የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ምርቶች የደህንነት ማረጋገጫ እና ቁጥጥር በኢትዮጵያ ህግ

ማውጫ

ይህን ጽሑፍ ያጋሩ

መግቢያ

ባለንበት ዘመን የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጅ ለአንድ ሀገር ልማት፤ እድገት፤ ደኅንነት፤ ለዜጎች ኑሮ ሁኔታ መሻሻል እና ለአጠቃላይ ዘላቂ ልማት ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት ይታወቃል፡፡ ነገር ግን ከኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጅ ምርቶች እድገት እና መራቀቅ ጋር ተያይዞ በሀገር ደኅንነት፤ ሰላም እና መረጋጋት፤ በኢኮኖሚ እና በዜጎች አካል እና ጤና ላይ ከፍተኛ ጉዳትም ሊያስከትልም ይችላል ፡፡ በመሆኑም ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ እና ከሀገር የሚወጡ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ምርቶች በሀገር ደኅንነትና ቁልፍ መሰረተ ልማቶች ላይ የሚያስከትሉትን አሉታዊ ተፅዕኖ ለመከላከል የሚያስችል ስርዓትን መዘርጋት በማስፈለጉ አገራችንም የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ምርቶች የደኅንነት ማረጋገጫና ቁጥጥር አዋጅ ቁጥር 1310/2016 ዓ/ም ልታወጣ ችላለች ፡፡

ይህ ጽሁፍ ሁለት ክፍል ያለው ሲሆን በክፍል አንድ በአዋጁ ላይ የተካተቱ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ምርቶች የደኅንነት ማረጋገጫ እና ቁጥጥር የሚደረግባቸው ምርቶች ምንነትን፤ ክልከላ እና ገደብ ስለተጣለባቸው የኤሌክትሮኒክስ ምርቶች እና የደኅንነት ፍቃድ የተሰጠው ሰው እና የተቆጣጣሪ ግዴታዎችን በአጭሩ የምንዳስስ ይሆናል፡፡

የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ምርቶች የደኅንነት ማረጋገጫ እና ቁጥጥር የሚደረግባቸው ምርቶች ምንነት

የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ምርቶች የደኅንነት ማረጋገጫና ቁጥጥር አዋጅ ቁጥር 1310/2016 ዓ/ም በአንቀጽ 2/1 ስር የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ምርት ማለት የኤሌክትሮኒክ ዳታዎችን እና ሲግናሎችን ለማነፍነፍ፤ለማስተጓጎል፤ ለመጥለፍ፤ ለመደምሰስ፤ ለማሳሳት፤ ለማወክ ለመስረቅ እና ተአማኒነት ለማሳጣት የሚያስችል እና በኢንፎርሜሽን ደኅንነት ላይ ስጋት ሊፈጥር የሚችል የቴክኖሎጂ ቁስ፤ ንድፍ፤ ስልተ ቀመር፤ ዘዴ፤ አገልግሎት ወይም መተግበሪያ ነው በማለት ትርጉም ሰጥቶታል፡፡ አዋጁ በአንቀጽ 2/3 ስር የኢንፎርሜሽን ደኅንነት ስጋት ማለት ኢንፎርሜሽን በሚሰበሰብበት፤ በሚተነተንበት፤ በሚከማችበት፤ በሚሰራጭበት ወይም ጥቅም ላይ በሚውልበት ወቅት ተአማኒነቱን፤ ሚስጢራዊነቱን እና ተደራሽነቱን ሊያሳጡ የሚችሉ ስጋቶች ናቸው በማለት ያስቀምጣል፡፡

የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ምርቶች ተገቢውን ቁጥጥር እና ክትትል ካልተደረገባቸው ሀገር ላይ የደኅንነት ስጋት ሊያስከትሉ ይችላሉ፡፡ በአጠቃላይ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ምርቶች በሀገር ደኅንነት ላይ ሊያደርሱት ከሚችሉት አሉታዊ ተጽእኖ አንጻር የኢትዮጵያ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህነት አስተዳደር በተለያዩ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ምርቶች ላይ በየጊዜው ክልከላ እና ገደብ ይጥላል፡፡

ክልከላ እና ገደብ ስለተጣለባቸው የኤሌክትሮኒክስ ምርቶች

ክልከላ እና ገደብ ስለተጣለባቸው የኤሌክትሮኒክስ ምርቶች ከማየታችን በፊት የዚህን አዋጅ ተፈፃሚነት ወሰን ማየት አስፈላጊ ነው፡፡ የዚህን አዋጅ ተፈጻሚነት ወሰን ስንመለከት በአዋጁ አንቀጽ 3/1/ መሠረት ይህ አዋጅ ምርቶች ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት፤ ከሀገር በማስወጣት፤ በማምረት፤ በመፍጠር፤ በመሸጥ ፤በመለወጥ፤ በመያዝ፤ በማዘዋወር፤ በማስተዋወቅ፤ ጥቅም ላይ በማዋል ወይም ጥቅም ላይ እንዲውል የማመቻቸት ተግባር ላይ በተሰማራ ሰው ላይ ተፈጻሚ ይሆናል፡፡ ነገር ግን አዋጁ በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት፤ በፌዴራል ፖሊስ እና ደኅንነት ተቋማት ላይ ተፈጻሚ እንደማይሆን ተደንግጓል፡፡

የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ምርቶች በሀገራዊ የኢንፎርሜሽን ደኅንነት ላይ ሊያደርሱ ከሚችሉት አሉታዊ ተጽህኖ አንጻር የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር በተለያዩ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ምርቶች ላይ በየጊዜው ክልከላ እና ገደብ ይጥለል፡፡

ክልከላ የተደረገበት ምርት ማለት፡- በሀገራዊ የኢንፎርሜሽን ደኅንነት ላይ ሊያደርስ ከሚችለው አሉታዊ ተጽእኖ አንጻር በዚህ አዋጅ መሠረት ወደ ሀገር እንዳይገባ ፤ከሀገር እንዳይወጣ ወይም ጥቅም ላይ እንዳይውል ሙሉ ክልከላ የተጣለበት የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ምርት ነው፡፡ በመሆኑም በአስተዳደሩ ክልከላ የተደረገበት የኢንፎርሜሽን የቴክኖሎጂ ምርት በምንም ሁኔታ ወደ ሀገር ማስገባት አይቻልም፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት እነዚህ ምርቶች ወደ ሀገር ቢገቡ ደኅንነት ላይ ሊያደርሱ የሚችሉት አሉታዊ ተጽዕኖ ከፍተኛ በመሆኑ ነው፡፡

በሀገራችን ከድህንነት ሁኔታ አንጻር ክልከላ የሚደረግባቸውን የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ምርቶችን አስተዳደሩ በየጊዜው ዝርዝራቸውን የሚያወጣ ሲሆን ከነዚህም ምርቶች ውስጥ የሲም ቦክስ ሰርቨር (SIM BOX/SIM Servers)፣ ከፍተኛ ኃይል ያላቸው የጨረር መሳሪያዎች (Laser pointers (high output power)፤ ሌዘር ጠቋሚዎች እና የኤሌክትሪክ ሽጉጦች Taser flashlights (electric guns) የመሳስሉትን በሀገር ደኅንነት፤ በኢኮኖሚ እና በሰዎች አካል እና ጤና ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርሱ ምርቶችን ያካትታል፡፡

ነገር ግን አስተዳደሩ ለትምህርት ወይም ለጥናት እና ምርምር ዓላማ ክልከላ የተደረገበት ምርት ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገባ፤ ከሀገር እንዲወጣ ወይም በሀገር ውስጥ እንዲመረት፤ እንዲገጣጠም እና እንዲፈጠር በልዩ ሁኔታ ሊፈቅድ ይችላል፡፡ ይህን ፍቃድ ለማግኘት የሚያመለክት ሰው አሰተዳደሩ የሚያወጣውን ጥብቅ የሆኑ ቅደመ ሁኔታዎችን ማሟላት እና አመልካቹ በሀገር ደኅንነት ላይ የሚያደርሰው ስጋት አነሰተኛ መሆኑ ሲረጋገጥ ብቻ ነው፡፡

ገደብ የተደረገበት ምርት ማለት፡- በኢንፎርሜሽን ደኅንነት ላይ ሊያደርስ ከሚችለው አሉታዊ ተጽዕኖ አንጻር በዚህ አዋጅ መሠረት አግባብነት ባለው የድህንነት ማረጋገጫ ፍቃድ ብቻ ወደ ሀገር እንዳይገባ፤ ከሀገር እንዳይወጣ ወይም ጥቅም ላይ እንዳይውል ገደብ የተደረገበት የቴክኖሎጂ ምርት ነው፡፡

በሀገራችን ከደኅንነት ሁኔታ አንጻር ገደብ የተደረገባቸው የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ምርቶችን አስተዳደሩ በየጊዜው ዝርዝራቸውን የሚያወጣ ሲሆን ከነዚህም ምርቶች ውስጥ የደኅንነት ካሜራዎች እና DVR/NVR (Security Cameras and DVR/NVR)፤ የመገናኛ ሬዲዮዎች (Walkie Talkie Radio)፤የጂፒኤስ መከታተያዎች እና የጂፒኤስ ፍጥነት ገዳቢዎች (GPS Trackers and GPS Speed Limiters)፤ የአለምአቀፍ የዳሰሳ ሳተላይት ሲስተም (ጂኤንኤስኤስ) ተቀባዮች (Global Navigation Satellite System (GNSS) receivers)፤ የቪዲዮ ኮንፈረንስ መሳሪያዎች (Video Conference Equipment)፤ ጌትዌይ( Gateway)፤ የአውታረ መረብ መቀየሪያ (Network Switch)፣ ራውተር (Router)፤ ገመድ አልባ የመዳረሻ ነጥቦች (Wireless Access Points)፤ የገመድ አልባ ተቆጣጣሪዎች (Wireless Controllers)፤ የአውታረ መረብ /ማከማቻ አገልጋዮች (Network/Storage Servers) እና ሌሎች ለሀገር ደኅንነት ስጋት የሆኑ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ምርቶችን ይጨምራል፡፡

