በሕፃናት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች

ማውጫ

ይህን ጽሑፍ ያጋሩ

መግቢያ

ሕጻናት በአካላቸው ያለመጠንከር እና በአዕምሯቸው ለጋነት የተነሳ ራሳቸውን በራሳቸው ለመምራት የማይችሉ በመሆናቸው የሌሎች ድጋፍና ጥበቃ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ስለሆነም ሕፃናት የተሟላ ስብዕና እንዲኖራቸው እንዲሁም ለጉዳቶች ሳይዳረጉ እንዲያድጉ ልዩ ጥበቃና እንክብካቤ ማግኘት የሚያስችላቸው የሕግ ማዕቀፍ እና ከለላ ሊሰጣቸው ይገባል፡፡

የሕጻናቱን መብትና ደኅንነት ለመጠበቅ ትኩረት የሰጡ የተለያዩ ዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ የሕግ ማዕቀፎች ወጥተው ተግባራዊ እየተደረጉ ይገኛል፡፡ ሀገራችንም እነዚህን ዓለም አቀፍና አህጉራዊ የሕግ ድንጋጌዎችን ተቀብላ ከማጽደቋም ባሻገር በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ-መንግሥት፣ በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ እና በወንጀል ሕግ ውስጥ በርካታ ድንጋጌዎች ተካተዋል፡፡ ሆኖም እነዚህን ሕጎች በመተላለፍ በሕፃናት ላይ ወንጀሎች ይፈፀማሉ፡፡ በዚህ አጭር ጽሁፍ ስለነዚህ ወንጀሎች በተለይም በኢ.ፌ.ዲ.ሪ የወንጀል ሕግ የተደነገጉትን የምንመለከት ይሆናል፡፡

በሕጻናት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ምንነት

ሕፃን የሚለው ቃል የማኅበራዊ ትርጉም እንደየማህበረሰቡ አኗኗርና ባህላዊ ሁኔታ የሚለያይ ሊሆን ይችላል። ሕፃናት በየትኛውም ማኅበረሰብ ውስጥ ተገቢውን የሕግ ከለላ ማግኘት ይቻላቸው ዘንድ በዓለም አቀፍም ሆነ በሀገራችን የሕግ ማዕቀፎች ሰፍረው ጥቅም ላይ የዋሉ ትርጓሜዎች አሉ። የተባበሩት መንግስታት የሕፃናት መብቶች ስምምነት አንቀጽ 1 ላይ “ህፃን ማለት ማንኛውም ዕድሜው ከ18 ዓመት በታች የሆነ ሰው ማለት ነው” ይላል። የአፍሪካ የሕፃናት መብቶች እና ደኅንነት ቻርተር አንቀጽ 2 በተመሳሳይ መልኩ “ሕፃን ማለት ማንኛውም ዕድሜው ከአሥራ ስምንት ዓመት በታች የሆነ የተፈጥሮ ሰው ነው” ሲል ተርጉሞታል፡፡

የሀገራችንን ሕጎች ስንመለከትም በኢትዮጵያ ቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 215 መሠረት “ለአካለ መጠን ያልደረሰ ሰው ማለት ጾታ ሳይለይ ማንኛውም እድሜው 18 ዓመት ያልሞላው ልጅ ነው” በማለት ትርጉም ሰጥቶታል። እንዲሁም በሰው የመነገድና ሰውን በሕገ-ወጥ መንገድ ድምበር የማሻገር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣው አዋጅ ቁጥር 1178/2012 አንቀጽ 2(10) ላይ “ሕጻን ማለት ዕድሜው ከ18 ዓመት በታች የሆነ ማንኛውም ሰው ነው” በማለት ተመሳሳይ ትርጉም አስቀመጦ ይገኛል፡፡ የኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ የወንጀል ኃላፊነት ያለባቸውን ሰዎች ለመለየት ለአካለ መጠን ያልደረሱ በማለት በዕድሜ ከፋፍሎ ያስቀመጠ ቢሆንም ህፃን ወይም አካለ መጠን ያልደረሰ የሚለውን ትርጉም ያላስቀመጠ በመሆኑ ከላይ የተጠቀሱትን ዓለም አቀፍና የሀገር ውስጥ የሕግ ድንጋጌዎችን መጠቀም ተገቢ ነው። በመሆኑም ሕፃን የሚለው ትርጉም 18 ዓመት ያልሞላው ለአካለ መጠን ያልደረሰ ሰው መሆኑ ከዓለም አቀፍም ሆነ ከሀገር ውስጥ ሕጎች መረዳት ይቻላል።

