የፌደራል ተቋማት የፋይናንስና የግዢ ሕጎች የአፈፃፀም ጥሰት መነሻዎችን አስመልክቶ በተደረገ የዳሰሳ ጥናት ላይ ውይይት ተካሄደ

Discussion Held on a Survey of the Causes of Violations of Federal Financial and Procurement Laws in Federal Institutions

የፍትሕ ሚኒስቴር የፌዴራል ዋና ኦዲተር ሪፖርትን መነሻ በማድረግ የፌደራል የፋይናንስ የግዥ ሕጎች የአፈፃፀም ጥሰት መንስኤውና ሊወሰድ ስለሚገባው የመፍትሄ ሀሳብ በሚል በ87 የፌዴራል ተቋማት ላይ የተደረጉ የፋይናንስ ኦዲት ሪፖርቶች ዳሰሳ መሠረት ተደርጎ ያካሄደውን ጥናት በዛሬው እለት በአዲስ አበባ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት አቅርቦ ውይይት ተካሂዶበታል።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጭ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ የሺእመቤት ደምሴ(ዶ/ር) ሀገር እንደ ሀገር የሚገነባዉ በተቋማት መሆኑንና እነዚህ ተቋማት በሕግና በሥርዓት ተመስርተዉ ስራቸዉን ማከናወን እንደሚገባቸዉ ገልጸዉ እነዚህ ተቋማት በየአመቱ የሚለቀቅላቸዉን በጀት ሲጠቀሙ ሀብትና ንብረት በአግባቡ የሚመሩበት የፋይናንስና የግዥ መመሪዎች መኖራቸዉን ተናግረዉ ነገር ግን እነዚህ የሕግ ማእቀፎች በአተገባበር ሂደት ዉስጥ በርካታ ክፍተቶችና የሕግ ጥሰቶች እንደሚስተዋሉባቸዉ በሚደረጉ ክትትሎች መረጋገጣቸዉን አመላክተዋል፡፡

በመሆኑም ለነዚህ ክፍተቶች ተጠያቂነትን ማስፈን ብቻዉን በቂ ባለመሆኑ አማራጭ የመፍትሄ ሀሳብ ለማቅረብ የፍትሕ ሚኒስቴር በነዚህ የህጋዊነት ክፍተቶች ተመስርቶ የችግሮቹን መንስኤዎች በማጥናት ለዉይይት በማቅረቡ ምስጋና አቅርበዋል።

በፍትሕ ሚኒስቴር የመንግሥት ሕግና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ ክቡር አቶ በላይሁን ይርጋ በበኩላቸዉ የመንግሥት ሀብት በተለያዩ ምክንያቶች ጥቅም ላይ ሲውል ክፍተቶች እነደሚስተዋሉ እና እነዚህ ክፍተቶች በአንዳንድ ተቋማት ላይ በተደጋጋሚ የሚስተዋል መሆኑን ከፌደራል ኦዲት እና ከተወካዬች ምክር ቤት በሚቀርቡ ሪፓርቶች የተመላከቱ መሆኑን ገልጸዋል ።

እነዚህ የኦዲት ግኝቶች ከተከሰቱ በኋላ ከሚከተሉ ተጠያቂነቶች ቀድሞ የችግሮቹን ምንጭ በማጥናት መፍትሄ ማስቀመጥ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዉ የፍትሕ ሚኒስቴር በአዋጅ በተሰጠዉ ሥልጣን መሠረት ሀገራዊ ፋይዳቸዉ እና ህዝባዊ ጠቀሜታቸዉ ከፍተኛ የሆኑ ህጎች ላይ የአፈፃፀም ክትትል እና ጥናት እንደሚያደርግ ጠቁመዉ በተያዘዉ በጀት ዓመትም የፌዴራል ኦዲተር ሪፖርትን መነሻ በማድረግ በሁለት አዋጆች ማለትም የፋይናንስ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 648/2001 እና የግዥ ንብረት አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 649/2001 በተሻሻለዉ 1333/2016 ተመስርቶ በተመረጡ ተቋማት መረጃዎችን በመሰብሰብ የአፈፃፀም ክትትል ማድረግ መቻሉንና በዚህም ለህጎቹ አተገባበር ተግዳሮት የሆኑ ቁልፍ ጉዳየችን በመለየት የህጎቹን አፈፃፀም ለማሳደግ የሚያስችሉ ምክረ ሃሳቦች መመላከታቸዉ ገልፀዋል፡፡

የዳሰሳ ጥናቱ በዋናነት በሚታዩ ተደጋጋሚ ክፍተቶች መንስኤዉን መለየትና ለችግሮቹ የመፍትሄ ሀሳብ መስጠትን ዓላማ ያደረገ ሲሆን የመንግሥት ተቋማትም ይህንኑ ምክረ-ሀሳብ በመጠቀም የፋይናንስ አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያስችላቸዉ መሆኑ በጥናቱ ተመላክቷል።

በዋናነት ጥናቱ ሕግን ያልተከተሉ ወይም የክፍያ መስፈርቶች ሳይሟሉ የሚፈጸም ክፍያ፣ ውዝፍ ተሰብሳቢ ሂሳብ በተመለከተ፣ተከፋይ ሂሳቦች የተመለከቱና የግዥ ሂደትን አለመከተል የሚሉ አራት መሠረታዊ ግኝቶችን ያመላከተ ሲሆን ለነዚህ ጥሰቶች መንስኤዎቹም የቁጥጥር ሥርዓት ጠንካራ አለመሆን፣ የዉስጥ ኦዲት ጠንካራ ነፃና ገለልተኛ አለመሆን፣ የኦዲት ምክረ ሀሳብ አፈፃፀም ዝቅተኛ መሆንና የተጠናከረ የተጠያቂነት ሥርዓት ተግባራዊ አለማድረግ፣ የዕቅድ ችግር እና የሕግ ክፍተት መሆናቸዉንና ለነዚህም መፍትሄ ይሆናሉ የተባሉ ምክረ ሀሳቦች ተካተዉበታል።

በዉይይቱ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጭ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢን እና አባላትን ጨምሮ የተቀማት ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ የፌዴራል ምክትል ዋና ኦዲተር፣ የግዥ ዋና ዳይሬክተር እና ሌሎች ከፍተኛ ስራ ሀላፊዎች ተሳታፊ ሆነዋል።

Tagged Under: accountability mechanisms • audit • audit report • budget management • committee • compliance • federal • Federal Government • financial • Financial Management • financial mismanagement • Financial Regulations • Government • government spending • internal audit • Laws • legal framework • management • office • parliamentary • parliamentary committee • policy recommendations • procurement • public procurement • report • violations
የቅርብ ጊዜ ዜናዎች