ለወንጀል ህግ መከበር እና የወንጀል ፍትሕ ስርዓት መረጋገጥ የማህበረሰቡ ሚና ከፍተኛ መሆኑ ተገለፀ

Community Role Emphasized in Ensuring Compliance with Criminal Law and Justice System

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የንቃተ ሕግና ትምህርት ሥልጠና ዳይሬክቶሬት ከአዲስ አበባ ፍትሕ ቢሮ ጋር በመተባበር ለወንጀል ሕግ መከበር እና የወንጀል ፍትሕ ስርዓት መረጋገጥ የማህበረሰቡ ሚና እና ሀሰተኛ ሰነድን መከላከል በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች በአዲስ አበባ ደረጃ ለሁሉም ክፍለ ከተማ ለሚገኙ የህብረተሰብ ተወካዮች ክፍለ ከተማ አቀፍ ደረጃ ሥልጠና በዛሬው ዕለት በዋናው መስሪያ ቤት መስጠት ጀምሯል፡፡

በዚህ ከተማ አቀፍ የሥልጠና ማስጀመሪያ መድረክ በመገኘት የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት በፍትሕ ሚኒስቴር የተቋም ግንባታና ሪፎርም ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ ክቡር ኤርሚያስ የማነብርሀን (ዶ/ር) እንዳሉት የወንጀል መከላከል ስራ ውጤታማ ሆኖ እንዲተገበር እያንዳንዱ ሰው የራሱ ሚና እንዳለው አንስተው፣ ወንጀል የህብረተሰቡን ጥቅም ይጎዳል፣ፀጥታን ያደፈርሳል ፣ሰላምን ያናጋል ፣ የሀገርን ኢኮኖሚ ያቃውሳል እንዲሁም የዜጎችን በሰላም ወጥቶ የመግባት መብትን ይጥሳል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

አክለውም ፍትሕ ሚኒስቴር የወንጀል መከላከል ሚናውን ለመወጣት የተቋሙን የማኅበራዊ ትስስር ገፆችን በመጠቀም የንቃተ ሕግ ትምህርታዊ ፅሁፎችን በማጋራት እንዲሁም የተለያዩ የሥልጠና መድረኮችን በማዘጋጀት የገፅ ለገፅ የንቃተ ሕግ ሥልጠና ሲሰጥ መቆየቱን ጠቁመው ዛሬ ዕለት መሰጠት የተጀመረው የሥልጠና መርሃ ግብር በቀጣይ በአስራ አንዱም ክፍል ከተሞች ለሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎች በአራት ማዕከላት ተለይቶ ሥልጠና የሚሰጥ መሆኑን ገልፀዋል፡:

የአዲስ አበባ ፍትሕ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ክቡር አቶ ተስፋዬ ደጀኔ በበኩላቸው የሥልጠናው ዓላማ የሥልጠናው ተሳታፊዎች የወንጀል ሕግ ምንነት ፣ የወንጀል ሕግ ሊስከትል የሚችለው ጉዳትንና ጉዳቱን አውቆ ለመከላከል የህብረተሰቡ ፣ ተቋማት እና የሚዲያ ሚና ምን እንደሆነ በስልጠው የሚዳሰስ መሆኑን አውስተዋል፡፡

ወንጀል እንደወንጀል የተደነገገው ለህብረተሰቡ መልካም ጥቅም እንዲያስገኝ ነው ያሉት ምክትል ኃላፊው ፤ወንጀል በህብረተሰቡ ዘንድ ያልተረጋጋ ኑሮ እንዲከሰት ፣ያልተመጣጠነ ኢኮኖሚ ስርኣት እንዲሰፍን እና በሀገረ መንግሥት ላይ የመፍረስ አደጋ የሚደቅን በመሆኑ መከላከል እንደሚስፈልግ ገልጸዋል፡፡

ምክትል ኃላፊው አያይዘውም እንዳሉት የወንጀል ምንነትን ተረድተን ፣ወንጀል ሊያስከትል የሚችለውን ጉዳት አውቀንና ተረድተን መዲናችን የተረጋጋችና ከወንጀል የፀዳች ለማድረግ ሚናችንን መወጣት አለብን ብለዋል፤እንዲሁም ሥልጠናውን በንቃት በመከታተል የምታገኙትን ዕውቀት ለህብረተሰብ በአግባባ እንድታስተላልፉ ሲሉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ሥልጠናው በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የንቃተ ሕግ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት ዓቃቤ ሕግ እየተሰጠ የሚገኝ ሲሆን በቀጣይ በተመረጡ አራት ማዕከላት መሰጠት የሚቀጥል ይሆናል፡፡

Tagged Under: Crime Prevention • Justice System
የቅርብ ጊዜ ዜናዎች