ክስ ማቋረጥ

ማውጫ

ይህን ጽሑፍ ያጋሩ

መግቢያ

የወንጀል ክስ ወንጀል ፈፅመዋል ተብለው በተጠረጠሩ ሰዎች ላይ በዋናነት በዐቃቤ ሕግ የሚቀርብ ነዉ፡፡ ይሁን እንጂ እኚ የቀረቡ ክሶች ሁልግዜም ይቀጥላሉ ማለት አይደለም፡፡ የተመሰረቱ ክሶች በተለያዩ ህጋዊ መክንያቶች ሊቋረጡ ይችላሉ፡፡ በአለማችን ላይ ሀገራት በወንጀል ፍትሕ ሥረዓታቸው ውስጥ የወንጀል ክስ በተጠርጣሪዎች ላይ ከተመሰረተ በኋላ በፍርድ ቤት በመታየት ላይ እያለ ክስ በተለያዩ ምክንያት ማቋረጥ የሚቻልበትን ሁኔታዎች በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥረዓታቸው ውስጥ ደንግገው ይገኛሉ፡፡ አገራችንም በ1954 በወጣው የወ/መ/ሥ/ሥ ሕግ እና የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 943/2008 ላይ ክስ የሚቋረጥባቸውን ሁኔታዎችን ደንግጋ ትገኛለች፡፡ ይህም ጹሁፍ የክስ ማቋረጥ ምንነት፤ ክስ ማቋረጥ የሚችልባቸው እና የማይቻልባቸው ወንጀሎች፤ ክስ የሚቋረጥባቸው ምክንያቶች፤ ክስን ለማቋረጥ ዐቃቤ ሕግ የፍርድ ቤት ፍቃድ ያስፈልገዋል ወይም አያስፈልገውም የሚሉትን ጥያቀዌዎች እንዲሁም ክስ ማቋረጥ የሚያስከትለውን ውጤቶች በአጭሩ ለመዳሰስ ይሞክራል፡፡

የክስ ማቋረጥ ምንንት

የተለያዩ አገራት በህጋቸው ውስጥ ክስ ማቋረጥ ማለት ምን ማለት እንደሆነ፤ ክስ በምን ምክንያት እንደ ሚቋረጥ፤ መቼ እንደሚቋረጥ፣ ማን እንደ ሚያቋርጥ በግልጽ በህጋቸው ውስጥ ደንግገው ይገኛሉ፡፡ ከዚህ ውስጥ በ1985 የወጣው የአውስትራልያ የወንጀል ሕግ ለፍትሕ ዓላማ ሲባል ለጊዜው የወንጀል ክስ የሚነሳበት ሁኔታ ነው በማለት ትርጉም ሲሰጠው፤ የህንዱ የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥረዓት ሕግ በአንቀጽ 321 ስር ዐቃቤ ሕግ ወይም ረዳት ዐቃቤ ሕግ በሙሉም ሆነ በከፊል በተከሳሽ ላይ የመሰረተውን ክስ የሚያቋርጥበት ወይም የሚተውበት ሁኔታ ነው በማለት ክስ ማቋረጥን ይተረጉመዋል፡፡

በአገራችን በ1954 የወጣው የወ/መ/ሥ/ሥ ሕግም ሆነ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 943/2008 ላይ ምንም እንኳን ስለ ክስ ማቋረጥ ቢጠቅሱም ነገር ግን ክስ ማቋረጥ ማለት ምን ማለት እንደሆነ በቀጥታ ትርጉም አይሰጡትም፡፡ ይሁን እንጅ ከነዚህ ህጎች እንደምንረዳው ክስ ማቋረጥ ማለት ዐቃቤ ሕግ ወይም ሌላ በሕግ ክስ ለመመስረት ሥልጣን የተሰጠው አካል አንድን በፍርድ ቤት እየታየ ያለ የወንጀል ክስ ለሕዝብ እና ለመንግሥት ጥቅም ሲል በሙሉም ወይም በከፊል ፍርድ ከመሰጠቱ በፊት ክሱን የሚያነሳበት ሁኔታ ነው፡፡

