለቀለብ ተቀባዩ ኑሮ አስፈላጊ የሆነውን ነገር ለማግኘት ሲባል የወጣ ዕዳ መሆኑ ከተረጋገጠ የቀለብ ገንዘብ ሊተላለፍና ሊያዝ እንደሚችል ከተደነገገው ጋር ተገናዝቦ ከታየ የቀለብ ገንዘብ ማለት ለጡረታ የሚከፈል ገንዘብ እስከሆነ ድረስ የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 404 (ሠ) ገዳቢ የሆነ ድንጋጌ መስሎ አይታይም፡፡
በአጠቃላይ በፍትሐብሔር ጉዳይ ክስ መስርቶ እንደመከራከር ሁሉ የከሳሽ ለፍርድ አፈፃፀም የሚሆን ሀብትና ንብረት በፍርድ ቤት ማሳገድ የፍርድ አፈፃፀሙን የተሳለጠ ያደርገዋል፡፡