በሕፃናት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን ስንመለከት ደግሞ በዓለም አቀፉ የሕጻናት መብት ስምምነት እንደተደነገገው ሕፃኑ በወላጆቹ፣ ወይም በሕጋዊ አሳዳሪዎቹ ወይም በማንኛውም ሌላ ሰው ሥር በሚገኝበት ጊዜ ማናቸውም ዓይነት አካላዊና አእምሮአዊ ጥቃት፣ በደል፣ ጭቆና፣ ግዴለሽ ወይም ቸልተኛ አያያዝ፣ ማንገላታት ወይም ብዝበዛና የወሲብ ጥቃት እንዳይደርስባቸው አባል አገራት ተገቢ የሆኑ ሕጋዊ፣ አስተዳደራዊ፣ ማኅበራዊና ትምህርታዊ እርምጃዎችን ይወስዳሉ በማለት አስቀምጦታል (ዓለም አቀፍ የሕፃናት መብት ስምምነት (እ.ኤ.አ 1989) አንቀጽ 19 (1))፡፡ ከዚህ አንቀጽ ድንጋጌ ይዘት በመነሳት በሕጻናት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ማለት ሆነ ተብሎ ኃይልን ወይም ጉልበትን በመጠቀም ወይም ለመጠቀም በማስፈራራት ወይም በማታለል ወይም በማባበል፣ በአንድ ሕጻን ጤንነት፣ ሕይወት፣ ዕድገት፣ ወይም ክብር ላይ ተጨባጭ ወይም ወደ ፊት ሊከሰት የሚችል ጉዳት የሚያደርስ ድርጊት መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

በሕፃናት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች

በሌሎች ሰዎች ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች የተመለከቱ የሕግ ድንጋጌዎች ለሕፃናት

እንደማንኛውም ሰው ተፈፃሚ የሚሆኑ ቢሆንም በኢ.ፌ.ዲ.ሪ የወንጀል ሕግ አምስተኛ መጽሐፍ ላይ በሕፃናት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ተደንግገው ይገኛሉ፡፡ በመሆኑም በልዩ ሁኔታ በሕፃናት ላይ ጥቃት በማድረስ ከሚፈፀሙ ወንጀሎች ወስጥ፡-

በሰው ህይወት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች

  • ሕፃን መግደል (አንቀጽ 544)
  • በጎጅ ልማዳዊ ድርጊቶች አማካኝነት በሰው ህይወት፣ አካል እና ጤና ላይ ጉዳት በማድረስ የሚፈፀሙ ወንጀሎች፤
  • በጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች አማካይነት በእርጉዝ ሴቶች እና ሕፃናት ህይወት ላይ ጉዳት ማድረስ( አንቀጽ 561)
  • በጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች አማካይነት በእርጉዝ ሴቶች እና ሕፃናት አካል ላይ ጉዳት ማድረስ( አንቀጽ 562)
  • የሰውን ሕይወት፣ አካል ወይም ጤንነት ለአደጋ በማጋለጥ የሚፈጸሙ ወንጀሎች
  • ሰውን ለአደጋ ማጋለጥ ወይም መተው (በጤናው፣ በዕድሜው፣ በሁኔታው ወይም በማናቸውም ሌላ ምክንያት ራሱን ለመጠበቅ የማይችለውን ሌላ ሰው…. በዕድሜው የሚለው ለሕፃናት ተፈፃሚ ይሆናል) (አንቀጽ 574)
  • ለአካለ መጠን ያልደረሱ ልጆችን መጉዳት (ሕፃናትን የሚመለከት) (አንቀጽ576)

