መግቢያ
በዓለም አቀፍም ይሁን በሀገር አቀፍ ሕግጋት እውቅና ተሰጥቷቸው ጥበቃ ከሚደረግላቸው መብቶች አንዱ የግል ነጻነት መብት ነው፡፡ የግል ነጻነት መብት ሲባል በግለሰቦች አካልም ሆነ ንብረት ወይም የይዞታ መብት ላይ የሚደረግን አግባብነት የሌለው ጣልቃ ገብነት ለማስከበር ሲባል የተቀመጠ መብት ነው፡፡ አግባብነት የሌለው ጣልቃ ገብነት ሁከት የሚባል ሲሆን ከዚህ በመነሳት ሁከት በማንኛውም ሕጋዊ ሰብዓዊ ወይም ኢኮኖሚያዊ መብት ላይ የሚደረግ ወረራ ወይም አግባብነት የሌለው ጣልቃ-ገብነት ነው ብሎ ማስቀመጥ ይቻላል፡፡
ሁከት ወይም በይዞታ ላይ የሚደረግ ወረራን መከላከልና ማስከበር በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ-መንግሥት እንዲሁም ሀገሪቱ በተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ጥበቃ የተደረገለት ከመሠረታዊ ሰብዓዊ መብቶችና ነጻነቶች አንዱ ነው፡፡ ሁከት በወንጀልና በፍትሐብሔር ጉዳዮች ላይ የተለያዬ ገጽታ ያለው ቢሆንም በመሠረታዊነት ጥበቃ በሚደረግለት መብት ባሕርይ ግን ተመሳሳይነት አላቸው፡፡ ይህም ንበረትን በነጻነት የማስተዳደር፣ የመቆጣጠርና የመጠቀም …ወዘተ መብቶችን ያጠቀልላል፡፡ ይህም የሆነው ባለይዞታ የሆነ ሰው የንብረቱ ባለሃብት እንደሆነ ስለሚገመትና ሁከትን በሕግ መከልከልም ማሕበረሰባዊ ደኅንነትና ሰላምን ለማስጠበቅ የሚረዳ በመሆኑ የተነሳ ነው፡፡ ይህም ከወንጀል ሕጉ አንቀጽ 686 መገንዘብ እንደሚቻለው ሁከት በሌላ ሰው ሰላማዊ ይዞታ ላይ በኃይል ድርጊት፣ በዛቻ፣ በመሳሪያ በቡድን ሊፈጸም የሚችል በመሆኑ ነው፡፡
በዚህ አጭር ጽሁፍ የሁከት ምንነት፣ ሁከት ተፈጠረ የሚባልበት ሁኔታና ጊዜ፣ ሁከት በፍትሐብሔርና በወንጀል ጉዳዮች ያለው ልዩነትና ሁከት የሚወገድባቸው መንገዶች የሚሉትን እንመለከታለን፡፡
ሁከት ምንድን ነው?
በጥቅሉ ሲታይ ሁከት በሚንቀሳቀሱ ወይም በማይንቀሳቀሱ ንበረቶቸ ወይም ይዞታዎች ላይ የሚደረግ ጣልቃ ገብነት ነው፡፡ የጣልቃ ገብነቱ ዓይነትም የንብረቱን ሁኔታ ወይም ይዘት በመለወጥ፣ ንብረቱን በኃይል በመያዝና በመድፈር፣ ያለሕግ ወይም ያለፈቃድ በመውረርና በመቆጣጠር፣ ከሕጋዊው ባለመብት ወይም ባለይዞታ ላይ በመንጠቅና በመሰወር …ወዘተ ሊፈጸም ይችላል፡፡ የሁከት ተግባር በማይንቀሳቀሱ ንበረቶች ላይ (ለምሳሌ እንደ መኖሪያ ቤት፣አጥር ግቢ፣ መሬት፣ ጀልባ፣ መስሪያ ቤት፣ ድርጅት፣ ሕንጻ፣ ቢሮዎች፣ መጋዘን ወይም ግምጃ ቤት የመሳሰሉ የተከለሉና የተጠበቁ ቦታዎች ላይ) ወይም በተንቀሳቃሽና በልዩ ተንቀሳቃሽ የንብረት ጥቅሞች ላይ ሊፈጸም ይችላል፡፡ በተጠበቁና በተከለሉ ቦታዎች ላይ ዛቻና ማስፈራራትን፣ መሳሪያን ወይም ሌላ ማንኛውንም ኃይል በመጠቀም የሚደረግ የሁከት ተግባር የፍትሐብሔር ብቻ ሳይሆን የወንጀልም ኃላፊነት ሊያመጣ ይችላል፡፡ ምክንያቱም ይህ ዓይነት ሁከት በንብረት ላይ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ሰዎች ግላዊ ነጻነትም ጭምር ሊፈጸም የሚችል በመሆኑ ነው፡፡ በተፈጠረው ሁከት ላይ የሚወሰዱ የፍትሐብሔርም ይሁን የወንጀል እርምጃዎችም እንደተፈጠረው የሁከት ዓይነት የሚወሰኑ ናቸው፡፡
ሁከት ተፈጠረ የሚባለው መቼ ነው?
ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው በወንጀልና በፍትሐብሔር ጉዳዮች ላይ ሁከት ተፈጥሯል የሚባልባቸው ሁኔታዎች የሚጋሩት የጋራ ባህርይ ቢኖርም የሚለያዩባቸው ሁኔታዎችም አሉ፡፡ በመሆኑም በሁለቱ የሕግ ማዕቀፎች አንጻር ሁከት ተፈጠረ ማለት ስለሚቻልበት ሁኔታ በእያንዳዱ ህጎች ለይቶ መመልከት ተገቢ ይሆናል፡፡
በፍትሐብሔር ጉዳይ ሁከት ተፈጥሯል የሚባልባቸው ሁኔታዎች
- ጣልቃ-ገብነቱ በማያሻማ ወይም በማያጠራጥር የሌላ ሰው ይዞታ ላይ የተደረገ ሲሆን፡- አንድ ይዞታ የማያሻማ ወይም የማያጠራጥር ነው የሚባለው በስውር ወይም በድብቅ የተያዘ ይዞታ ሲሆን ነው፡፡ ይህም የሆነው በስውር ወይም በድብቅ የተያዘ ይዞታ ማናቸውንም የይዞታ መብት የማይሰጥ በመሆኑ ነው (የፍ/ብ/ሕ/ቁ 1146 (1)፡፡ አንድ ይዞታ በስውር ወይም በድብቅ የተያዘ ነው የሚባለው ደግሞ ንበረቱን በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ መንገድ ይዞ የሚገኘው ሰው በያዘው ንብረት ላይ አንዳች መብት እንደሌለው ለማሳሰብ በሚያስችል ሁኔታ ባለይዞታነቱን የደበቀ እንደሆነ ወይም ንብረቱን ይዞ የሚጠቀመው ሰው ንብረቱ ወይም ነገሩ የእርሱ ስለመሆኑ በአካባቢያዊ ሁኔታዎች (Circumstances) ተመዝኖ የሚያጠራጥር ሆኖ ሲገኝ ወይም ንብረቱን የያዘው ስለሌላ ሰው እንደሆነ መሆኑን የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 1146 (2)፣ (3)) ይደነግጋል፡፡ ምክንያቱም አንድን ንብረት ስለሌላ ሰው ሆኖ የያዘ ሰው እንደንብረት ጠባቂ እንጂ እንደ ባለይዞታ ሆኖ ስለማይቆጠር ነው (የፍ/ብ/ሕ/ቁ. 1147 (1)) ፡፡ እዚህ ላይ ግን ይዞታን በጠባቂ አማካኝነት መያዝ አይቻልም ለማለት ሳይሆን ክርክር ባጋጠመ ጊዜ እውነተኛ ባለይዞታው ጠባቂው ሳይሆን የይዞታ መብቱን በጠባቂው አማካኝነት የሚፈጽመው ሰው መሆኑን ለማመልከት ነው፡፡ ይህንንም “በቀጥታ ወይም እንዲያው ነገሩን ይዞ ብቻ በሚቆይ በአንድ ሌላ ሰው አማካኝነት ባለይዞታ ለመሆን ይቻላል” ከሚለው የፍትሐብሔር ሕጉ (ቁጥር 1141) ድንጋጌ መረዳት ይቻላል፡፡
- የማያጠራጥር ይዞታ ይዞታውን በቋሚነት በመቆጣጠር ወይም ለረዥም ጊዜ በማስተዳደርና አስፈላጊውን የንብረት ጥበቃ በማድረግ ወይም ስለዚሁ ይዞታ ያልተቋረጠ ክትትል በማድረግና በይዞታው በመገልገል ሊሆን ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ በይዞታው ላይ የሚፈጠሩ ጊዜያዊ መሰናክሎችና መቋረጦች ወይም ሊወገዱ የሚችሉ እንቅፋቶች ባለይዞታነትን አያስቀሩም (የፍ/ብ/ሕ/ቁ. 1142)) ፡፡