በሌላ በኩል አብዛኛው ጊዜ ክስ ማቆረጥ፤ ምሕረት እና ይቅርታ ማካከል ያለው ልዩነት እና አንድነት በአብዛኛው ሰው ላይ ግርታን የሚፈጥር ሲሆን፤ በአዋጅ ቁጥር 1089/2010 የምሕረት አሰጣጥ እና አፈጻጸም ሥነ-ሥርዓት አንቀጽ 2/1 ላይ ምሕረት ማለት ምን ማለት እንደሆነ ትርም የሚሰጥ ሲሆን ይህም፡-

“ምሕረት” ማለት፡- የወንጀል ምርመራ ከመጀመሩ በፊት፣ ከተጀመረ በኋላ፣ የክስ ሂደት ላይ እያለ ወይም የወንጀል ቅጣት ውሳኔ ከተሰጠ በኋላ በተመሳሳይ ወንጀል የተጠረጠሩ ወይም የቅጣት ውሳኔ ያገኙ ሰዎችን ያለምንም ገደብ ወይም በአንዳንድ ገደቦች ወይም ግዴታዎች ከወንጀል ተጠያቂነት ነጻ ማድረግ ነው በማለት ትርጉም ይሰጠዋል፡፡

በሌላ በኩል የይቅርታ አሰጣጥ እና አፈጻጸም ሥነ ሥርዓት ለመደንገግ የወጣ አዋጅ ቁጥር 840/2006 አንቀጽ 2/1 ላይ፡-

ይቅርታ ማለት ፡- የቅጣት ፍርድ በሙሉ ወይም በከፊል ቀሪ እንዲሆን ወይም የቅጣት ፍርዱ አፈጻጸም እና አይነት ቀለል ተደርጎ እንዲፈጸም ማድርግ ነው በማለት ትርጉም ሰጥቶት ይገኛል፡፡

የፖሊስ ምርማራ መዝበብ መዝጋት፣ ማቋረጥ እና የክስ ማቋረጥ እንድነት እና ልዩነት

በአብዛኛው ጊዜ ከክስ ማቋረጥ ጋር ተያይዞ የሚነሳው ጥያቄ የክስ ማቋረጥ እና የፖሊስ የወንጀል ምርመራ መዝገብ መዘጋት እና መቋረጥ አንድነት እና ልዩነት ሲሆን፤ የፖሊስ የወንጀል ምርመራ መዝገብ መዘጋት እና መቋረጥ የሚፈጸመው በተለያዩ ምክንያቶች የወንጀል ምርመራው መዝገብ ምርመርው ሳይጀምር ፤በምርመራ ላይ እያለ ክስ ተመስርቶ ፍርድ ቤት ሳይደርስ በፊት ዐቃቤ ሕግ የፖሊስ የወንጀል ምርመራ መዝገቡን ያሚዘጋበት እና የሚያቋርጥበት ሁኔታ ነው፡፡ነገር ግን ክስ መቋረጥ የመከናወነው የውንጀል ምርመራ ተጠናቆ ከስ ተመስርቶ ጉዳዩ በፍርድ ቤት በመታየት ላይ ሳለ ነው፡፡

የፖሊስ የወንጀል ምርመራ መዝገብ የሚዘጋበት ሁኔታ

የወ/መ/ሥ/ሥ ህገ አንቀጽ 39 የፖሊስ የወንጀል ምርመራ መዝገብ የሚዘገበትን ሁኔታዎች በመዘርዘር ያስቀመጠ ሲሆን ይህም ተጠርጣሪው የሞተ እንደሆነ ፤ተጠርጣሪው እድሜው ከ9 ዓመት በታች እንደሆነ፤ያለመከሰስ መብት ያለው እንደሆነ ፤ከዚ ቀደም ጉዳዩ ፍርድ ያገኘ እንደሆነ ፤ጉዳዩ በሌላ ፍርድ ቤት እየታየ ያለ እንደሆነ ዐቃቤ ሕግ የፖሊስ የወንጀል ምርመራ መዝገብን እንደሚዘጋ ይደነግጋል፡፡

