የፍትሕ ሚኒስቴር ከሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በጋራ በመሆን በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ አማካኝነት ያስለሙትን፤ በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን ፤የወጣት ጥፋተኞች መረጃና የወሲባዊ ጥቃት አድራሾች መረጃ መመዝገቢያ ስርዓት ማስጀመሪያ መርሀ-ግብር ታህሳስ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ተካሂዱዋል፡፡
ፍትሕ ሚኒስቴር የላቀ፤ፈጣን፤ ቀልጣፋ፤ ተደራሽ፤ ውጤታማና አካታች እንዲሁም ተገልጋይ ተኮር የፍትሕ አገልግሎት ለመስጠት የተለያዩ ሥራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡ ከነዚህ ሥራዎች ውስጥ አንዱ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ለህብረተሰቡ ተደራሽ የሆነ አገልግሎት መስጠት ፤የወንጀል መረጃን በአግባቡ መያዝ ለዚህ የሚያስፈልጉ ስርዓቶችን መገንባት እንደሚያስፈልግ በማመን ባለፉት ሶስት አመታት ተቋሙ ውስጥ የሚሰሩ ሥራዎችን እና አገልገሎቶችን በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂን ሰርዓቶች ዲጂታላይዝድ የማድረግ ተግባራትን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሲያከናውን መቆየቱ ተገልጿል፡፡
ለአብነትም የጥብቅ ፍቃድ አገልገሎትን ሙሉ ለሙሉ ዲጂታይዝ ማድረግ፣ ከህግ ማርቀቅ እና ፍትሐብሄር ጉዳዮችን የተመለከተ አገልገሎት ጥያቄዎችን ፤ ከዐቃብያነ ሕግ መረጃ አስተዳደርና ምዘና ሰርዓት፤ ከዕውቀት አስተዳደርና ሌሎች አግልገሎት ጋር በተያያዘ የለሙ ሲስተሞች ተግባር ላይ እንደዋሉ ተደርጓል፡፡
በዛሬው ዕለት ወደተግባር የገባው ሲስተም በአገራችን የአስገድዶ መድፈር እና በህፃናት ላይ የሚደርስ ጥቃትን አስመልክቶ ትክክለኛ አሀዛዊ መረጃ ለማግኘት ወሳኝ መሆኑ ተገለፀ ሲሆን፤ በዚህም ሲስተሙ በመረጃ እጥረት ምክንያት የፍትሕ መጓደልን ከመቅረፍ አኳያ ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ተነግሩዋል፡፡
የለማው ሲስተሙ ደጋጋሚ ወንጀል የሚፈፅሙ፣ በአመክሮ የሚፈቱና ታርመው የሚወጡ ወንጀለኞች ተመልሰው ወንጀል ቢሰሩ ደጋጋሚነታቸው የማይታወቅበት ሂደትን የሚቀርፍ ብሎም ትክከለኛና አስተማሪ የሆነ ቅጣት ከማሰጠት አኳያ ዐቃቤ ሕግም ሆነ ፖሊስ ደጋጋሚ ወንጀለኛ ነው ብሎ መረጃ ለማቅረብ የማይደፍርበት ሁኔታን ለማስቀረት አይነተኛ ሚና እንደሚጫወት ተገልጿል፡፡
በዕለቱ ሲስተሙን በማበልጸግ ሂደት የነበሩ ሁኔታዎች እንዲሁም ሲስተሙን እንዴት መጠቀም እንደሚቻል ሲስተሙን ያበለፀገው ድሬደዋ ዩኒቨርስቲ ሲስተሙን በተመለከተ ማብራርያ በባለሙያዎችን የቀረበ ሲሆን፤ በቀጣይም ለሚመለከታቸው አካላት ሲስተሙን አስመልክቶ ተከታታይ ስልጠናዎች እንደሚሰጡ ተገልጿል፡፡
በመድረኩ ማጠቃለያ በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ ለልደታ ቅርንጫፍ ፅ/ቤት እና ለልደታ ፖሊስ መምሪያ የበለጸገውን ሲስተም ፓይለት ለማድረግ የሚያስችላቸው ላፕቶ፣ ዴስክ ቶፕ ኮምፒውትር እና ሌሎች ቁሳቁስ ተበርክቶላቸዋል፡፡
በማስጀመሪያ በመድረኩ የፍትሕ ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ የአዲስ አበባ ፖሊስ፤ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሥራ ሃላፊዎች እንዲሁም የድሬደዋ ዩኒቨርስቲ ምክትል ፕሬዝደንት እና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች የተወከሉ ባለድረሻ አካላት ተገኝተዋል፡፡