የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን በወንጀል ምርመራ፤ ከስና ክርክር የጋራ ጉዳዮች የመግባቢያ ስምምነት ሰኔ 19/2017 ዓ.ም ተፈራረሙ፡፡
በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ በኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀኔራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል በወንጀል ምርመራ፣ ክስና ክርክር ስራዎች ያሉ ችግሮችን በመቅረፍ ብቁ፣ በቴክኖሎጂ የተደገፈና ሀገራዊ ስታንዳርድ ያለው አገልግሎትን በጋራ ለመስጠት የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ በመፈረምና እና የጋራ ዕቅድ በማውጣት በቅንጅት መሥራት በሀገር ደረጃ ተዓማኒነት ያለው የፍትሕ ተቋማት እንዲንኖሩ የሚያደርግ መሆኑን በመግለፅ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅባቸውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ኮሚሽነሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር ሚንስትር ክብርት ወ/ሮ ሐና አርዓያሥላሴ በበኩላቸው የወንጀል ፍትሕ አሰተዳደሩን ውጤታማ ለማድረግ የፍትሕ አካላት በቅንጅት መስራታቸው አስፈላጊ እንደሆነ አንስተው፤ የተፈረመው የትብብር ስምምነት ስትራቴጂካዊ በሆኑ የጋራ ጉዳዮች ላይ በተለይም በወንጀል ምርመራ፣ ክስ እና ክርክር ስራዎች ቋሚ የቅንጅት እና የጋራ የመረጃ ስርዓትን ለመዘርጋት፣ ግልፅ የጋራ አመታዊ ዕቅድ ለማውጣትና የጋራ የክትትልና ድጋፍ ስርዓትን ለመተግበር፣ የአቅም ግንበታ ስራዎችን በጋራ ለመሥራት እንዲሁም ተናባቢ አደረጃጀት እና የአሠራር ስርዓትን ተግበራዊ ለማድረግ የሚያስችል እንደሆነ ገልፀዋል፡፡
የጋራ የስምምነት ሰነዱ ከሁለቱ ተቀማት በተወጣጡ ኃላፊዎች አማካኝነት ያለፉት አመታት የተቀማቱ የተልዕኮ አፈፃፀም ላይ በተከናወነ ጥልቅ ጥናት ላይ ተመስርቶ የተዘጋጀ እንደሆነ ተመላክቷል፡፡
ከፊርማው ሥነ-ሥርዓት ጋር ተያይዞ ተሳታፊዎች በሰንዳፋ በሚኘው የፌደራል ፖሊስ የፎረንሲክ ምርመራና የምርምር ልህቀት ማዕከል ውስጥ ያሉ ከ13 በላይ የፎረንሲክ ምርመራ የሚካሄድባቸው ላብራቶሪዎችን እና የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርስቲን የማስፋፊያ የግንባታ ስራዎችን ጉብኝተዋል፡፡
በመርሀ-ግብሩ ላይ የፍትሕ ሚኒስቴር ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች፤ የፌደራል ፓሊስ ኮሚሽን ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች፤ የክልልና የከተማ አሰተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን ከፍተኛ ኃላፊዎች፤ የክልል ፍትሕ ቢሮ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