የፍትሕ ሚኒስቴር ከሴንተር ፎር ጀስትስ ጋር በመተባበር ነፃ የሕግ ድጋፍ ረቂቅ አዋጅ የግብአት ማሰባሰቢያ የምክክር መድረክ ከሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት፣ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እና ከዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ ተሳታፊዎች በተገኙበት በአዲስ አበባ ውይይት አካሂዷል።
ነፃ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት አሰጣጥ በዘርፉ ብዙ ተዋንያን የሚሳተፉበት አገልግሎት መሆኑንና ለአብነትም መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ዩኒቨርስቲዎች፣የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ተከላካይ ጠበቆችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት መኖራቸውን የገለፁት በፍትሕ ሚኒስቴር የሕግ ጥናት ማርቀቅና ማጠቃለል ዳይሬክተር ጀነራል አቶ አዲስ ጌትነት እነዚህ ባለድርሻ አካላት የሚሰጡት አገልግሎት የተበታተነና ቅንጅት የጎደለው በመሆኑ እነዚህን ችግሮች በመቅረፍ የተናበበና ወጥነት ያለው ብሎም ተደራሽነቱን ለማስፋት አዋጁ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።
በመሆኑም ፍትሕ ሚኒስቴር በተሰጠው በአገር አቀፍ ደረጃ አገልግሎቱን የማስተባበር ኃላፊነት በመነሳት ነፃ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት ስትራቴጅን በማዘጋጀት ፀድቆ ስራ ላይ የዋለ መሆኑንና ስትራቴጅውን ለማስፈፀም ረቂቅ አዋጁ መዘጋጀቱን ዳይሬክተር ጀነራሉ አያይዘው ገልፀዋል።
ባለድርሻ አካላትም ከዚህ ቀደም አገልግሎቱን ሲሰጡ የተስተዋሉ ክፍተቶችን ያጋጠሙ ችግሮችን በጋራ ቀርፈው የበለጠ ተጠናክረው ዘርፉን የሚደግፉበት ሥርዓት መፍጠር አስፈላጊ መሆኑን ያነሱት አቶ አዲስ ተሳታፊዎች አስፈላጊውን ግብአት በመስጠት ፍሬያማ ውይይት እንዲያደርጉ በመጠቆም ድጋፍ ላደረገው ሴንተር ፎር ጀስቲስ ምስጋና አቅርበዋል።
የሴንተር ፎር ጀስቲስ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኩምሳ ጉተታ በበኩላቸው ነፃ የሕግ ድጋፍ አገልግሎትን ማገዝ ድርጅታቸው ከሚሰራባቸው ተግባራት አንደኛው የሆነውን የታራሚዎችን ሰብዓዊ መብት ጋር የሚገናኘ መሆኑን አንስተው በዚህም ከዚህ ቀደም በተበጣጠስ መንገድ ሲሰጥ የነበረውን አገልግሎት አሰጣጥ በመፍታት በአገር አቀፍ ደረጃ ወጥ የሆነ የተሳለጠና የፍትሕ ተደራሽነቱ የተረጋገጠ አገልግሎት ለመስጠት አዋጁ የሚኖረው አስተዋፅኦ የጎላ እንደሆነ ተናግረዋል።
የረቂቅ አዋጁን አጠቃላይ ይዘት ያቀረቡት በፍትሕ ሚኒስቴር የሕግ ጥናት ማርቀቅና ማጠቃለል ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ጉደታ ቀንዓ፣ ፍትሕ የማግኘት መብትን ለማረጋገጥ ለፍትሕ ተደራሽነት እንቅፋት የሆኑ ችግሮችን መቅረፍና የእኩልነት መብት ለአዋጁ መነሻ ምክንያቶች መሆናቸውን የገለፁ ሲሆን፣ ከአገልግሎት አሰጣጥ አንፃርም የተደራሽነት ችግሮችን በመቅረፍ ለሁሉም የህብረተሰብ ከፍሎች ተደራሽ ማድረግን አዋጁ በግልፅ እንደሚያስቀምጥ ተናግረዋል።
ለረቂቅ አዋጁ ግብአት የሚሆኑ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ከውይይቱ ተሳታፊዎች የተነሱ ሲሆን ከመድረኩ አወያዮች ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል።