በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ጉዳዮች መከታተያ ዳይሬክቶሬት የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያውን የሩብ ዓመት እቅድ አፈፃፀም ሪፖርትን ሀዋሳ እና ድሬዳዋን ጨምሮ ከሁሉም ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊዎችና ቡድን መሪዎች ጋር ግምገማ አካሄዷል፡፡
በፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ጉዳዮች መከታተያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ጌቱ ታደሰ የቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሶስት ወራት እቅድ አፈፃፀም ሪፖርትን ሲያቀርቡ እንደገለጹት ምርመራቸው ተጠናቆ በቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች መወሰን ካለባቸው 15,314 የምርመራ መዝገዛግብት ውስጥ 97% በሚሆኑት ላይ ውሳኔ ለመስጠት ታቅዶ በ14,806 (96.7%) መዝገቦች ላይ በዐቃቤ ሕግ ውሳኔ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
ዳይሬክተሩ አያይዘውም በሩብ ዓመት ሪፖርታቸው ላይ በቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች በሁሉም የወንጀል ክርክር መዛግብት የመርታት ምጣኔን አስመልክቶ በተከሳሽ 95%፣ በመዝገብ 97% ለማድረስ ታቅዶ በክርክር ላይ ከነበሩ 17,443 መዛግብት እና 21,498 ተከሳሾች ውስጥ በፍርድ ቤት በ2,452 መዛግብት እና በ3,623 ተከሳሾች ላይ ውሳኔ ተሰጥቷል፤ በ2,386 መዛግብት እና በ3,536 ተከሳሾች ላይ የጥፋተኝነት፣ በ66 መዛግብት እና በ87 ተከሳሾች ላይ ደግሞ ነፃ በማለት ፍርድ ውሳኔ ሰጥቷል ያሉ ሲሆን አፈፃፀሙ በመዝገብ 97.31%፣ በተከሳሽ 97.6%፣ በአማካይ አፈፃፀሙ 97.5% በማድረስ ከዕቅድ በላይ መፈፀም መቻሉን ገልጸዋል፡፡
ዳይረክተሩ በፍትሐብሔር ጉዳዮች የሚሰጥ ፍርድ ማስፈፀምን በተመለከተ 1 ሚሊዮን 901 ሺ 885 ብር የሆነ በዓይነት እና በገንዘብ የሚተመን በፍርድ ቤት ክርክር ተደርጎባቸው ለፍርድ ባለመብቶች እንዲወሰን በማድረግ አብዛኞቹ ውሳኔዎች በአፈፃፀም ሂደት ላይ የሚገኙ ሲሆን ከተወሰነው ውሳኔ ውስጥም 1 ሚሊዮን 061 ሺ 885 ብር የሆነ ለፍርድ ባለመብቶች እንዲከፈል ተደርጓል ሲሉ አክለዋል፡፡
ከሰብዓዊ መብት ማስከበር ጋር በተያያዘ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ውስጥ 4,796 በማረፊያ ቤት የሚገኙ ተጠርጣሪዎችን እና ድሬዳዋ ማረሚያ ቤት የሚገኙ ታራሚዎችን ጉብኝት በማድረግ ችግሮችን በመለየት መፍትሔ እንዲሰጥ ማድረግ ተችሏል ብለዋል፡፡
በሩብ ዓመቱ ውስጥ በቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች 1,931 ተገልጋዮች አገልግሎት ጠይቀው ለ1,922 አገልግሎት ጠያቂዎች አገልግሎቱን በዜጎች ቻርተር በተቀመጠው መስፈርት መሠረት ምላሽ መስጠት ተችሏል ያሉት አቶ ጌቱ በቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች 379 አቤቱታዎች ቀርበው 371 አቤቱታዎች በተቀመጠው ስታንዳርድ መሠረት ምላሽ የተሰጠባቸው ሲሆን አፈፃፀሙን 97.9% በማድረስ ከዕቅድ በላይ መፈፀም መቻሉን በሪፖርታቸው ላይ በዝርዝር አብራርተዋል፡፡
በቀረበው የ2017 የሩብ ዓመት ሪፖርትም በበጀት ዓመቱ በቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች የእቅድ አፈፃፀም ወቅት የታዩ ጥንካሬዎችን፣ ውስንነቶችን እና እያጋጠሙ የነበሩ ችግሮችን የየቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊዎች እና ቡድን መሪዎች ያነሱ ሲሆን ለተነሱት ጥያቄዎችና አስተያየቶች ዳይሬክተሩ ተገቢውን ማብራሪያና ምላሽ በመስጠት የግምገማ መድረኩ ተጠናቋል፡፡