ክቡር የመንግሥት ሕግና ፍትሕ አገልግሎት ሚ/ር ዴኤታ አቶ በላይሁን ይርጋ ከሕግ ባለሙያዎች ለሰብዓዊ መብት ሥራ አስፈጻሚ እና የቦርድ አባላት ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡ በውይይቱ ወቅት የደርጅቱ ፕረዚዳንት የሆኑት አቶ አመሓ መኮንን በሰብዓዊ መብቶች ዙሪያ እየሰሩ ያሉትን ሥራዎች እና ከፍትሕ ሚኒስቴር ጋር በትብብር ለመሥራት ድርጅቱ ያለውን ፍላጎት እና በትብብር ሊሰሩ የሚችሉ ጉዳዮች አንስተዋል፡፡ አቶ አምሓ ሞኮንን ትኩረት ሰጥተው ካነሷቸው ጉዳዮች ውስጥ ለሕዝብ ጥቅም የሚደረግ የክርክርን በተመለከተ፣ የሕግ ድጋፍ አገልግሎትን እና የሰብዓዊ መብቶች አጠባበቅ ይገኙበታል። ከዚህም በተጨማሪ በሽግግር ፍትሕ ሂደት ላይ አስተዋጾ ማበርከት በሚችሉበት እና በሚረቀቁ ሕጎች ላይ ተሳትፎ ማድረግ በሚችሉበት ሁኔታዎች ላይ ሐሳባቸውን ገልጸዋል፡፡
የመንግሥት ሕግና ፍትሕ አገልግሎት ሚኒስቴር ዴኤታ የሆኑት አቶ በላይሁን ይርጋ ፕረዝዳንቱ ላነሷቸው ጉዳዮች አመስግነው ፍትሕ ሚኒስቴር በነዚሁ ጉዳዮች ላይ በርካታ ሥራዎችን እየሰራ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ በተነሱት ጉዳዮች ሊኖር የሚችለውን አተያይ ሲገልጹ ለሕዝብ ጥቅም የሚደረግ ክርክርን ለፍትሕ ሥርዓቱ አስተዋዕኦ በሚያበረክትበት አግባብ መመራት እንዳለበት፥ እንዲሁም የሀገርን ገዕታ እና ጥቅም አደጋ ላይ በማይጥል ሁኔታ ሊሰራ እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥተው አንስተዋል። ድርጅቱ ለሕብረተሰቡ እየሰጠ ያለውን የሕግ ድጋፍ አገልግሎት አበረታተው ህብረተሰቡ ይበልጥ የሕግ ድጋፍ በሚያገኝበት ሁኔታ ላይ ፍትሕ ሚስቴር በሚሰራቸው ሥራዎችም ጭምር ተሳታፊ መሆን እንደሚችሉም ጠቅሰዋል፡፡
በተጨማሪም ከሽግግር ፍትሕ ሂደት ጋር ተያይዞ አገር በቀል መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች መሳተፍ የሚችሉባቸው ሰፊ ስራዎች እንዳሉ ገልጸው ከፍትሕ ሚኒስቴር ጋር ተቀራርቦ በሚሰሩ ስራዎች ድርጅቱ መሳተፍ እንደሚችል አክለው ገልጸዋል፡፡ በሕግ ማርቀቅ ሂደት የተሳትፎ ጥያቄን በሚመለከት ፍትሕ ሚኒስቴር በሚያረቃቸው ሕጎች ላይ መንግስታዊ ያልሆኑ አካላት የሚሳተፉበት ሁኔታ እንዳለ እና ህጎቹ ከመጽደቃቸው በፊት አስተያየት እንዲሰጥባቸው የማደረግ ኃላፊነት ስላለበት እዚህም ላይ በጋራ የሚሰሩ በርካታ ሥራዎች እንሚኖሩ ገልጸዋል፡፡
በወይይቱ ላይ ተሳታፊ የነበሩት የወንጀል ሥነ-ሥርዓት ሕግ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ትዕግስት መሐቤ በበኩላቸው የሕግ ባለሙያዎች ለሰብዓዊ መብት ድርጅት በረቂቅ የወንጀል ሥነ-ሥርዓት ሕግ ላይ ከዚህ በፊት የሰጡትን ግብዓት በማስታወስ አመስግነው አሁንም የወንጀል ሥነ-ሥርዓት ሕጉ ከጸደቀ በኋላ ማስፈጸሚያ ሆነው የሚዘጋጁ በርካታ ረቂቅ መመሪያዎች ስላሉም እዛ ላይ መሳተፍ እንሚችሉ ገልጸዋል፡፡
የሕግ ባለሙያዎች ለሰብዓዊ መብት ድርጅት ፕረዝዳንት አቶ አመሃ መኮንን ከመንግሥት ሕግና ፍትሕ አገልጎት ሚ/ር ዴኤታ አቶ በላይሁን ይርጋ ለተሰጣቸው ምላሽ አመስግነው በተነሱ ጉዳዮች ላይ ቀጣይነት ያለው ግንኙነት ፈጥሮ መሰራት በሚቻልበት ሁኔታ ሐሳባቸውን ሰተዋል፡፡.
በመጨረሻም አቶ በላይሁን የሕግ ባለሙያዎች ለሰብዓዊ መብት ስራ አስፈጻሚ እና የቦርድ አባላት ፍትሕ ሚኒስቴር ድረስ በመምጣት ላነሷቸው ጉዳዮች አመስግነው ውይይቱ ተጠናቋል፡፡