በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የወንጀል ፍትሕ ስርዓቱን ለማሻሻል እና ለማጎልበት ከአውሮፓ ህብረት በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ለሚተገብረው ፕሮጀክት በሴቶችና ባለብዙዘርፍ ዳይሬክቶሬት አስተባባሪነት በኦሮሚያ ክልል ከዞንና ከወረዳ ለተወጣጡ የአንድ ማዕከል ባለሙያዎች የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠና በአዳማ ከተማ ተሰጥቷል።
በሥልጠና መድረኩ ላይ ተገኝተው መድረኩን በንግግር የከፈቱት በፍትሕ ሚኒስቴር የሴቶችና ባለብዙ ዘርፍ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ዳግማዊት አላምኔ የፍትሕ ሚኒስቴር የሴቶችና ሕፃናት ወንጀል ምርመራን አስመልክቶ ዘርፈ ብዙ ስራዎች እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው ከግንዛቤ ማሳደግ እና ወንጀል መከላከል ባለፈ የአገልግሎቱን ተደራሽነት ለማሳደግ የማዕከላቱ ቁጥር እንዲጨምር የተለያዩ ርብርቦች መኖራቸውን አውስተዋል፡፡ አያይዘውም ማዕከላቱ ደረጃቸውን ጠብቀው አገልግሎት እንዲሰጡ የሚመደቡ ባለሙያዎች በቂ የሆነ እውቀትና ክህሎት እንዲኖራቸው የተለያዩ ሥልጠናዎች እየተሰጡ መሆኑንና ከዚህም ጋር ተያይዞ ከብዙ ተቋማት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ስለመሆኑ ዳይሬክተሯ ገልፀዋል፡፡
ከዚህ በፊት የአንድ ማዕከል አገልግሎት ላይ ለሚሰሩ ባለሙያዎች ሥልጠና የተሰጠ መሆኑን ያነሱት ዳይሬክተሯ የአሁኑን ሥልጠና በፊት ከተሰጡት ሥልጠናዎች ለየት የሚያደርገው በተመረጡ የአንድ ማእከል አገልግሎት መስጫ ማዕከላት በመሄድ፣ የሥልጠና ፍላጎት ዳሰሳ ጥናት በማድረግ እና በጥናቱ ውጤቶች መሠረት የተለዩ ክፍተቶችን ለመሙላት የተዘጋጀ ሥልጠና ማቴሪያል መሆኑን ጠቅሰዋል።
ሥልጠናው በሌሎች ክልሎች በቀጣይ እንደሚሰጥ የጠቆሙት ወ/ሮ ዳግማዊት በዚህ ሥልጠና መድረክ ተሳታፊዎች የሚያነሱዋቸው ጉዳዮች የተዘጋጀውን የሥልጠና ማቴሪያል በይበልጥ ለማዳበር እና ለማጠቃለል እንደሚረዳ በመጥቀስ ለዚህም የሥልጠናው ተሳታፊዎች የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ በአፅንዖት ተናግረዋል፡፡