- በሌላ በኩል በአንድ ይዞታ ላይ ሁከት አደረሰ የተባለው ሰው በንብረቱ ላይ የባለቤትነት መብት ቢኖረው እንኳን ባለቤቱ በተመሳሳይ ጊዜና ሁኔታ የንብረቱ ትክክለኛ ባለይዞታ እስካልሆነ ድረስ ሁከቱን የሚያስቀረው አይሆንም (የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ውሳኔዎች ፡ እነሳሙኤል ውብሸትና ብዙነህ በላይነህ፡ መ.ቁ 27506፣ ቅጽ 6፣ ገጽ 192-194 ፣ እነ ረዳት ሳጅን አያኖ አንጀሎና ወ/ሮ አለሚቱ ጫሌቦ ፡ መ/ቁ. 36645 ቅጽ 9 ገጽ 31 ፣ ዋት ኢንተርናሽናል ኃ/የተ/የግ/ማ እና ወ/ሮ ፎዚያ ቃዲ ፣ መ/ቁ 70801 ፣ቅጽ 13 ገጽ 441-442)፡፡ የንብረት ባለቤት የሆነ ሰው በተመሳሳይ የባለይዞታነት መብት (Possessory Right) ከሌለው ንብረቱን እጅ አድርጎ በያዘው ሰው ላይ የመፋለም ክስ (Petitory Action) ከሚያቀርብ ውጭ ሁከት ተፈጥሮብኛልና ሁከቱ ይወገድልኝ ብሎ ጥያቄ ሊያቀርብ አይችልም ማለት ነው፡፡
- ሁከቱ የተፈጠረው ጉድለት በሌለበትና ባለይዞታው በእውነት በሚያዝበት ይዞታ ላይ ሲሆን፡- ይዞታ ጉድለት የሌለበት (Non-Defective) ነው የሚባለው በኃይል ወይም በሌላ ሕገ-ወጥ ተግባር ያልተገኘና የማያጠራጥር ወይም የማያሻማ እንዲሁም ለረዥም ጊዜ ያልተቋረጠ ወይም ያልቀረ ሲሆን ነው፡፡ ይህም ማለት ይዞታው በምክንያታዊ ሰው እይታ ወይም አስተሳሰብ ለተራዘመና ላልተለመደ ጊዜ ከቆየ በባለይዞታውና በንብረቱ መካከል የነበረው ግንኙነት እንደተቋረጠ ስለሚቆጠር ይዞታ አለ ለማለት ስለሚያዳግት ነው፡፡ በሌላ በኩል አንድ ይዞታ ሕጋዊ ነው የሚባለው በሰላማዊ ሁኔታ የተያዘ ሲሆን ነው ፡፡ በሌላ አገላለጽ ሁከቱን በኃይል ወይም በሌላ መንገድ ለማስወገድ ይዞታው ራሱ በሌላ ሁከትና ኃይል የተያዘ መሆን የለበትም፡፡ የይዞታን እውነተኛነት በተመለከተም ባለይዞታው ይዞታውን በእጁ ማድረጉ እንደተበቀ ሆኖ አያያዙም በተረጋገጠና ባልተጭበረበረ መንገድ ወይም በማናቸውም ሁኔታ ሕገወጥ ባልሆነ መንገድ ያልተያዘ መሆን ይኖርበታል፡፡ እዚህ ላይ ሁከት ተፈጥሯል አልተፈጠረም የሚለውን ጉዳይ ለመወሰን ባለይዞታው ንብረቱን እጅ ያደረገበት መንገድ (ለምሳሌ የኪራይ ውል) አስፈላጊ አይደለም የሚሉ ክርክሮች ይነሳሉ፡፡ ይህም ከባለይዞታነት የተሻለ የባለሃብትነት መብት ካለ ይዞታ ይለቀቅልኝ የሚል ጥያቄ ከማቅረብ የሚያግድ አለመሆኑንና የንብረት ባለቤትነትም ከንብረት ባለይዞታነት አንጻር ሲታይ ሰፋ ያለ መብትን የሚያጎናጽፍ ነው በሚል የሚቀርብ ክርክር ነው፡፡ የሆነ ሆኖ ግን የሕጉ ዓላማና መንፈስ የሚያሳየው ባለቤትነት ስላለ ብቻ አንድን ሕጋዊ ባለይዞታ በሁከት ይወገድልኝ ጥያቄ ወይም በኃይል ማስለቀቅ እንደማይችል ነው፡፡ ከዚህ ይልቅ ሁከት ተፈጠረብኝ የሚል አካል ይዞታውን ያገኘበት ሕጋዊ አግባብና በእውነት የሚያዝበት መሆኑ ግንዛቤ መወሰድ እንዳለበት ያስገድዳል፡፡
በወንጀል ጉዳይ ሁከት ተፈጥሯል ስለሚባልባቸው ሁኔታዎች
