ስምምነቱን የፍትሕ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አለምአንተ አግደው እና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ሁሪያ አሊ ተፈራርመዋል።
ስምምነቱ የፍትሕ ሚንስቴር የሚሰጣቸው አገልግሎቶች ኦንላይን እንዲሰጡ በማድረግ ጥራት ያለው፣ ፈጣን፣ ቀልጣፋና ወቅታዊ የሆነ የመረጃ ፍሰት እንዲኖር ያልተቋረጠ ድጋፍ ማድረግን ያቀፈ ነው።
የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ትራንስፎርሜሽን እንዲሁም አግባብ ባለው ስርዓት የዳታ ማዕከል አማካኝነት የሚሰጡ አገልገሎቶች እንዲኖሩ ማድረግ የስምምነቱ አካል ሲሆኑ ኦንላይን የሚሰጡ አገልግሎቶች ሳይቆራረጡ እንዲሰጡ ድጋፍ ማድረግም በስምምነቱ መሠረት በትኩረት የሚከናወኑ ተግባራት መሆናቸው ተጠቅሷል፡፡
በፍትሕ ሚኒስቴር በኩል ስምምነቱን የፈረሙት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አለምአንተ አግደው ከፊርማ ስነ ስርዓቱ በኋላ ባደረጉት ንግግር የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የፍትሕ ስርዓቱን ለማዘመን እያደረገ ላለው የቴክኖሎጂ ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበው በቀጣይ ተቋማችን በሕግ የተሰጡትን ሥልጣን ኃላፊነቶች በሚገባ ለመወጣት ወቅቱ የሚጠይቀውን የቴክኖሎጂ ግብዓት በማሟላት ከቀድሞ የተሻለ አገልግሎት መስጠት እንዲችል የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የተለመደ ድጋፉን እንደሚያደርግ እተማመናለው ብለዋል፡፡
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ሁሪያ አሊ በበኩላቸው የመንግሥት አገልግሎቶችን ኦንላይን ማድረግ ዜጎች ግልፅ፣ ቀልጣፋ እና ተጠያቂነትን የሚያረጋግጥ አገልግሎት እንዲያገኙ ያስችላል ካሉ በኋላ የፍትሕ ሚኒስቴር አገልግሎቱን ለማዘመን እያደረገ ያለውን ጥረት አድንቀው በቀጣይ በቴክኖሎጂ መደገፍ ያለባቸውን አገልግሎቶች ከማሟት አንጻር ሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸው ከተቋሙ ጎን እንደሚቆም አረጋግጠዋል፡፡