የዲሞክራሲ ተቋማት ተግባርና ኃላፊነት በኢትዮጵያ

ማውጫ

ይህን ጽሑፍ ያጋሩ

መግቢያ

ማንኛውም ሰው በዓለም ዓቀፍ ደረጃም ይሁን በሀገራችን መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን የአስተዳደሩን ሕዝባዊነት የሚያረጋግጡ ተቋማት መኖራቸውን በፅኑ ይደግፋል ተብሎ ይታመናል። ተጠያቂነት (Accountability) ወይም ግልጸኝነትና ተጠያቂነት ሳይኖር በአንድ ሀገር ላይ ዴሞክራሲ፣ የሕግ የበላይነት፣ ፍትሕና መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን ማድረግ የማይታሰብ ነው። ሀገራችን ኢትዮጵያም ከዚህ እሳቤ በመነሳት ፍትሕን፣ ዴሞክራሲንና መልካም አስተዳደርን ለማረጋገጥ የሚያግዙ ተቋማትን አቋቁማ ትገኛለች።

በሀገራችን ካሉ የዴሞክራሲ ተቋማት መካከል ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም፣ ምርጫ ቦርድ፣ የተወካዮች ምክር ቤት፤ የፌዴሬሽን ምክር ቤት፤ ወዘተ ሲሆኑ እነዚህ ተቋማት በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ላይ ትልቅ ሚና ያላቸው በመሆኑ ጠንካራ አደረጃጀትና ተፅእኖ ለመፍጠር የሚችል አቅም ሊኖራቸው ይገባል። ምክንያቱም ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ያለ ዲሞክራሲያዊ ተቋማትና ያለ ዴሞክራሲያዊ አመራር የማይታሰብ በመሆኑ ነው። በዚህ አጭር ጽሁፍ ሁሉንም የዴሙክራሲ ተቋማት ኃላፊነትና ተግባር ብናይ የሚሰፋ በመሆኑ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ እምባ ጠባቂ ተቋም እና የኢትዮጵያ ምርጫ ቦረድ ያለባቸው ኃላፊነትና ተግባር ምን እንደሆነ ለመዳሰስ ይሞከራል።

የዴሞክራሲ ተቋማት የሚባሉት እነማን ናቸው?

ዴሞክራሲ የሚለው ቃል የሁለት የግሪክ ቃላቶች ጥምረት ወጤት ሲሆን (demos=) ማለት People (ሕዝብ) ሲሆን (kratein=) to govern, to rule. (ማስተዳደር መምራት) ማለት ሲሆን በአጭሩ ዴሞክራሲን ህዝባዊ አስተዳደር ልንለው እንችላለን። የዴሞክራሲ ጽንሰ ሀሳብ በጣም ሰፊ ሲሆን ለሰው ልጆች በተፈጥሮም ይሁን በሕግ የተሰጡ መብቶች ተግባራዊ የሚሆኑት ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ሲዘረጋ ነው። በሀገራችን ኢትዮጵያ ዜጎች በህገ-መንግሥትም ሆነ በሌሎች ህጎች የተረጋገጡላቸውን መብቶች ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ለማስከበር የተለያዩ መንገዶችን የሚጠቀሙ ሲሆን በዋናነት የዴሞክራሲ ተቋማትን በመጠቀም መብቶቻቸው እንዲከበርላቸው ያደረጋሉ።