የሁከት ማድረግ ወንጀል በማይንቀሳቀስ ንብረት (ቤት ፣ ይዞታ፣ መሬት ሕንጻ) ላይ ከሚፈጸሙ ወንጀሎች አንዱ መሆኑን የወንጀል ሕጉ ከአንቀጽ 685-687 አስቀምጧል፡፡ ይሁን እንጂ ዓለም አቀፉ የሕግ ሳይንስም ይሁን የእኛ ሀገር ሕግ ሁከት የግል ነጻነቶች መገለጫ በሆኑ የግል ቤቶችና ሌሎች የተከለሉ ወይም የተከለከሉ ቦታዎች ላይ የሚፈጸም የመድፈር ተግባርም (Invasion of Privacy or Trespass) በነዚህ ይዞታዎች ላይ ሁከት በማድረስ ሊፈጸም እንደሚችል ያመለክታሉ፡፡ ያም ሆነ ይህ ግን ጥበቃ በተደረገላቸው ይዞታዎች ላይ የሚደረግ የሁከት ተግባር ተፈጸመ የሚባለው የሚከተሉት ሁኔታዎች ሲሟሉ መሆኑን ዓለም አቀፉ ተሞክሮ ያሳያል፡፡
1. ሁከት የፈጠረው ሰው ወደአንድ ይዞታ ወይም የተከለከለ ስፍራ ለመግባት ወይም ገብቶ ለመቆየት በሕግ ወይም በሌላ አግባብ ያልተፈቀደለት (Neither Licensed nor Previledged to eneter or remain) መሆን አለበት፡- ይህም ማለት ሁከት የፈጠረው ሰው ወደሌላ ሰው ይዞታ ለመግባት ወይም ገብቶ ለመቆየት የማይፈቀድለት መሆኑን የሚያውቅ ወይም ከነገሮች ሁኔታ አንጻር ያልተፈቀደለት ስለመሆኑ በቂ የማወቅ እድል ያለው መሆን ይኖርበታል ማለት ነው፡፡ የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 686 (1) እንደሚደነግገው ማንም ሰው እያወቀ መብት ሳይኖረው ወይም ጥቅም ለማግኘት ሲል በሌላ ሰው ሰላማዊ ይዞታ ላይ ሁከት ሊፈጠር እንደሚችል አስቀምጧል፡፡ “በሕግ ሳይፈቀድለት (ከሕግ ውጭ)” የሚለው አነጋገር የሕብረተሰቡን ሰላምና ደሕንነት ለማረጋገጥ ሲባል በፍርድ ቤት የመበርበሪያ ትእዛዝ ወይም የሚመለከተውን አካል በማስፈቀድ የሚደረጉ ጣልቃ-ገብነቶችን ከሁከት ተግባር ለመለየት የተቀመጡ ልዩ ሁኔታዎች ናቸው፡፡ ወደ አንድ ይዞታ ለመግባት ወይም ይዞ ለመቆየት የሚያስችል ፈቃድ በሕግ በተፈቀደ መብት፣ ምክንያታዊ ሰው ሊረዳው በሚችለው ምልክት፣ በንግግር ወይም በጽሑፍ ሊገለጽ ይችላል፡፡
እዚህ ላይ አከራካሪው ጉዳይ አንድ ቦታ ወይም ይዞታ ያልተፈቀደና የተከለከለ መሆኑን እንዴት ማወቅ ይቻላል የሚለው ነው፡፡ ይህ ጥያቄ የሚነሳው በግልጽ በሕግ ክልከላና ጥበቃ የሚደረግባቸውን ወይም በግልጽ በሚታወቅ ሁኔታ የተከለከሉ ይዞታዎችን በሚመለከት ሳይሆን ብዙ ጊዜ የመዝናኛ ስፍራዎች፣ የሕዝብ አገልግሎት መስጫ ተቋማት (ለምሳሌ የሕዝብ ቤተ-መጻሕፍት)፣ ለተወሰኑ ሰዎች ብቻ የተፈቀዱ አካባቢዎችን ወዘተ የሚመለከት ነው፡፡ ይህን ጉዳይ በተመለከተ ምንም እንኳን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 686 (1) በጥቅሉ “የሌላ ሰው ይዞታ የሆነውን መሬት ወይም ሕንጻ የወረረ ወይም የያዘ ወይም ፤ በማናቸውም ሌላ አኳኋን የሌላ ሰው ሰላማዊ ይዞታ በሆነ መሬት ላይ ሁከት ያደረሰ እንደሆነ …” በማለት ቢያስቀምጠውም በሌላ የወንጀል ሕጉ ድንጋጌ (አንቀጽ 604) ላይ ግን እነዚህን ይዞታዎች ለመዘርዘር ይሞክራል፡፡ በመሆኑም የወንጀል ሕግ በጠባቡ የሚተረጎም በመሆኑ ከላይ “በማናቸውም ሌላ አኳኋን” ሚለው አገላለጥ ከወንጀል ሕጉ ከራሱ ድንጋጌዎችና ዓላማዎች አንጻር በጥንቃቄ መታየት ይኖርበታል፡፡ ለምሳሌ ያሕል የተለቀቁና የተተው ይዞታዎች ላይ ሁከት ተፈጠረብኝ የሚል የግል አቤቱታ ወይም እንደነገሩ ሁኔታ የወንጀል ክስ አቅራቢ ይዞታው በእርግጥም የተለቀቀ፣ የተተወና ለማንኛውም ሰው ክፍት የተደረገ ስለመሆኑ ወይም አለመሆኑ አካባቢው ላይ ያለውን ሁኔታ በአግባቡ በመመለከትና በመመርመር ማረጋገጥ ይጠበቅበታል፡፡
2. ወደ ይዞታው ለመግባት ወይም ለመቆየት የሚያስችል ቅድመ-ሁኔታ (ሕግ፣ የጥንቃቄ እርምጃ ወይም ስነ-ስርዓት) አለመሟላት፡- በሌላ በኩል ምንም እንኳን ይዞታው ለመግባት የተፈቀደ ቢሆንም ወደይዞታው ለመግባት የሚፈልግ አካል ግን ለመግባት ወይም ለመያዝ ወይም በይዞታው ለመቆየት የሚያስፈልጉ ቅድመ-ሁኔታዎችን ማሟላት ሊጠበቅበት ይችላል፡፡ ለምሳሌ ያሕል የተፈቀደለት ልዩ ባለሙያ መሆኑን ማሳየት፣ ነዋሪ መሆኑን ወይም የፍተሻ ቅድመ-ሁኔታን መፈጸም ሊጠበቅበት ይችላል፡፡ በተጨማሪም በይዞታው ለመገልገል ወይም ለመጠቀም ከሚያስፈልግ ነገር ውጭ ሌሎች አላስፈላጊ እቃዎችን ወይም መሳሪያዎችን መያዝ አለመያዙ ሁከት የማድረግ ወይም አለማድረግ ሁኔታዎችን የሚወስኑ ጉዳዮች ናቸው፡፡ ለምሳሌ ወደ አንድ ላብራቶሬ ለመግባት የሚያስፈልግ ቅድመ-ሁኔታ ወደአንድ ሆቴል ለመግባት ከሚያስፈልግ ቅድመ-ሁኔታ ሊለይ ይችላል፡፡
ተገቢው ጥንቃቄና ሕጋዊ ስነ-ስርዓት ሳይፈጸም የሚደረግ ሁከትን በተመለከተ ይሕንኑ ስነ-ስርዓትና የጥንቃቄ እርምጃ መውሰድ በሚገባው የመንግሥት ሠራተኛ ወይም የሰራዊት አባል ሊፈጸም የሚችል ሲሆን ይዞታውን ለመቆጣጠር ከሚያስችል ኃይል በላይ ወይም በሕግ ከታዘዘው ወይም ከተፈቀደው ስርዓት ውጭ የሰውን ንብረት መያዝን ወይም መውሰድን የሚመለከት ሲሆን ይሕ በሆነ ጊዜ በሁከት ማድረግ ወንጀል ብቻ ሳይሆን ሥልጣንን ያለአግባብ በመገልገልና የግል ይዞታዎችን በመድፈር ወንጀልም ሊያስጠይቅ ይችላል፡፡
ሁከትን ማስወገድ የሚቻልባቸው መንገዶችና የመፍትሔ እርምጃዎች
የሁከት ማስወገጃ ዘዴዎችና ሕጋዊ የመፍትሔ እርምጃዎች አሁንም እንደጉዳዩ ባሕርይ (ፍትሐብሔር ወይም ወንጀል) ሊለያይ ይችላል፡፡ ነገር ግን ከምክንያታዊ ጥርጣሬ በላይ የተረጋገጠ ሁከት የማድረግ የወንጀል ተግባር የፍትሐብሔር ኃላፊነትም ጭምር ሊያመጣ የሚችል መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ይሆናል፡፡
በፍትሐብሔር ጉዳይ ሁከትን ማስወገድ