ነገር ግን እነዚህ ምርቶች በሀገር ላይ ያላቸው የደኅንነት ስጋት አነስተኛ ሲሆን የድህንት ማረጋገጫ ፍቃድ በማውጣት ወደ ሀገር ለማስገባት ፤ለማስወጣት ወይም ጥቅም ላይ ለማዋል ይቻላል፡፡

የደኅንነት ማረጋገጫ ፍቃድ ማለት፡- ይህን አዋጅ መሠረት በማድረግ የተለዩ ገደብ የተጣለባቸውን ምርቶች ወደ ሀገር ለማስገባት ፤ለማስወጣት ወይም ጥቅም ላይ ለማዋል የሚሰጥ ፍቃድ ነው፡፡ በዚህ አዋጅ አንቀጽ 6 መሠረት አስተዳደሩ ገደብ የተደረገበትን ምርት በመጠቀም ቁጥጥር የሚደረግባቸውን ተግባራት ለማከናወን የሚያስችል የደኅንነት ፍቃድ ማረጋገጫ ይሰጣል፡፡ በአጠቃላይ አስተዳደሩ የሚከተሉትን የደኅንነት ማረጋገጫ ፍቃድ አይነቶችን የሚሰጥ ሲሆን ይህም፡-

  • ምርቶች ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት የሚያስችል ቅድመ ፍቃድ
  • ወደ ሀገር ውስጥ ለገቡ ምርቶች የማስለቀያ
  • ምርቶች ወደ ውጪ የመላኪያ ወይም
  • ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለማምረት፤ለመሸጥ እና ሌሎች ቁጥጥር የሚደረግባቸው ተግባራት ለማከናወን የሚያስችል ፍቃድ ነው፡፡

ነገር ግን በዚህ አዋጅ መሠረት በአስተዳደሩ የሚሰጠው የደኅንነት ማረጋገጫ ፍቃድ ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ብሔራዊ ደኅንነትን ከማስጠበቅ እና የቴክኖሎጂዎችን የቴክኒክ ደረጃ እና ብቃት ከማረጋገጥ አንጻር የሚሰጡትን ፍቃድ እና ቁጥጥር አያስቀርም፡፡

ይህ አዋጅ በአንቀጽ 4 ላይ ክልከላ እና ገደብ ስለተጣለባቸው የኤሌክትሮኒክስ ምርቶች ሁኔታ እና የአስተዳደሩን ኃላፊነት እና ተግባር የደነገገ ሲሆን በዚሁም መሠረት አስተዳደሩ፡-

  • ክልከላ እና ገደብ የሚጥልባቸውን ምርቶችን ከብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት እና ከሌሎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት፤ ይለያል በመመሪያ ያወጣል፤
  • በመመሪያ ገደብ ወይም ክልከላ የተጣለባቸውን ምርቶች ዝርዝር በየአመቱ ከቴክኖሎጂ እድገት እና ተለዋዋጭነት አንጻር ማሻሻያ ማድረግ ይኖርበታል፤
  • በኢንፎርሜሽን ደኅንነት ላይ ስጋት ወይም አደጋ የሚፈጥር አዲስ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ምርት ወደ ሀገር በሚገባበት፤ ከሀገር በሚወጣበት ወይም በሀገር ውስጥ በማንኛውም መልኩ ጥቅም ላይ በሚውልበት ወቅት ተጨማሪ ክልከላ ወይም ገደብ ሊጥል ይችላል፤
  • ክልከላ ወይም ገደብ የሚደረግባቸውን ምርቶች ዝርዝር በዌብሳይት እና በተለያዩ አማራጮች ለሕዝብ ተደራሽ ማድረግ እንዳለበት ይደነግጋል፡፡