የፖሊስ የወንጀል ምርመራ መዝገብ ማቋረጥ

የወ/መ/ሥ/ሥ ሕግ አንቀጽ 42 ላይ የፖሊስ የወንጀል ምርመራ መዝገብ የሚቋረጥበት ሁኔታዎች በመዘርዘር ያስቀመጠ ሲሆን፤ ይህም በተጠርጣሪው ላይ ክስ ማቅረብ የሕዝብ እና የመንግሥትን ጥቅም ያሚያስጠብቅ ከሆነ እና በፍትሕ ሚኒስተሩ እንዲያቋርጥ ሲታዘዝ፤ጥፋተኛ ለማድረግ በቂ ማስራጃ ያሌለ እንደሆነ ፤የተጠረጠረውን ሰው ለማግኘት ያማይቻል ከሆነ ወይም በሌለበት ክሱ ሊታይ ያማይችል ከሆነ፤በይርጋ የታገደ እንደሆነ ወይም ለተፈጸመው ወንጀል ምሕረት ወይም ይቅርታ የተሰጠ እንደሆነ ዐቃቤ ሕግ የፖሊስ የወንጀል ምርመራ መዝገብ እንደሚዘጋ በህጉ ላይ ተደንግጎ ይገኛል፡፡ነገር ግን በወ/መ/ሥ/ሥ/ ህጉ 42 ስር የፖሊስ የወንጀል ምርመራ መዝገብ የሚቋረጥበት ምክንያት የሆኑ ሁኔታዎች ባሌሉ ወይም በተሟሉ ጊዜ ለምሳሌ ጥፋተኛ ለማድረግ በቂ ማስራጃ ባለመኖሩ ምክንያት የተቋረጠ የውንጀል ምርመራ መዝገብ በቂ ማስረጃ በተገኘ ጊዜ፤ የተጠረጠረውን ሰው ለማግኘት ወይም በሌለበት ክሱ ሊታይ ያማይችል በመሆኑ ምክንያት የተቋረጠ የውንጀል ምርመራ መዝገብ ተጠርጣሪው ሲገኝ ፤በፍትሕ ሚኒስተሩ ትእዛዝ የተቋረጠ የውንጀል ምርመራ መዝገብ የፍትሕ ሚኒስተሩ እንደገና ምርመራው እንዲቀጥል ስያዝ ዓቃቤ ሕግ በወ/መ/ሥ/ሥ/ ቁጥር አንቀጽ 42 መሠረት ያቋረጠውን የፖሊስ ያምርመራ መዝገብ በድጋሚ ሊያንቀሳቀስ ይችላል፡፡

ክስ የሚቋረጥባቸው ህጋዊ ሁኔታዎች

በ1954 የወጣው የወ/መ/ሥ/ሥ ሕግ እና የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 943/2008 ላይ ክስ የሚቋረጥባቸው ሁኔታዎች እና ምክንያቶችን በመዘርዘር አስቀምጧል፡፡

የወ/መ/ሥ/ሥ ሕግ አንቀጽ 122 ላይ ስለ ክስ ማንሳት በሚያትተው አንቀጽ ስር ከባድ የግፍ አገዳደል ፤ከባድ የወንበዴነት ተግባር መሰራት ከቀረበው ክስ በቀር ዐቃቤ ሕግ በተከሳሽ ላይ የቀረበውን ማንኛውንም ክስ በፍርድ ቤቱ ፈቃድ ከፍርድ በፊት ክሱ በሚሰማበት በማንኛውም ጊዜ ክሱን ለማንሳት ይችላል በማለት የደነገገ ሲሆን፤ ክሱን እንዳነሳ በመንግሥት ታዝዣለው ብሎ ዐቃቤ ሕግ ለፍርድ ቤቱ ሲያመለከረት ዐቃቤ ህጉ ክሱን እንዲያነሳ ከመንግሥት የታዘዘ መሆኑን ፍርድ ቤቱ ከተረዳ ፍርድ ቤቱ መፍቀድ አለበት በማለት ይደነግጋል፡፡በተጨማሪም ዐቃቤ ሕግ በማንኛውም ግዜ ለወደፊት ክሱን ለመቀጠል እንደሚችል በግጽ አስቀምጧል፡፡

በሌላ በኩል የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 943/2008 6/3 (ሠ) ስር ዐቃቤ ሕግ የፌዴራል መንግሥትን በመወከል የወንጀል ጉዳዩች ክስ ይመሰርታል፣ ይከራከራል፣ ለሕዝብ ጥቅም አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው ክስ ያነሳል፣ የተነሳ ክስ እንዲቀጥል ያደርጋል:: ሆኖም ጉዳዩ ሀገራዊ ይዘት የሚኖረው ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩን በማማከር ክስ ስለሚያነሳበት አግባብ መመሪያ ያወጣል፤በማለት ደንግጎ ይገኛል፡፡