በአንድ ንብረትና በባለቤቱ ወይም ባለይዞታው መካከል ያለውን ግንኙነት ሕግ እውቅና ሰጥቶ ከማንኛውም ሰው የሚመጣን ሕገ ወጥ ጣልቃ ገብነት ቅድሚያ በመከላከል ጥበቃ ያደርጋል፡፡ ሕግ ለንብረት መብት ጥበቃ ለማድረግ ሊደርስ የሚፈልግበት ግብ ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞችን በመንከባከብ ሰዎች ጥሪቶቻቸው በተቀላጠፈ ሁኔታ ለመጠቀም እንዲችሉ የሚያነሳሳቸው ይሆናል፡፡ በመሆኑም ከንብረቱ ጋር በሕግ ተቀባይነት ያለው ግንኙነት ያለው ሰው ባገኘው የንብረት መብት ላይ ሌላ ሰው ጣልቃ በሚገባበት ጊዜ የንብረት መብት ማስከበሪያ የሆኑ መንገዶችን በመጠቀም የንብረት መብቱ እንዲከበርለት ማድረግ ይችላል፡፡ አንድ ባለይዞታ መብቱን በሁለት መንገድ ማስከበር ይችላል፡፡
- ኃይል በመጠቀም (የፍ/ብ/ሕ/ቁ. 1148)
- የሁከት ይወገድልኝ አቤቱታ በፍርድ ቤት (የፍ/ብ/ሕ/ቁ.1149)
የይዞታ መብትን ኃይልን በመጠቀም ማስከበር
አንድ ባለ ይዞታ ይዞታው ላይ ንጥቂያ ወይም ሁከት የተፈጠረበት እንደሆን በኀይል ለመከላከል ይችላል፡፡ ይኸውም ንብረቱን ከነጣቂ ወይም በድብቅ ከሚወስድ ሰው ማስለቀቅ ማለት ነው፡፡ ይህን የማስከበሪያ መንገድ ስንጠቀም ግንዞቤ ውስጥ ማስገባት ያለብን ሁኔታዎች አሉ፡፡ እነዚህም፡-
- የኃይል ተግባሩ ለችግሩ ምክንያት በሆነው ወይም ችግሩ በፈጠረው ሰው ላይ እንጂ በሦስተኛ ወገን ላይ ተፈጻሚ መሆን እንደማይገባው።
- የኃይል መጠኑ ተመጣጣኝ መሆን አለበት።
- ኃይል የምንጠቀመው ወዲያውኑ ሁከቱ እንደተፈጠረ መሆን አለበት።
እነዚህ ሁኔታዎች በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 78 ከተደነገገው የመከላከል መብት ጋር የጠበቀ ቁርኝት ያለው ይመስላል፡፡ የተቃጣን ጥቃት በመመለስ ሕይወትን፣ አካልን ወይም ንብረትን በሕግ የተሰጠ መብትን በመከላከል ማስቀረት እንዲቻል ሕገ ወጥ ጥቃትን የሚያወግዝ ጠቅላላ መግባቢያ ላይ የቆመ መርህ ነው፡፡ ይህም በተለይም ጉዳዩን ለፍርድ ቤት ለማቅረብ ዳኝነት ለመጠየቅ ጊዜ በማይኖርበት አጋጣሚ ብቸኛ ወደ ፍርድ ቤት ሳይሔድ መብትን የማስከበሪያ መንገድ ነው፡፡
ይህ የመብት ማስከበሪያ መንገድ በሚንቀሳቀስም ሆነ በማይንቀሳቀስ ንብረት (ይዞታ) ላይ ልንጠቀምበት የምንችል መሆኑ ከድንጋጌው መረዳት እንችላለን፡፡ ይኸውም በፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 1148(1) “… ሁከት ለማንሳት…” እና 1148(2) “ንጥቂያ ሲወሰድ … ወዲያውኑ በጉልበት በማስለቀቅ …” የሚሉት ቃላት ማንም ሰው በይዞታው ላይ ለሚቃጣበት ሁከት ተመጣጣኝና አስፈላጊ የሆነ እርምጃ በመውሰድ ሁከቱን ሊያስወግድ እንደሚችል ያስቀምጣል፡፡ ተመጣጣኝነቱ በተፈጠረው ሁከት ልክ የሚወሰን ሲሆን አስፈላጊነቱ የሚመነጨው ደግሞ በንብረቱ ላይ ወደፊት ሊደርስ ከሚችለው ጉዳትና የመፍትሔ እርምጃው ከሚሰጠው ጊዜ አንጻር የተቀመጠ ነው፡፡ ይሕን የአስፈላጊነትና