በሰው የግል ነጻነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች

  • ለአካለ መጠን ያልደረሰ ልጅን መጥለፍ (አንቀጽ 589)፣
  • ሕጻንን ማለዋወጥ እና የራስ ያልሆነን ህጻን መውሰድ (አንቀጽ 591)፣
  • ለአካለ መጠን ያልደረሰ ልጅን አለማቅረብ (በፍርድ ቤት ትእዛዝ ወይም ውሳኔ መሠረት ልጁን እንዲረከብ መብቱ ለሆነ ሰው ወይም ተቋም አላስረክብም ማለት (አንቀጽ 592 )፣
  • በመልካም ጠባይ እና በቤተዘመድ ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች (በግብረ ሥጋ ነጻነትና ንፅህና ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች)
  • ዕድሜያቸው አስራ ሶስት ዓመት በሆነና አስራ ስምንት ዓመት ባልሞላቸው ልጆች ላይ የሚፈጸም የግብረ ስጋ ድፍረት በደል (አንቀጽ 626) ፣
  • በሕፃናት ልጆች ( ዕድሜያቸው አስራ ሶስት ዓመት ያልሞላ) ላይ የሚፈፀም የግብረ ሥጋ ድፍረት በደል (አንቀጽ 627) ፣
  • ለተፈጥሮ ባሕርይ ተቃራኒ የሆኑ የግብረስጋ ግንኙነቶች
  • ለአካለ መጠን ያልደረሱ ልጆች ላይ የሚፈጸም የግብረሰዶም ጥቃትና ለክብረ-ንጽህና ተቃራኒ የሆኑ ድርጊቶች (አንቀጽ 631)፣

በመልካም ጠባይ ላይ ከሚፈጸሙ ወንጀሎች

  • ለመልካም ሥነ ምግባርና ለመልካም ፀባይ ተቃራኒ የሆነ ብልግናና አሣፋሪ ሥራን በአደባባይ ለአካለመጠን ባልደረሰ ልጅ ፊት ሲፈፀም አንቀጽ 639/2
  • ጸያፍ ወይም የብልግና ወይም ለመልካም ጠባይ ተቃራኒ የሆኑ ነገሮችን ለሕዝብ መግለፅና፤ እንደዚህ ያሉትን ነገሮች ለአካለ መጠን ላልደረሱ ልጆች አስቦ ያሳየ፣ የሰጠ ወይም ያስረከበ (አንቀጽ 640 /2/ (ለ)) ወይም ለዚሁ ዓላማ አካለ መጠን ያልደረሱ ልጆች የግብረስጋ ግንኙነት የፈፀሙ በማስመሰል ያሳየ ወይም ሀፍረተ ስጋቸው እንዲታይ ያደረገ (አንቀጽ 640 (ሐ) እና ለአካለመጠን ያልደረሱ ልጆችን አደጋ ላይ ከሚጥሉ ስራዎች የመጠበቅ ኃላፊነት ያለመወጣት (አንቀጽ 644)፣

በቤተ ዘመድ ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች

  • በሁለቱም ጾታ ላይ ሊፈፀም የሚችል ቢሆንም አንቀጽ 648 ላይ ያለዕድሜ ጋብቻ ብዙ ጊዜ በሴቶች ላይ የሚፈጸም ጥቃት ሆኖ እንመለከታለን፣

በክብር መዝገብ ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች

  • የሕፃን መወለድን ወይም ተጥሎ መገኘትን አለማስታወቅ (አንቀጽ 656)፣
  • አስመስሎ ህፃንን ማቅረብ ወይም መለወጥ (አንቀጽ 657) ፣
  • የቀለብ መስጠት ግዴታን አለመፈጸም (አንቀጽ 658 )፣
  • የልጅ ማሳደግ ግዴታን አለመፈጸም (አንቀጽ 659 )፣

ከወንጀል ሕጉ በተጨማሪ በሰው የመነገድ እና ሰውን በህገ- ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣ አዋጅ ቁጥር 1178/12 በሴቶች እና ሕጻናት ላይ ሊፈፀሙ ስለሚችሉ ወንጀሎች እና የሚያስከትሉት ቅጣት አካቶ ይገኛል፡፡