በ1954 የወጣው የወ/መ/ሥ/ሥ ሕግ እና የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 943/2008 ስር የተቀመጡትን ድንጋጌዎች ስንመለለት አንዳንድ ጥያቄዎችን የሚያጭሩ ሲሆኑ ከዚህም ውስጥ ዓቃቤ ሕግ ብቻውን ክስ ማቋረጥ ይችላል ወይስ የፍርድ ቤትን ፍቀድ ማግኘት አለበት፤ዓቃቤ ሕግ ክስ የማያቋርጥባቸው እና የሚያቋርጥባቸው የወንጀል አይነቶች አሉ የሚሉት ናቸው፡፡

ዓቃቤ ሕግ ብቻውን ክስ ማቆረጥ ይችላል ወይስ የፍርድ ቤትን ፍቀድ ማግኘት አለበት የሚለውን ጥያቄ ስንመለከት

በ1954 የወጣው የወ/መ/ሥ/ሥ ሕግ አንቀጽ 122 ስር ዓቃቤ ሕግ በተከሳሽ ላይ ያቀረበውን ማንኛውንም ክስ በፍርድ ቤቱ ፈቃድ ከፍርድ በፊት ክሱ በሚሰማበት በማንኛውም ጊዜ ክሱን ለማንሳት ይችላል፡፡ ክሱን እንዳነሳ በመንግሥት ታዝዣለው ብሎ ዓቃቤ ሕግ ለፍርድ ቤቱ ሲያመለክት ዓቃቤ ህጉ ክሱን እንዲያነሳ ከመንግሥት የታዘዘ መሆኑን ፍርድ ቤቱ ከተረዳ መፍቀድ አለበት፡፡ ፍርድ ቤቱ ክሱን ለማንሳት ወይም ላለማንሳት ለሚሰጠው ውሳኔ ምክንያቱን መስጠት አለበት በማለት የደነገገ ሲሆን ከወ/መ/ሥ/ሥ ህጉ እንደምንረዳው ዓቃቤ ሕግ ክስ ለማቋረጥ የፍርድ ቤትን ፍቃድ ማግኘት እንዳለበት ሲሆን፤ ነገር ግን የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 943/2008 አንቀጽ 6/3 (ሠ) ስር ዓቃቤ ሕግ የፍርድ ቤት ፍቃድ ሳያስፈልግው የሕዝብ እና መንግሥትን ጥቅምን ለማስጠብቅ ሲል ክስ ያነሳል የተነሳ ክስ እንዲቀጥል ያደርጋል በማለት ደንግጎ ይገኛል፡፡ ከላይ እንደምንረዳው በ1954 የወጣው የወ/መ/ሥ/ሥ ሕግ አንቀጽ 122 መሠረት ክስ ለማንሳት የፍርድ ቤት ፍቃድ እንደሚያስፈልግ ሲሆን በሌላ በኩል የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 943/2008 አንቀጽ 6/3 (ሠ) መሠረት ክስ ለማንሳት የፍርድ ቤት ፍቃድ ማግኘት እንደማያስፈልገው ነው፡፡

እነዚህ ህጎች በእኩል ደረጃ ላይ ያሉ የሕግ አዋጆች ሲሆኑ በሕግ ፍልሰፍና በእኩል ደረጃ ላይ ያሉ ህጎች የቀድሞ ሕግ እና አዲስ የወጣ የሕግ አንቀጾች በተጋጩ ጊዜ አዲስ የወጣው የሕግ አንቀጽ ተቀባይነት ይኖራዋል፡፡በመሆኑ በያዝነው ጉዳይ ላይ የወ/መ/ሥ/ሥ ሕግ በ1954 ዓ/ም የወጣው ሲሆን የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ማቋቋሚያ አዋጅ በ2008ዓ/ም የወጣ በመሆኑ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ማቋቋሚያ አዋጅ አንቀጾች ተቀባይነት እና ተፈጻሚነት አላቸው፡፡ በመሆኑ ዓቃቤ ሕግ ክስን ያለ ፍርድ ቤት ፍቃድ ለማቋረጥ ይችላል ያሚለው የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ማቋቋሚያ አዋጅ አንቀጽ ተቀባይነት እና ተፈጻሚነት ይኖረዋል፡፡