የተመጣጣኝነት መርህ ከፍትሐብሔር ሕጉ ቁጥር 1148 (3) ድንጋጌ መረዳት ይቻላል፡፡ ድንጋጌው “… የጊዜው አጋጣሚ ካላስገደደ በቀር ባለይዞታ የሆነ ሰው ከእጅ እልፊት መታገስ አለበት” በማለት ያስቀምጣል፡፡ ኃይልን በመጠቀም ሁከትን ለማስወገድ የሚወሰደው እርምጃ ሁከቱ በተፈጠረበት ጊዜ ወይም ሁከቱ ከተፈጠረ በኋላ ወዲያውኑ ሊወሰድ እንደሚችል የሚያስቀምጥ ሲሆን “ወዲያውኑ” የሚለው አገላለጽ በንጥቂያ ወይም ንብረትን በመደበቅ ወይም በመሰወር የተፈጸመን የሁከት ተግባር የንብረቱን መዳረሻ በመከታተልና በማስመለስ የሚፈጸም መሆኑን ያመለክታል፡፡ የድንጋጌው ንዑስ አንቀጽ (2) “… እጅ ያደረገው ነገር በንጥቂያ ወይም በስውር የተወሰደበት እንደሆነ” በማለት ማስቀመጡ ድንጋጌው የተቀመጠው ተንቀሳቃሽ ንበረቶችን ወይም እቃዎችን ለማስመለስ ታሳቢ ተደርጎ የተቀመጠ መሆኑን የሚያመለክት ሲሆን ይህ ማከለት ግን በማይንቀሳቀሱ ግዙፍ ንብረቶች ላይ የሚፈጸምን ሁከት በኃይል ወይም ጉልበት በመጠቀም ማስወገድ አይቻል ማለት አይደለም (የፍ/ብ/ሕ/ቁ 1148(1))፡፡ ኃይለን ወይም ጉልበትን በመጠቀም ይዞታን የማስከበር ሂደት አመክንዮ ሁከትን በመታገስ ጉዳዩን በፍርድ ከመመለስ ይልቅ ወዲያውኑ ችግሩን በማስወገድ ራስን መርዳት ተቀባይነት ያለው መሆኑን ያሳያል፡፡
በይዞታ ላይ የሚፈጠር ሁከትን በፍርድ ማስወገድ
በሕጋዊ ይዞታው ላይ ሁከት የተፈጠረበት ወይም ከሕግ ውጭ ንብረቱ የተወሰደበት ሰው ጉዳዩን ለፍርድ ቤት በማቅረብ እንደነገሩ ሁኔታ ፡
- በይዞታው ላይ የተፈጠረው ሁከት እንዲወገድ (cessation of interference) እና/ወይም
- ይዞታው ወይም ንብረቱ እንዲመለስ (restoration of possession) እና/ወይም
- በሁከቱ ምክንያት የደረሰ ጉዳት ካላ ካሳ እንዲከፈለው (compensation for damages)
በመጠየቅ የክስ አቤቱታ ማቅረብ እንደሚቻል በፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 1149 ተገልጿል፡፡ እነዚህ የመፍትሔ እርምጃዎች በአንድ ጊዜ ወይም እንደየሁኔታው በተናጠል ታይተው የሚተገበሩ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ በአንድ የመሬት ባለይዞታ ላይ የተሰራን ግዙፍ ሕንጻ ሁከት ለማስወገድ በሚል ከማፍረስ ይልቅ ካሳ በመክፈል ማሰናብት አማራጭ ላይኖረው ይችላል፡፡ ባለይዞታው የንብረቱ ባለሃብት ካልሆነ በቀር እነዚህን የመፍትሔ እርምጃዎች ለመጠቀም የሚፈልግ ማንኛውም ሰው ጥያቄውን ሁከቱ ከተፈጠረበት ወይም የያዘውን እቃ ከተነጠቀበት ጊዜ ጀምሮ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ማቅረብ ይጠበቅበታል፡፡