የደኅንነት ፍቃድ የተሰጠው ሰው እና የተቆጣጣሪ ግዴታ

ይህ አዋጅ የተከለከሉ ተግባራትን ጨምሮ የደኅንነት ፍቃድ የተሰጠው ሰው እና የተቆጣጣሪ ግዴታዎችን በመዘርዘር አስቀምጧል፡፡

የተከለከሉ ተግባራት

አዋጅ በአንቀጽ 5 ስር የተከለከሉ ተግባራትን ያስቀመጠ ሲሆን ይህም፡-

  • በዚህ አዋጅ አንቀጽ 4 ን
    • ንዑስ አንቀጽ 1 መሠረት ማለትም አስተዳደሩ ከብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት እና ከሌሎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት መመሪያ በማውጣት ክልከላ እና ገደብ የጣለባቸውን ምርቶችን በመጠቀም ማንኛውንም ቁጥጥር የሚደረግበትን ተግባራት ማከናወን፤
  • የጸና የደኅንነት ማረጋገጫ ፍቃድ ሳይኖረው በዚህ አዋጅ አንቀጽ 4 ንዑስ አንቀጽ 1 መሠረት ገደብ የተደረገበትን ምርት በመጠቀም ማንኛውንም ቁጥጥር የሚደረግበትን ተግባራት ማከናወን የተከለከለ ነው በማለት ይደነግጋል፡፡

ነገር ግን በዚህ አዋጅ መሠረት የተደነገገው ክልከላ ቢኖርም፤ክልከላ የተደረገበትን ምርት ለትምህርት ወይም ለጥናት እና ምርምር ዓላማ ወደ አገር እንዲገባ፤ ከአገር እንዲወጣ ወይም ጥቅም ላይ እንዲውል አስተዳደሩ መመሪያ በማውጣት እና የቁጥጥር ሥርዓት በመዘርጋት ሊፈቅድ ይችላል፡፡

የደኅንነት ፍቃድ የተሰጠው ሰው ግዴታ

አዋጅ በአንቀጽ10 ስር የደኅንነት ማረጋገጫ ፍቃድ የተሰጠው ሰው ግዴታዎችን በመዘርዘር ያስቀመጠ ሲሆን ማንኛውም የደኅንነት ማረጋገጫ ፍቃድ የተሰጠው ሰው፡-

  • የደኅንነት ማረጋገጫ ፍቃድ ምርት ለተፈቀደለት ዓላማ እና ወሰን ብቻ የመጠቀም፤
  • ምርቶችን አስመልክቶ የተሰጠውን ፍቃድ ወይም ፍቃድ ያገኘበትን ምርት ለሦስተኛ ወገን በማንኛውም መልኩ አስተዳደሩን ሳያሳውቅ እና ፍቃድ ሳያገኝ ያለማስተላለፍ፤ ያለማዋስ፤ እንዲጠቀምበት ያለማድረግ እና በሌላ ሰው እጅ እንዳይገባ የማድረግ፤
  • የተሰጠውን ፍቃድ ምርቱን በሚይዝበት እና በሚጠቀምበት ወቅት የመያዝ፤
  • ለፍቃዱ መሰጠት አስፈላጊ የሆኑ መስፈርቶች ላይ ለውጥ ሲኖር ለአስተዳደሩ ወዲያውኑ የማሳወቅ፤
  • ፍቃድ የተሰጠበት ምርት ሲበላሽ፤ ሲጠፋ፤ ሲሰረቅ ወይም በማንኛውም ሁኔታ ከቁጥጥር ውጪ መሆኑን እንዳወቀ በ8 ሰዓት ውስጥ ለአስተዳደሩ ማሳወቅ
  • አስተዳደሩ የቁጥጥር ኃላፊነቱን በሚወጣበት ወቅት የሚጠይቃቸውን አስፈላጊ መረጃዎች የማቅረብ እና ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ የመስጠት፤

የተቆጣጣሪ ግዴታ

ይህ አዋጅ በአንቀጽ 17 ስር አንድ ተቆጣጣሪ የስራ ተግባሩን ሲያከናውን ሊከተለው የሚገባውን ስነ ምግባር እና ግዴታውን ያስቀመጠ ሲሆን ይህም ማንኛውም ተቆጣጣሪ ፡-

  • ቁጥጥር በሚያደርግበት ወቅት ማንነቱን የሚገልጽ መታወቂያ የመያዝ እና የማሳየት፤
  • በተሰጠው ሥልጣን እና ተግባር ወሰን ብቻ ኃላፊነቱን የመወጣት፤
  • በትጋት፤ በታማኝነት እና በጥንቃቄ ኃላፊነቱን የመፈጸም፤

በአጠቃላይ በቁጥጥር ወቅት የሚያገኘውን ማንኛውንም መረጃ ወይም ሰነድ በሚስጢር የመጠበቅ ኃላፊነት እና ግዴታ እንዳለበት ይደነግጋል፡፡

ማጠቃለያ

በአጠቃላይ ይህን አዋጅ እና አዋጁን ለማስፈጸም በሚወጡ ደንቦች እና መመሪያዎች ላይ የተቀመጡ ሌሎች ግዴታዎችን ማክበር እንዳለበት ይደነግጋል፡፡