በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት እና በፕላንና ልማት ሚኒስቴር አስተባባሪነት የተመራው የፌደራል የሱፐርቪዥን ቡድን የፍትሕ ሚኒስቴርን የሪፎርም እንቅስቃሴዎች እንዲሁም የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ተቋምን አገልግሎት አሰጣጥ ቃኝቷል፡፡
በሱፐርቪዥኑም ወቅት በተቋም ግንባታ እና ሪፎርም ዘርፍ የሚኒስትር ዲኤታ አማካሪ በሆኑት በአቶ አማኑኤል ታደሰ አማካኝነት በተለይም በተቋሙ የፍትሕ ዘርፍ የሪፎርም እንቅስቃሴዎች ያሉበት ቁመና ምን ይመስላል የሚለውን ለማመላከት ለቡድኑ ሪፖርት ቀርቦ ሰፋ ያለ ማብራሪያ የተሰጠበት ሲሆን በኢትዮጵያ የሽግግር ፍትሕ አስፈላጊነት ላይ እንዲሁም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በሽግግር ፍትሕ ዙሪያ ያከናወናቸው እና ሊያከናውን ያቀዳቸውን ቀጣይ ተግባራት በሕግ ማርቀቅ ማጠናከርና ማጠቃለል ምክትል ዳይሬክተር ጀኔራል ወ/ሮ ቃልኪዳን ደረጀ አማካኝነት ለቡድኑ በዝርዝር ቀርቧል፡፡ በተልይም ከሪፎርሙ እንቅስቃሴዎች ትግበራ ጋር ተያይዞ ጠንካራ ጎኖች፣ያጋጠሙ ተግዳሮቶች እና የተወሰዱ የመፈትሄ እርምጃዎችም በዝርዝር ተነስተው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡
በተያያዘም የፍትሕ ሚኒስቴር ወደ ትግበራ የገባባቸው ስራዎች በተለይም የአገልግሎት አሰጣጥ ስርአቱን ለማዘመንና ቀልጣፋ ለማድረግ የለሙ ቴክኖሎጂዎችን የሱፐርቪዥን ቡድኑ ጎብኝቷል፡፡
ቀጥሎም የሱፐርቪዥን ቡድኑ የስነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ተቋም አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ የቀረበለትን ሪፖርት የተመለከተ ሲሆን በሪፖርቱም ላይ በተለይም የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ልማት አሰጣጥ፣ የተቋሙ የ10ዓመት ስትራቴጂካዊ የትኩረት መስኮችና አቅጣጫዎች፣ እንዲሁም የተቋሙ የአገልግሎት አሰጣጥ ፍሰትን በተመለከተ አበይት ጉዳዩች የተዳሰሱ ሲሆን በተለይም ተቋሙ ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተያይዞ እያጋጠሙት ያሉ ችግሮችን በግልፅ አመላክቷል፡፡ የቀረበውንም ሪፖርት መሠረት በማድረግ የሱፐርቪዥን ቡድኑ በተቋሙ ዋናው መስሪያ ቤትና በስሩ ካሉ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች መካከል አንዱን ጎብኝቷል፡፡