የኢትዮጵያ ሕዝብ እንባ ጠባቂ ጠቋም ተግባርና ኃላፊነት

የኢ.ፌ.ድ.ሪ ህገ-መንግሥት አንቀጽ 25 ሁሉም ሰዎች በሕግ ፊት እኩል እንደሆኑና በመካከላቸውም በዘር፣ በቀለም፣ በጾታ፣ በሀይማኖት፣ በፖለቲካና ማኅበራዊ ህይወታቸው ምንም አይነት ልዩነት ሳይደረግ የሕግ ዋስትና የማግኘት መብት እንዳላቸው በግልፅ ከመደንገጉም በላይ ማንኛውም ሰው በነዚህ መብቶችና ነፃነቶች ተጠቃሚ እንደሆነ ተመልከቷል። የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም በሕግ የተደነገጉ የሰዎች መብቶችና ጥቅሞች በአስፈፃሚው አካላት እና በግል ድርጅቶች መከበራቸውን በማረጋገጥ የሕግ የበላይነትን መሠረት ያደረገ ጥራት፣ ቅልጥፍናና ግልፅነት ያለው መልካም የመንግሥት አስተዳደር እና የኢንዱስትሪ ሰላም እንዲሰፍን ማድረግ ዋና ዓላማው እንደሆነ የኢትዮጵያ ህዝቦች እንባ ጠባቂ ተቋምን ለማቋቋም የወጣውን አዋጅ ቁጥር 1142/2011 አንቀጽ 6 ባሻሻለው አዋጅ ቁጥር 1307/2016 አንቀጽ 4 ላይ ተቀምጦ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም በመንግሥት የሚወጡ ፖሊሲዎችና ህጎች ከዜጎች ህገ-መንግስታዊ መብቶች የማይቃረኑ መሆናቸውን ማረጋገጥ፣ የዜጎች ሀሳብን በነጻነት የመግለፅ መብቶች ማረጋገጥ፣ ዜጎች በብቃት ለመብቶቻቸው እንዲቆሙ ማድረግ፣ ፍትሀዊ ምርጫ እንዲኖር ማስቻልና መልካም አስተዳደር የማስፈን ሚና መጫወት የቀረቡለትን የአስተዳደር በደል አቤቱታዎች መሠረት በማድረግ መመርመርና ተገቢውን የመፍትሄ ሀሳብ ማቅረብ፣ ለህብረተሰቡ በተለያየ ዘዴ ስለ አስተዳደራዊ ፍትሕ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት መስጠት በዋናነት ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል እንደሆነ በአዋጁ ላይ ተመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ተግባርና ኃላፊነት

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ከዴሞክራሲያዊ ተቋማት መካከል አንዱ ሲሆን እንደ ኢትዮጵያን አቆጣጠር በ1992 ዓ.ም በአዋጅ ቁጥር 210/1992 እንዲቋቋም ተደርጓል። የኮሚሽኑ ተግባር ሰብዓዊ መብቶችምን እንደሆኑ ለማህበረሰቡ ማስተማር፣ መብቶች እንዳይጣሱ መጠበቅ፣ መብቶች በምሉዕነት ሥራ ላይ እንዲውሉና እንዲተገበሩ ማድረግ እና ተጥሰው ሲገኙ አስፈላጊው እርምጃ እንዲወሰድ ማድረግ ዋና ዓላማው ነው።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በአዋጅ ቁጥር 210/1992 ላይም ሆነ በተሻሻለው አዋጅ ቁጥር 1224/2012 አንቀጽ 2 መሠረት ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል በኢ.ፌ.ድ.ሪ ሕገ-መንግሥት ውስጥ የተደነገጉት ሰብዓዊ መብቶች በማንኛውም ዜጋ፣ በመንግሥት አካላት፣ በፖለቲካ ድርጅቶች፣ በሌሎች ማኅበራት መከበራቸውን ማረጋገጥ፡ በመንግሥት የሚወጡ ሕጎች፣ ደንቦች፣ መመሪያዎች፣ እንዲሁም ትዕዛዞች በሕገ-መንግሥቱ ከተረጋገጡ የዜጎች ሰብዓዊ መብቶች ጋር የማይቃረኑ መሆናቸውን ማረጋገጥና ማህበረሰቡ ስለሰብዓዊ መብት በቂ ዕውቀት ኖሮት መብቱን የማክበርና የማስክበር ባህል እንዲያዳብር መገናኛ ብዙሀን በመጠቀም ማስተማር ነው። ሌላው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ደርሶ ቅሬታዎች ሲቀርቡለት ምርመራ ማካዴድ ከትግባሮቹ መካከል ሲሆን ነባር ሕጎች እንዲሻሻሉና አዳዲስ ሕጎች እንዲወጡ ወይም ፖሊሲዎች እንዲቀየሱ ማሰባሰብ ሌላው ተግባሩ ነው። በምርጫ ወቅት የሰብዓዊ መብቶች አጠባበቅን ክትትል ማድረግ፤ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት ስለ ሰብዓዊ መብቶች አጠባበቅ ሁኔታ ክትትል ማድረግ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ማናቸውንም ማረሚያ ቤቶች፣ ፖሊስ ጣቢያዎች ወይም በቁጥጥር ወይም በእገታ ስር የሚገኙ ሰዎች ያሉበትን ስፍራ እንዲሁም እንደ ትምህርት ቤት፣ ሆስፒታል፣ መጠለያ ጣቢያ፣ የገበያ ማዕከል የመሳሰለ እና የሕዝባዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማትን ያለ ቅድመ ማስታወቂያ መጓብኘት እና ሌሎች ዓላማውን ለማስፈጸም የሚያስችሉ ተግባራትን መፈጸም የኮሚሽኑ ተግባር ነው።

የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ

ሌላኛው የዴሞክራሲ ተቋም የኢትዮጵያ የምርጫ ቦርድ ሲሆን ይህ ተቋም በህገ-ምንግስቱ አንቀጽ 102 ላይ በሕግ መቋቋም እንዳለበት መልክቷል። ምርጫ ዋናው ዴሞክራሲያዊ መብት የሚተገበርበት መሳሪያ በመሆኑ በኢ.ፌ.ድ.ሪ ህገ-መንግሥት አንቀጽ 38 ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የሆነ ዜጋ የመምረጥም ሆነ የመመረጥ መብት እንዳለው ተደንግጎ የሚገኝ ሲሆን ይህን መብት ተፈጻሚ ለማድረግ ተቋም የሚያስፈልግ በሆኑ የምርጫ ቦርድ እንዲቋቋም ሆኗል።

የኢትዮጵያ የምርጫ ቦርድ 2011 ዓ.ም በአዋጅ ቁጥር 1133/2011 እንደገና እንዲቋቋም የተደረገ ሲሆን በዚህ አዋጅ አንቀጽ 7 ላይ የቦርዱ ሥልጣንና ተግባራት ተዘርዝረው እናገኛቸዋለን። በዚህ መሠረትም ምርጫ ቦርዱ የሚከተሉትን ተግባራት ሲያከናውን ይስተዋላል፡-

• በህገ-መንግስቱ እና በምርጫ ሕግ መሠረት የሚካሄድ ማንኛውንም ምርጫ እና ህዝበ ውሳኔ በገለልተኝነት ያስፈጽማል፤

• ለመራጮች ትምህርት እንዲሰጡ ለሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ፍቃድ በመስጥት የመከታተልና የቁጥጥር ስራ ያከናውናል፤

• በየደራጃው እና በየጊዜው የሚካሄዱ ምርጫዎች ነጻና ፍትሃዊ በሆነ መንገድ እንዲካሄዱ ሁኔታዎችን የማመቻቸትና የማረጋገጥ ስራን ያከናውናል፡

• የምርጫ አስፈጻሚዎችን ገለልተኝነትና ነጻነት የማረጋገጥ እንዲሁም በምርጫ አስፈጻሚነታቸው ምክንያት የሚደርስባቸውን ተጽእኖ የመከላከል ስራን ይከውናል፡

• በምርጫ ሂደት የምርጫ ውጤት የሚያዛንፍ የሕግ ጥሰት ተከስቷል ብሎ ሲያምን ውጤቱን መሰረዝና ድጋሚ ምርጫ ማካሄድ እንዲሁም በምርጫ ሂደት የተፈጸመ የሕግ መጣስ፤ ማጭበርበር ወይም የሰላምና ጸጥታ ማደፍረስ ድርጊት የፈጸሙ ግለሰቦችን በሕግ እንዲጠየቁ የማድረግ ስራን ያከናውናል።

የምርጫ ቦርድ ሥልጣንና ተግባር ከላይ የተዘረዘሩት ብቻ ሳይሆኑ ሌሎች በርካታ ተግባራትን የሚከናውን ሲሆን ህዝበ ውሳኔ ማካሄድ ሲያስፈልግም አስፈላጊውን በጀት በመመደብ ህዝበ ውሳኔው እንዲደረግ ያደርጋል። በተጨማሪም የመመረጥ መብት ተግባራዊ እንዲሆን ተመራጮችን በግልም ሆነ በፓርቲ ይመዘግባል አስፈላጊውን እገዛም ያደርጋል::

ማጠቃለያ

በአጠቃላይ የዴሞክራሲ ተቋማት የምንላቸው ከላይ የተቀመጡት ብቻ ሳይሆኑ ሌሎች ተቋማትም ለዴሞክራሲ ስርዓት መተግበር ከፍተኛ ሚና የሚጫወቱ ተቋማት አሉ የዚህ ጽሁፍ ትኩረት በነዚህ ተቋማት ላይ የሆነበት ምክንያት የተቋማቱ ዋና ስራቸውና ተግባራቸው የዴሞክራሲ ስርዓት እንዲስፍንና በስፋት ዜጎች መብታቸውን እንዲያስከብሩ እና እንዲከበርላቸው የሚያደርጉ በመሆናቸው ነው። በአንድ ሀገር ውስጥ የዴሞክራሲ ተቋም መኖር ዜጎች ዴሞክራሲያዊም ይሁን ሰብዓዊ መብታቸው እንዲከበር እና ግዴታውን የሚወጣ መብቱን ጠያቂ የሆነ ትውልድ እንዲፈጠር ያደርጋል።

በንቃተ ሕግ፣ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ

ተቀራራቢ ጽሑፎች