አዋጁ በሰው የመነገድ፣ ሰውን በህገ ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር እና በህገ-ወጥ መንገድ ለስራ ወደ ውጪ አገር መላክ ወንጀሎች በዜጎች አካል፣ ህይወት እና ደኅንነት ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርሱና ለሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚያጋልጡ በመሆናቸው እንዲሁም በሰው መነገድ በተለይም በሴቶች እና ሕጻናት መነገድን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠርና ወንጀል ፈፃሚዎችን ለመቅጣት የወጣ ነው፡፡

በአዋጁ እንደተደነገገው ማንኛውም ሰው ሌላውን ሰው በባርነት ወይም በባርነት መሰል ተግባር፣ በአገልጋይነት ወይም ዕዳ መያዣነት የያዘው፣ አካሉን በማውጣት ወይም በዝሙት አዳሪነት ወይም መሰል የወሲብ ተግባር ብዝበዛ የፈፀመበት፣ በግዳጅ ስራ ወይም አገልግሎት፣ በልመና፣ በወንጀል ተግባር፣ በግዳጅ ጋብቻ ያሰማራ ወይም ሕፃናትን በጉልበት ስራ የበዘበዘ ወይም እነዚህን መሰል የብዝበዛ ተግባራት የፈፀመ እንደሆነ በሰው የመነገድ የወንጀል የፈፀመ በመሆኑ በወንጀል ይቀጣል፡፡ (በሰዎች የመነገድ እና ሰዎችን በህገ ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር አዋጅ 1178/12 አንቀጽ 3) ፡፡

በአዋጁ አንቀጽ 7 መሠረት ማንኛው ሰው ሌሎች ሰዎች ከሚፈጽሙት የዝሙት አዳሪነት ተግባር ወይም የሥነ-ምግባር ብለሹነት ለመጠቀም ሲል ወይም የሌላውን ሰው ፍትወተ ሥጋ ፍላጎት ለማርካት በማስብ ሌላውን ሰው ለዝሙት ተግባር ያሰማራ፣ ያገናኘ፣ ያቀረበ፣ በዝሙት አዳሪነት ያስቀመጠ፣ የሥራ ወይም የመኖሪያ ቤቱን ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ለዚህ ተግባር ያዋለ ወይም ያከራየ ወይም በማናቸውም ሌላ መንገድ የሌላውን ሰው የዝሙት ድርጊት ወይም የሥነ-ምግባር ብልሹነት መጠቀሚያ አድረጎ መያዝ፡፡

በሌላ በኩል ማንኛውም ሰው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የገንዘብ ወይም ቁሳዊ ጥቅም ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ ሰውን በሕገ ወጥ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ ግዛት እንዲገባ፣ ከኢትዮጵያ ግዛት እንዲወጣ፣ በኢትዮጵያ ግዛት እንዲተላለፍ ያደረገ ወይም ሰው ከኢትዮጵያ ግዛት ለማስወጣት ዝግጅት ያደረገ፣ በሂደት ላይ የተገኘ፣ ያጓጓዘ ወይም የተቀበለ እንደሆነ በህገ-ወጥ መንገድ ድንበር በማሻገር ወንጀል ተጠያቂ ይሆናል፡፡

ማጠቃለያ

በአጠቃላይ ሰዎች በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸው ውስጥ የሰዎችን መብት የማክበር ግዴታ ያለባቸው መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ በልዩ ሁኔታ ደግሞ ሕፃናት ለጥቃት ተጋላጭ ከሚባሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ውስጥ ቀዳሚዎቹ በመሆናቸው መብቶቻቸውን ማክበር ተገቢ ነው፡፡ ህብረተሰባችን ይህን በመገንዘብ እና ለሕፃናት ቅድሚያ በመስጠት ከላይ የተመለከትናቸው ወንጀሎችም ሆኑ ሌሎች ጥቃቶች እንዳይፈፀሙባቸው የበከሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባል፡፡ መንግሥትም የሕፃናትን መብቶች የማስከበር እና የመጠበቅ ኃላፊነት ሚናውን መወጣት ይኖርበታል፡፡

በንቃተ ሕግ፣ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