ዓቃቤ ሕግ ክስ የማያቋርጥባቸው እና የሚያቋርጥባቸው የወንጀል አይነቶች የወንጀል አይነቶች አሉ ወይ ያሚለውን ጥያቄ ስንመለከት

በ1954 የወጣው የወ/መ/ሥ/ሥ ሕግ አንቀጽ 122/1 መሠረት ዓ/ሕግ ከባድ ያግፍ አገዳደል እና ከባድ የውንብድና ወንጀልን ክስ ማቋረጥ እንደማይችል ያስቀመጠ ሲሆን ነገር ግን የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 943/2008 ዓቃቤ ሕግ ክስ ማቋረጥ የማይችልባቸው ያስቀመጠው ምንም ያወንጀል አይነት የሌለ በመሆኑ ዓቃቤ ሕግ ማንኛውንም ያወንጀል ክስ ማንሳት ይችላል የሚያስብል ነው፡፡

እነዚህ ህጎች በእኩል ደረጃ ላይ ያሉ የሕግ አዋጆች ሲሆኑ በሕግ ፍልሰፍና በእኩል ደረጃ ላይ ያሉ ህጎች የቀድሞ ሕግ እና አዲስ የወጣ የሕግ አንቀጾች በተጋጩ ጊዜ አዲስ የወጣው የሕግ አንቀጽ ተቀባይነት ይኖራዋል፡፡በመሆኑ በያዝነው ጉዳይ ላይ የወ/መ/ሥ/ሥ ሕግ በ1954 ዓ/ም የወጣው ሲሆን የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ማቋቋሚያ አዋጅ በ2008ዓ/ም የወጣ በመሆኑ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ማቋቋሚያ አዋጅ አንቀጾች ተቀባይነት እና ተፈጻሚነት አላቸው፡፡ በመሆኑ ዓቃቤ ሕግ ከባድ ያግድያ ወንጀል እና ከባድ የውንብድና ውንጀልን ክስን ማቋረጥ እንደሚችል እንረዳለን፡፡

በሌላ በኩል የካቲት 25/2003 ዓ.ም የወጣው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የወንጀል ፍትሕ ፖሊሲ በኢትዮጵያ ሕጎች እና ኢትዮጵያ ባፀደቀቻቸው አለም ዓቀፍ ስምምነቶች ውስጥ በሰው ልጅ ላይ የሚፈፀሙ ወንጀልች ተብለው የተደነገጉትን ወንጀሎች የሰው ዘር በማጥፋት፣ ያለፍርድ የሞት ቅጣት እርምጃ በመውሰድ፣ በአስገዲጅ ሰውን በመሰወር ወይም ኢ-ሰብዓዊ ድብደባ መፈፀም ወንጀሎች ለሕዝብ ጥቅም ሲባል ክስ የሚመሠረትባቸው የወንጀል ጉዳዮች ናቸው በማለት ያሚያስቀምጥ ሲሆን፡፡ እነዚህ ወንጀሎች በአለማቀፍ ደረጃ በማንኛውም አገር ፍርድ ቤት የሚታዩ በይርጋ የማይታገዱ ይቅርታ እና ምሕረት ያማይደርግላቸው ወንጀሎች እንደማሆናቸው ዓቃቤ ሕግ እንዚህን ወንጀሎች ማቋረጥ አይችልም፡፡

ሌላው ጥያቄ ዐቃቤ ሕግ ክስ እንዲቋረጥ መጠየቅ የሚቻለው መቼ ነው በየትኛው ደረጃ ነው የሚለው ሲሆን

የወ/መ/ሥ/ሥ ሕግ አንቀጽ122/1 ላይ ዐ/ሕግ በተከሳሹ ላይ ያቀረበውን ማንኛውንም ክስ ከፍርድ በፊት ክሱ በሚሰማበት በማንኛውም ጊዜ ክሱን ለማንሳት እንደሚችል ይደነግጋል፡፡

ክስን ማቋርጥ ለምን በሕግ ተፈቀደ

የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 943/2008 አንቀጽ 6/3 (ሠ) ስር ዓቃቤ ሕግ ለሕዝብ ጥቅም አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው ክስ ያነሳል፣ የተነሳ ክስ እንዲቀጥል ያደርጋል:: በማለት ያስቀመጠ ሲሆን ነግር ግን የሕዝብ ጥቅም ምን ማለት እንደሆነ የሕዝብ ጥቅም ያሚያስብሉ ሁኔታዎች ምን ምን እንደሆነ አይገልጽም፡፡ነገር ግን የካቲት 25/2003 ዓ.ም የወጣው የአገራችን የወንጀል ፍትሕ ፖሊሲ የሕዝብ ጥቅም ማለት ምን ማለት እንደሆነ ባይገልጽም ለሕዝብ ጥቅም ሲባል ክስ የማይመሠረትባቸው ጉዲዮች በመዘርዘር አስቀምጧል፡፡ ይህም፡-

