የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 42ኛ መደበኛ ስብሰባውን ሲያካሂድ ተገኝተው ከምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች የተለያዩ ማብራሪያዎችን የሰጡት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) መንግሥት የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በሌላ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የፕሪቶሪያ ስምምንት ለትግራይ ሕዝብ እፎይታ ማምጣቱንና ሰላም እንዲፈጠር ማድረግ መቻሉን ጠቅሰው የተፈናቀሉ ሰዎችን ወደቀያቸው የመመለስ ስራ በመሰራት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግሥት የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ለአፍራሽ ሀይሎች ምቹ እድልን የሚፈጥረውን ድህነት እና ኋላቀርነት ለመቅረፍ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ከዚሁ ጋር አያይዘውም ታስረው የነበሩ የቀድሞ የትግራይ ታጣቂች እንዲፈቱ የተደረገው መንግሥት ከሁሉም ነገሮች በላይ ለሰላም ትኩረት በመስጠቱ መሆኑን አስገንዝበው፤ የትግራይ የቀድሞ ታጣቂዎችን መልሶ ማቋቋምና ወደ ማህበረሰቡ እንዲቀላቀሉ ለማድረግ በትኩረት መሰራት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
አክለውም ሀገራዊ የምክክር መደረክም በርካታ መስተካከል የሚኖርባቸውን ጉዳዮች ማየት ያስቻለ መሆኑን ጠቅሰው በተለይ በምክክር መድረኩ ከህብረተሰቡ የተገኙ ሀሳቦችና ግብረ መልሶች ለሕግ ማሻሻያ የሚሆን ግብዓቶች የተገኘባቸው መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡
ሌላው በምክር ቤቱ አባላት ሙስና ተስፋፍቷል ችግሩን ለመከላከል ምን እየተሰራ እንደሆነ ማብራሪያ ቢሰጥ በሚል ለተነሳላቸው ጥያቄ በግል ደረጃ የሚፈፀም ሙስና እንጂ ተቋማዊ የሆነ የሙስና ተግባር የለም ያሉት ክቡር ጠቅላይ ሚንስትር፣ ሙስና በባህሪው የግል ውሳኔን የሚፈልግ ጉዳይ በመሆኑ ድርጊቱን በሕግና በመመሪያ ብቻ መከላከል ስለማይቻል ሙስናን መከላከል የሚያስችል የሪፎርም ስርዓት ተግባራዊ በመደረግ ላይ መሆኑን ገልፀዋል፡፡