የተቀናጀና ሁሉን አቀፍ የመከላከልና ምላሽ አሰጣጥ ስትራቴጅን ወደ ክልሎች ለማዉረድ የሚያስችል የዉይይት መድረክ በቢሾፍቱ ከተማ የተካሄደ ሲሆን ከአፋር እና ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተዉጣጡ ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት የመጀመሪያዉ ዙር መድረክ ነዉ፡፡
በሴቶች እና ሕፃናት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን ለመከላከልና ምላሽ ለመስጠት ብሎም የሕፃናት ፍትሕን ለማረጋገጥ የአምስት ዓመት ብሔራዊ ስትራቴጂ ተዘጋጅቶ የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸዉንና ከነዚህም ዉስጥ ለክልል ባለድርሻ አካላት የማሳወቅ ስራ መሰራቱን የገለፁት በፍትሕ ሚኒስቴር የሴቶች ሕፃናትና ባለብዙ ዘርፍ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ዳግማዊት አላምኔ ስትራቴጅዉን በየክልሉ ነባራዊ ሁኔታ ለመተግበር ታስቦ ከክልሎች ጋር የሚደረገዉ የመጀመሪያዉ ዙር ዉይይት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አክለዉም ተግባራቱ የበርካታ ባለድርሻ አካላትን ሚና የሚጠይቁ በመሆናቸዉ ከነዚህ አካላት ጋር በቅንጅት መሥራት እጅጉን አስፈላጊ መሆኑንና ይህም ያሉትን ክፍተቶች በጋራ እየለዩ መፍትሄ ለማምጣት እንደሚያግዝ ገልፀዉ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸዉን ሚና መወጣት እንዳለባቸዉ ጠቁመዋል፡፡
ከዚህ ቀደም ቅንጅታዊ አሠራርን ለመዘርጋት ከተሰሩ ዋና ዋና ስራዎች ዉስጥም ስትራቴጂ ቀርፆ ማፀደቅ፣የፍትሕ እንክብካቤ ማእከላት መመስረት እና ማስፋፋት፣የሕፃናት ተስማሚ ችሎቶች እና ቅንጅቱን ወደ ክልል ለማዉረድ እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን ለአብነት አንስተዋል፡፡
በመሆኑም ሁሉም ክልሎችና ባለድርሻ አካላት የተቀናጀና ሁሉን አቀፍ የመከላከልና ምላሽ አሰጣጥ ስትራቴጂን አስፈላጊነት ተገንዝበው እንደ ክልሉ ነባራዊ ሁኔታ ማዉረድ እንደሚገባ የተገለፀ ሲሆን ስትራቴጂዉን ሲያዘጋጅም የወንጀል ባህሪዉ የተለያዩ መልኮች ያሉት መሆኑ፣ተጎጅዎች ዘርፈ ብዙ መብቶችና ፍላጎት ያላቸዉ መሆኑ፣ከሁለተኛ ጥቃት ለመጠበቅ፣ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተናበዉ ለመሥራትና ችግሮቹን ለመፍታት የሚሉና ሌሎች የስትራቴጂዉን አመክንዮዎች ሊገነዘብ እንደሚገባ ተመላክቷል።
ቀጥሎም በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶችን ለመከላከልና ምላሽ ለመስጠት የተቀረፀዉን የአምስት ዓመት ብሔራዊ ስትራቴጂ የቀረበ ሲሆን ክልሎች ከዚሁ በመነሳት የራሳቸዉን ተሞክሮ የዳሰሰ የቅንጅታዊ አሠራር እቅድ የሚያቅዱ ይሆናል፤ ከሌሎች ክልሎች ጋር መሰል መድረኮች በቀጣይነት እንደሚካሄዱ ተገልጿል፡፡