  • የተፈፀመው ወንጀል በጣም ቀላል መሆኑን ሕጉ በግልጽ በደነገገ ጊዜ እና ክሱ ቢመሠረት የሚወሰነው ቅጣት ተግሳጽ፣ ማስጠንቀቂያ፣ ወቀሳ መሆኑ በጠቅሊይ ዓቃቤ ሕግ ከታመነ፣
  • ተጠርጣሪው በእድሜ መጃጀት ወይም በማይድን በሽታ በመያዙ ምክንያት ጉዳዩን በፍርድ ቤት መከታተል የማይችል የሆነ እንደሆነ፤
  • ወንጀሉ ከባድ ቢሆንም በተጠርጣሪውና በግል ተበዳይ መካከል የተፈጠረው የወንጀል ምክንያት በመደበኛ የወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ከሚሰጠው ውሣኔ ይልቅ በባሕላዊ ሕጎች እና ተቋማት ዘላቂ መፌትሔ ያገኛል ተብሎ በጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ ከታመነ፤
  • ጉዲዩ በክስ ሂደት ውስጥ ቢያልፍ ብሔራዊ የደኅንነትን ወይም የዓለም አቀፍ ግንኙነትን የሚጎዳ ይሆናል ተብሎ ከታመነበት፤
  • በቀላል እሥራት ወይም በሕጉ መሠረት በግል አቤቱታ ብቻ የሚያስቀጡ እና በግለሰብ ላይ የተፈፀሙ ወንጀሎች ሆነው በተበዳዩ እና በተጠርጣሪው መካከል እርቅ ተፈፅሞ ከሆነ፤
  • የክስ መመሥረት ተመጣጣኝና ሚዛናዊ ያልሆነ የጎንዮሽ ጉዳት የሚያስከትሌ ከሆነ፤
  • የተፈፀመው የወንጀል ድርጊት በቀላል እሥራት የሚያስቀጣና ጉዳቱ አነስተኛ ሆኖ ተከሳሹ ጥፋቱን አምኖ ተበዳዩን ወይም ስለእርሱ ባለመብቶች የሆኑትን በግልጽ ይቅርታ ከጠየቀ እና ያደረሰውን በደል መልሶ ለማስተካከል ዝግጁ ከሆነ፤
  • በማንኛውም ምክንያት ጉዳዩ ሥልጣን ባለው ፍ/ቤት ሳይቀርብ በመቆየቱ ወቅታዊነቱን ወይም አስፈላጊነቱን ሲያጣ፤
  • የተፈፀመው ድርጊት በጣም ቀላል ወንጀል ከሆነ እና ጉዳቱ አነስተኛ ሆኖ ተጠርጣሪው ያደረገው ድርጊት የወንጀል ባሕርይ እንዳለው ፍፁም ከሆነ ግንዛቤ ማጣት ከሆነ እና የመሳሰለት ናቸው፡፡ በማለት ይዘረዝራል፡፡

ክስ ማቋረጥ የሚያስከትለው ውጤት

የወ/መ/ሥ/ሥ ሕግ አንቀጽ 122 መሠረት ተጠርጣሪው ላይ ሌላ አዲስ ክስ ያልተመሰረተበት እና አዲስ ክስ ያልተዘገጀ እንደሆነ ተከሳሹ ለጊዜው ይለቀቃል በማለት የሚያስቀምጥ ሲሆን ነገር ግን ዐቃቤ ሕግ የተነሳውን ክስ ለወደ ፊት ለመቀጠል የሚከለክል ነገር እንዳሌለ ይደነግጋል፡፡ በተጨማሪም የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 943/2008 አንቀጽ 6/3 (ሠ) ላይ ዐቃቤ ሕግ ለሕዝብ ጥቅም አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው የተነሳ ክስ እንዲቀጥል ያደርጋል በማለት ደንግጎ ይገኛል::

በንቃተ ሕግ፣ ትምህርትና ሥልጠና የተዘጋጀ