ከዚህ ድንጋጌ መረዳት እንደሚቻለው ሁከት ለማስወገድ በፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 1149 መሠረት የሚቀርብ የክስ አቤቱታ ወይም “ሁከት ይወገድልኝ ክስ” ተብሎ የሚጠራው ይዞታን የመከላከል ግብ አለው፡፡ የይዞታ መብት የሕግ ጥበቃ ስለሚደረግለት ሌላ ባለመብት ነኝ የሚል አካል በሕግ ላይ የተደነገገውን ሥርዐት በመከተል መብቱን ከማስከበር በስተቀር ኀይልን በመጠቀም ባለይዞታውን ማስለቀቅ በሕግ ተቀባይነት አይኖረውም፡፡
አንድ ሰው የፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 1149ን ጠቅሶ የሁከት ይወገድልኝ የክስ አቤቱታ በሚያቀርብበት ጊዜ እንደ ዋነኛ ማስረጃ ተደርጎ መቅረብ ያለበት የይዞታ መብቱን የሚናገርለትን የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ/ደብተር ወይም ማስረጃ ነው፡፡ የሰበር ሰሚ ችሎት በሰበር መዝገብ ቁጥር 31113 ግንቦት 19 ቀን 2000 ዓ.ም በሰጠው ፍርድ የሕግ ትርጉም የሁከት ይወገድልኝ ክስ ለማቅረብና መብትን ለማስከበር የይዞታ መብት አለ ለማለት የሚቻለው የይዞታ ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት በማቅረብ ነው ሲል የተረጐመው፡፡ ይሁን እንጅ የሰነድ ማስረጃ ማቅረብ የተፈጠረውን ሁከት ለማስረዳት ብቸኛና የመጨረሻ ማስረጃ ነው ማለት አይደለም፡፡ ከሳሽ የሆነው ወገን ባለይዞታነቱንና በይዞታው ላይ የተፈጠረውን የሁከት ተግባር በማናቸውም ሁኔታ ሊያስረዳ ይችላል፡፡ በሌላ በኩል ተከሳሹም ከከሳሹ የተሻለ የባለይዞታነት መብት ካለው ሊያቀርብ እንደሚችል የፍ/ሕ/ቁ. 1149 (3) ድንጋጌ ያስቀምጣል፡፡ ጥያቄው የቀረበለት የፍትሕ አካልም ተገቢውን የጥያቄውን ተገቢነት በመመርመር በባለይዞታውና በሁከት አድራጊው መካከል ያለው ግንኙነት ወደሌላ ሁኔታ ከማምራቱ በፊት ተቀብሎ ማስተናገድ ይኖርበታል፡፡
የወንጀል ተጠያቂነት
ምንም እንኳን የሁከት ተግባሩ በፍትሐብሔር ሕጉ መሠረት የተስተናገደ ቢሆንም ሁከቱ በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 23 እና አንቀጽ 686 ላይ የተመለከቱት ሁኔታዎች ከተሟሉ ማለትም ሁከት የመፍጠር ወይም ጥቅም ለማግኘት በማሰብ የተፈጸመ የሁከት ተግባር ከሆነ የግል አቤቱታ ሲቀርብበት በመቀጮ ወይም በቀላል እስራ ሊያስቀጣ ይችላል፡፡ በሌላ በኩል የተፈጸመው የሁከት ተግባር የወንጀል አፈጻጸም በኃይል ድርፈጊት፣ በዛቻ ወይም በብዙ ሰዎች ተባባሪነት ወይም አደገኛ መሳሪያ በመያዝ የሆ እንደሆነ በወንጀል ክስ አቅራቢነት እስከ አምስት ዓመት ለመድረስ በሚችል ጽኑ-እስራት የሚያስቀጣ ይሆናል፡፡
ማጠቃለያ
በአጠቃላይ በይዞታው ላይ ሁከት የተደረገበት ሰው ሕጉ ባስቀመጠው አግባብ ይዞታውን ማስመለስ እንዲሁም ጥፋት አድራሹ በሕግ እንዲቀጣ ማድረግ ይችላል፡፡
በንቃተ ሕግ፣ ትምህርትና ሥልጠና የተዘጋጀ