በፍልሰት ዙሪያ የሚሰሩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አገር አቀፍ ፎረም ተመሰረተ

National Forum Established for Civil Society Organizations Working on Migration Issues

በፍትሕ ሚኒስቴር የፍልሰት ትብብር ጥምረት ሴክሬታርያት ከጂ.አይ.ዜድ ቢ ኤም ኤም ጋር በመተባበር በፍልሰት ዙሪያ የሚሰሩ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አገር አቀፍ ፎረም ባለድርሻ አካላት፣ ዓለም ዓቀፍ ተቋማትና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በዛሬው እለት ምስረታው ተካሂዷል።

በምሰረታው ተገኝተው ንግግር ያደረጉት በፍትሕ ሚኒስቴር የተቋም ግንባታና ሪፎርም ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ ክቡር ኤርምያስ የማነብርሃን (ዶ/ር) ፍልሰት የልማትና የማኅበረሰብ እድገት መሳሪያ መሆኑንና መደበኛና ደህንነቱ የተጠበቀ ለማድረግ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኙ ገልፀዋል።

ሆኖም በአገራችን በተጨባጭ ያለው ሁኔታ በሰው የመነገድና በህገወጥ መንገድ ሰውን ድንበር ማሻገር ወንጀሎች ምክንያት ዜጎች በመተላለፊያና በመዳረሻ አገራት መብታቸው፣ ደህንነታቸውና ክብራቸው አደጋ ላይ እየወደቀ ከፍ ሲልም የአካልና የህይወት ዋጋ እየከፈሉ ይገኛልም ብለዋል።

አክለውም ከድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች በተጨማሪ በሀገር ውስጥ በሚፈፀም በሰው የመነገድ ወንጀል ምክንያት በተለይም በሴቶች እና በሕፃናት ላይ የተለያዩ ብዝበዛዎች የሚፈፀምባቸው መሆኑን አመላክተው ይህም ተግባር ለድንበር ተሻጋሪው መደበኛ ያልሆነ የሰዎች ዝውውር መጋቢ እየሆነና መደላድል እየፈጠረ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በነዚህና በመሰል መነሻ ሁኔታዎች ወንጀሎቹን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በፌደራልና በክልሎች መካከል እንዲሁም በመንግሥት ተቋማትና መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች መካከል ቅንጅት አስፈላጊ በመሆኑ በፍልሰት ዙሪያ በሚሰሩ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን በአንድ የትብብር ጥላ የሚያሰባስብ ፎረም መመስረቱ በድርጅቶቹ ውስጥ የሚኖረውን የተግባራት ድግግሞሽንና የሀብት ብክነትን በማስቀረት በፍልሰት አስተዳደር ውስጥ ሁሉን አቀፍ የሆነውን ቅንጅታዊ አሠራርን እንደሚያጠናክር ገልፀዋል።

የጂ.አይ.ዜድ ቢ.ኤም.ኤም የኢትዬጵያ፣ኤርትራና ጅቡቲ ቀጠናዊ አስተባባሪ ሚስተር Gertjan de Gruijter በበኩላቸው በፍልሰት ዙሪያ የሚሰሩ ድርጅቶች አንድ ላይ የሚሰሩበትን እድል በማመቻቸት ለፍልሰት አስተዳደሩ አጋዥ ማድረግ የሚኖረው ጠቀሜታ ሰፊ መሆኑን ጠቁመው ለአብነትም ለፍልሰት ፓሊሲው፣ጥናትና ምርምር ለማድረግ፣ለፓሊሲ አውጭዎች ብሎም ለሌሎች ጉዳዮች የሚኖረው ጠቀሜታ የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።

በፍልስት አስተዳደር ውስጥ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ሚና ምን እንደሆነ ያብራሩት በፍትሕ ሚኒስቴር የፍልሰት ትብብር ጥምረት ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ አብርሃም አያሌው ድርጅቶቹ በተለይም የአቅም ግንባታና ግንዛቤ ፈጠራ በማድረግ መደበኛ ፍልሰት እንዲጠናከር በማድረግ፣ የተጎጅዎችና የተጋላጭ ማኅበረሰብ ጥበቃ አገልግሎት አሰጣጥ እንዲጠናከር ማድረግ፣ዜጎችን ማዳን በተለይ በመተላለፊያና መዳረሻ አገራት ላይ በሚስተዋሉ ችግሮች ላይ መሥራት፣ ፓሊሲ እንዲጠናከር ግፊት በማድረግና በሌሎች ተግባራት ላይ የሚኖራቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልፀዋል።

በመድረኩ በፍልሰት ዙሪያ የሚሰሩ ብሔራዊ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ፎረም ለመመስረት የተዘጋጀው የመግባቢያ ሰነድ ይዘት የቀረበ ሲሆን፣ በውስጡ የትብብር መስኮች፣የጋራ ተግባራት፣የመረጃ ልውውጥ፣ቅንጅታዊ አሠራር፣ክትትልና ግምገማ የሚሉና ሌሎች በጥቅሉ 11 አንቀፆች ተካተውበታል።

በመጨረሻም 27 ድርጅቶች በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመውና የፎረሙ ሰብሳቢና ምክትል ሰብሳቢ ምርጫ ተካሂዶ መርሃግብሩ ተጠናቋል።

Tagged Under: Civil Society Organizations Collaboration Migration
የቅርብ ጊዜ ዜናዎች