ነፃ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት ፍትሕ የማግኘት መብትንና እኩልነት ላይ የተመሰረተ ፍትሕን ብሎም ሌሎች መሠረታዊ መብቶችንና ነጻነቶችን ለማረጋገጥ ትልቅ ፋይዳ ያለው ሲሆን አገልግሎቱን ለሚፈልጉ የህብረተሰብ ክፍሎች ተደራሽ ለማድረግ በርካታ ጥረቶች ሲደረጉ ቆይተዋል፡፡
ጥራት ያለው እና ተደራሽ የሆነ ነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት ሥርዓት ከመዘርጋት አኳያ የሚስተዋሉ ችግሮችን በዘላቂነት ለመቅረፍ የነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት ስትራቴጂ ተዘጋጅቶና ጸድቆ ከባለፈው ዓመት ጀምሮ ስራ ላይ የዋለ ሲሆን ስትራቴጂውን ወደመሬት አውርዶ ለመተግበር የሚያስችል የተሟላ የሕግ ማዕቀፍ አስፈላጊ በመሆኑ በጥናት ላይ ተመስርቶ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ረቂቅ አዋጁን የማዘጋጀት ስራ ሲሰራ ቆይቷል።
ረቂቅ አዋጁን ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመመካከር በሚገኘው ግብዓት መሠረት ማዳበር አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የክልል ፍትሕ ቢሮ ኃላፊዎች እና የጠቅላይ ፍርድ ቤቶች ፕሬዚዳንቶች በተገኙበት መድረክ ጥቅምት 23 ቀን 2017 ዓ.ም በአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ሰመራ ከተማ በረቂቅ አዋጁ ላይ የግብዓት ማሰባሰቢያ መድረክ ተካሂዷል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የኢ.ፊ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የመንግሥት ሕግና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ በላይሁን ይርጋ ባስተላለፉት መልዕክት የመድረኩ ዓላማ ነፃ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት ስትራቴጂን ወደስራ ለማስገባት የሚያስችል ጥራት ያለው ነጻ የሕግ አገልግሎት ሕግ ለማውጣት በዘርፉ ከተሰማሩ እና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ግብዓት ለማሰባሰብ መሆኑን ገልፀው ሕጉ የዜጎችን የማሕበራዊ ፍትሕ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ ብሎም ሌሎች መብቶች የበለጠ እንዲከበሩ ለማድረግ የሚኖረው ሚና የላቀ መሆኑን አመላክተዋል።
ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው አክለውም ነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት ረቂቅ አዋጁን በመድረኩ በተገኙት እና በቀጣይነት ከተለያዩ አካላት ጋር በሚደረጉ የምክክር መድረኮች በሚገኙ ግብዓቶች የማዳበር ሥራ የሚከናወን መሆኑን ገልፀዋል።
በመድረኩ ረቂቅ አዋጁ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የሕግ ጥናት፣ማርቀቅ እና ማጠቃለል ዳይሬክተር ጀነራል በሆኑት አቶ አዲስ ጌትነት ቀርቦ በተሳታፊዎች ውይይት የተደረገ ሲሆን በውይይቱ ረቂቅ አዋጁን ለማዳበር የሚያስችሉ ግብዓቶችን ከተሳታፊዎች በማሰባሰብ መድረኩ ተጠናቋል።