ክቡር ሚኒስትር ዲኤታዉ ይህን ያሉት የተቋም ግንባታና ሪፎርም ዘርፍ ስር ያሉ የስራ ክፍሎች የ2016 በጀት ዓመት የስራ አፈፃፀም የሱፐርቪዥን ሪፖርት እና የ2017 ዓ.ም እቅድ በቀረበበት ወቅት ተገኝተዉ ባስተላለፉት መልእክት ነዉ፡፡
የተቋም ግንባታና ሪፎርም ዘርፍ ሲቋቋም በፍትሕ ሚኒስቴር የተቋም መገንባትንና የሶስት አመቱ የፍትሕ ትራንስፎርሜሽን እቅድ በክልሎችና በፌዴራል በአጠቃላይ በአገር አቀፍ ደረጃ ያለዉን አፈፃፀም አስመልክቶ የማስተባበርና የመከታተል ዓላማዎችን አንግቦ መሆኑን የገለፁት ሚኒስትር ዲኤታዉ በዚህም የርትእ፣የፍትሕና የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የሚስያችሉ የሪፎርም ተግባራት ላይ ትኩረቱን አድርጎ ሲሰራ መቆየቱን አዉስተዋል፡፡
ሪፎርም እዉን የሚሆነዉ በቅድሚያ ሰዉ ላይ ሲሰራ መሆኑንና በዚሁም መሠረት የሰዉ ሀብቱን አቅም በመገንባት በኩል በርካታ ስራዎች መሰራቱን የገለፁት ሚኒስትር ዲኤታዉ የአሠራር ሥርዓትን በመትከልና በማሻሻል እንዲሁም የተቋሙን የቴክኖሎጅ አጠቃቀም በማሳደግ በኩል ከዘጠኝ የሚበልጡ የቴክኖሎጅ ዉጤቶችን ስራ ላይ እንዲዉሉ ማድረግ መቻሉንም አያይዘዉ ገልፀዋል፡፡
በመሆኑም በዛሬዉ ዉይይት በዘርፉ ስር ያሉ የስራ ክፍሎች በአንድ ዓመት ዉስጥ ያከናወኑትን የስራ አፈፃፀም ምን እንደሚመስልና ምን ደረጃ ላይ እንዳሉ ለማየት ሱፐርቪዥን መደረጉንና ግኝቱ ላይ ተወያይቶ በ2017 ዓ.ም እቅድ ያደገ የተሻሻለና ዉጤት ላይ መሠረት ያደረገ አድርጎ ለማቀድ እንደሚያስችላቸዉ ገልፀዉ ለዉይይቱ እዉን መሆን ድጋፍ ያደረገዉን ዩ.ኤን.ዲ.ፒን አመስግነዋል፡፡
ቀጥሎም በተቋም ግንባታ እና ሪፎርም ዘርፍ የፅ/ቤት ሀላፊ በሆኑት አቶ መዝሙር ያሬድ አማካኝነት የ2016 አፈፃፀም የሱፐርቪዥኑ ሪፖርት የቀረበ ሲሆን በዋናነት የሱፐርቪዥኑ ዓላማ የስራ ክፍሎቹ በሕግና በተቋሙ የተሰጣቸዉን ተግባርና ኃላፊነት በአግባቡ እየተወጡ መሆናቸዉን ማረጋገጥና ከግኝቶችና ከተሞክሮዎች በመነሳትም በቀጣይ የተሻለ እቅድ አቅዶ ዉጤታማ የሆነ ስራ ለመሥራት መሆኑን በዚሁ ወቅት ገልፀዋል፡፡
ዉይይቱ በዛሬዉና በነገዉ ዉሎዉ ከ2016 አፈፃፀም ከሱፐርቪዥኑ ሪፖርት በተጨማሪ ከየስራ ክፍሎቹ የ2017 በጀት ዓመት እቅድ ቀርቦ ዉይይት የሚካሄድበት ይሆናል፡፡
የስነ ምግባርና ጸረ ሙስና መከታተያ ዳይሬክቶሬት፣ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጅና መዝገብ አስተዳደር ስራ አስፈፃሚ፣ንቃተ ሕግ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት ፣ዓቃቤ ሕግ አስተዳደር ዋና ጉባኤ ፅ/ቤት፣ፍትሕ ሥርዓት ማሻሻያና ለዉጥ ስራ አመራር ዳይሬክቶሬት፣ክልል ጉዳዮች መከታተያና ድጋፍ ዳይሬክቶሬት፣የስትራቴጂ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት እንዲሁም የሴቶችና ባለብዙ ዘርፍ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት የተቋም ግንባታና የሪፎርም ዘርፍ የስራ ክፍሎች ናቸዉ፡፡