ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የፌደራል አስተዳደር ስነ ስርዓት አዋጅ ቁጥር 1183 ላይ ከፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ዳኞች ጋር ውይይት እያካሄደ ይገኛል

Ministry Holds Discussion with Federal High Court Judges on Federal Administrative Procedure Proclamation No. 1183

በኢፌዴሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የፌደራል ህጎች ተፈፃሚነት መከታተያ ዳይሬክቶሬት የፌደራል አስተዳደር ሥነ ስርዓት አዋጅ ቁጥር 1183 ላይ ከፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ዳኞች ጋር በቢሾፍቱ ከተማ ውይይት እያካሄደ ይገኛል፡፡

የውይይት መድረኩን በንግግር የከፈቱት የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ምክትል ፕሬዝደንት የሆኑት አቶ ተህሊት ይመስል ለሐገር እድገት እና ሰላም የሕግ አውጪ፣ አስፈፃሚ እና የዳኞች ተቋም ሚና በሚዛናዊ ቁጥጥር እና ክትትል ስርዓት የሚደገፍ ከሆነ ለፍትሕ ስርዓት ግንባታ እና የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ወሳኝ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ አክለውም ይህ የአስተዳደር ሥነ ስርዓት አዋጅ መውጣቱ እንደ ትልቅ ስኬት ይቆጠራል ብለዋል፡፡

የፌደራል ህጎች ተፈፃሚነት መከታተያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሪት ሀወኒ ታደሰ በበኩላቸው ፍትሕ ሚኒስቴር ከተሰጠው ሥልጣንና ተግባር ውስጥ የፌደራል ህጎች ወጥ ሆነው መፈፀማቸውን ማረጋገጥ እና ሕግ አስፈፃሚው አካል በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ስራዎችን እየሰራ መሆኑን ማረጋገጥ እንደሚገኙበት ጠቁመው የዚህ ሥልጣን እና ኃላፊነት መተግበሪያ ደግሞ የአስተዳደር ስነ ሥርዓት አዋጁ የመንግሥትን ሥልጣን እና ኃላፊነት ገደብ አድርጎ የሚሰራበትን መንገድ የሚያስቀምጥ ሕግ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የአስተዳደር ስነ ሥርዓት ህጉ አርቃቂ አባል እና የሕግ ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር መሀሪ ረዳኢ የአስተዳደር ሕግ የመንግሥት አስፈፃሚ አካላትን አመሰራረት፣ አደረጃጀት ፣ ሥልጣን እና ተግባር እንዲሁም አስተዳደራዊ ተግባርን ሲያከናውኑ ሊከተሏቸው የሚገቡ መርሆዎችና ስነ ሥርዓቶችን የሚደነግግ ሲሆን አስተዳደራዊ እርምጃዎቹ ቁጥጥርና ክለሳ የሚከናወንበት ስርዓትን የሚያመላክት ሕግ መሆኑን የአስተዳደር ሥነ ሥርዓት ህጉን ምንነት እና ጠቀሜታን ባቀረቡበት ወቅት ገልፀዋል ፤ በተጨማሪም ዶ/ር መሐሪ የኢትዮጲያ አስተዳደር ስነ ሥርዓት ሕግ ዳሰሳን አቅርበው ውይይት ተደርጎበታል፡:

ውይይቱን ተከትሎ ዳይሬክተሯ የአስተዳደር ስነ ሥርዓት ሕግ መውጣቱን ተከትሎ አተገባበሩ ምን ይመስላል የሚለውን አቅርበው ውይይት ተካሂዷል፤ ከተሳታፊዎች ለተነሱ አስተያየት እና ጥያቄዎችም ምላሽና ማብራሪያዎችን ሰጥተዋል፡፡ የአስተዳደር ሥነ ሥርዓት ሕግ የፍርድ ቤቶች የክለሳ ስነ ሥርዓት አፈፃፀም የዳሰሳ ጥናት ግኝትም ቀርቦ ውይይት እንደሚደረግ ዳይሬክተሯ ጠቁመዋል፡፡

የውይይት መድረኩ በፍትሕ ሚኒስቴር የተዘጋጀ ሲሆን ህዳር 14 እና 15 ቀን 2016 ዓ.ም በቢሾፈቱ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል፡፡

Relevant Departments and People
Tagged Under: Accountability administrative Administrative Law Administrative Procedure bishofttu court executive branch federal Federal High Court Government Government Accountability high Implementation judicial judicial review law legal Legal Compliance Legal Implementation Legal Reform procedure proclamation Regulatory Framework review rule Rule of Law
የቅርብ ጊዜ ዜናዎች

ተመሳሳይ ዜናዎች