በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር ብሔራዊ የፍልሰት ትብብር ጥምረት ጽ/ቤት፣ ከኢ.ፌ.ዴ.ሪ ስራና ክህሎት ሚኒስቴር፣ ከአለምአቀፉ የፍልሰት ድርጅት(IOM) እና ከአለምአቀፍ የስራ ድርጅት (ILO) ጋር የፍልሰት ተጎጂዎች ጥበቃ፤ መልሶ ማቋቋምና የውጪ ሀገራት የስራ ስምሪት ዙሪያ በሚከናወኑ ተግባራት ዙሪያ የውይይት መድረክ ተካሄደ፡፡
የፍልሰት ተጎጂዎች ጥበቃ፤ መልሶ ማቋቋምና የውጪ ሀገራ የስራ ስምሪት ቡድን አባላት ከፌደራልና ከክልል፤ እንዲሁም መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች የተውጣጡ አካላት ተሳትፎ የሚያደርጉበት ሲሆን፤ ለፍልሰት ተጎጂዎች ድጋፍና ጥበቃ በማድረግ በተለይ ወደ ሀገር ሲመለሱ ካለው ቅበላ ጀምሮ ማህበረሰቡ ውስጥ ተመልሰው እስኪቀላቀሉ ድረስ ያሉ ተግባራትን የማከናወመን እንዲሁም የውጪ ሀገር የስራ ስምሪቱ ህጋዊ መንገዱን ጠብቆ በሚፈለገው ደረጃ እንዲካሄድ የማድረግና የማስተባበር ዓላማዎች ያሉት መሆኑ ተመልክቷል፡፡
የአለምቀፉ የስራ ድርጅት(ILO) ተወካይ አቶ ብርሀን ካሳ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ፍልሰት የተለያዩ አካላትን በትብብር መሥራት የሚፈልግ በመሆኑ የፍልሰት ተጎጂዎች ጥበቃ፤ መልሶ ማቋቋምና የውጪ ሀገራት የስራ ስምሪት ቡድን አባላት በጉዳዩ ላይ ለውጥ ለማምጣት፤ ማኅበራዊ ፍትሕ እንዲስፋፋ ለማድረግ እና ለሁሉም ተመላሾች እኩል የሆነ ድጋፍና እንክብካቤ እንዲሰጥ በማድረግ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ማበርከት የሚጠበቅባቸው መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
በፍትሕ ሚኒስቴር ብሔራዊ የፍልሰት ትብብር ጥምረት ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ አብረሀም አያሌው በበኩላቸው የፍልሰት ጉዳይ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተወሳሰበ በመሄዱ ይህን ጉዳይ ማስተዳደሩ በዚያው ልክ ከሁኔታዎች ጋር እየተሻሻለ መሄድ እንደሚገባው ጠቅሰው፤ በመደበኛውና ኢ-መደበኛ በሆነ መንገድ በፍልሰት የሚጓዙ ዜጎች እንዲሁም ለውጪ ስራ ስምሪት የሚሄዱት ጭምር ለተለያዩ ችግሮች እየተጋለጡ በመሆኑ እነዚህን ዜጎች በተለያየ ደረጃ በመደገፍ የልማት ኃይል እንዲሆኑ መሥራት እንደሚገባ አሳስበው፣ በዚህ ተግባር ላይ በተለያየ ደረጃ የተሳተፉ አካላትን አመስግነዋል፡፡
ለሁለት ቀናት በተካሄደው የውይይት መድረክ ላይ ከኢ.ፌ.ዴ.ሪ ስራና ክህሎት ሚኒስቴር፣ ውጪ ጉዳይ ሚንስቴር፣ ከትምህርት ሚኒስቴር፣ከትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር፣ ከህብረተሰብ ጤና ኢንስትቲውት፣ከኢሚግሬሽና ዜግነት አገልግሎት፣ ከቀይ መስቀል ማህበር፤ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ እንዲሁም ከቤኒሻንጉል፣ አማራ፣ ደቡብ፣ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ ኦሮሚያ እና ትግራይ ክልሎች የተወከሉ የፍልሰት ተጎጂዎች ጥበቃ፤ መልሶ ማቋቋምና የውጪ ሀገራት የስራ ስምሪት ቡድን አባላት የሚሳተፉበት ሲሆን፤ በመድረኩ ባለፉት 11 ወራት የተከናኑ ስራዎች እንዲሁም በቀጣይነት በሚኖሩ ተግባራት ዙሪ አቅጣጫ ተስቷል፡፡