የዓለም ዓቀፍ የፍልሰት ስምምነት አህጉራዊ ስብሰባ በተመድ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን እና በዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት አስተባባሪነት በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ ነው።
በዚህ በአህጉራችን አፍሪካ ለሁለተኛ ጊዜ እየተካሄደ ባለው ስብሰባ የፍትሕ ሚኒስትሩ ክቡር ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ፣ የመንግሥት ሕግና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ ክቡር አቶ በላይሁን ይርጋን ጨምሮ ፣የአፍሪካ አገራት ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች፣ የተመድና የሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት መሪዎች እንዲሁም የለጋሽ ድርጅቶች ተወካዮች ብሎም የዘርፋ ከፍተኛ ባለሙያዎች እየተሳተፉበት ይገኛል፡፡
የስብሰባውን ተሳታፊዎች በየማዕረጋቸው እንኳን የሰው ልጅ መገኛ ወደሆነችው ኢትዮጵያ በሰላም መጣችሁ ሲሉ ንግግራቸውን የጀመሩት የፍትሕ ሚኒስትር ክቡር ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ2018 የጸደቀውን ዓለም አቀፍ የፍልሰት ስምምነትን (Global Compat for Migration) በመተግበር ላይ ትገኛለች ብለዋል፡፡
አያይዘውም የስምምነቱ አጀንዳዎች ከነበሩት 20 አጀንዳዎች ውስጥ 10ሩን ቅድሚያ በመስጠትና በተለያዩ የልማት ፖሊሲዎችና ዕቅዶች ውስጥ እንዲካተቱና ተፈጻሚ እንዲሆኑ በማድረግ መደበኛ ያልሆነውን ፍልሰት በመከላከልና በመቆጣጠር በሌላ በኩል መደበኛ ፍልሰትን በማስፋት ከፍልሰት የሚገኘውን ጥቅም አሟጦ በመጠቀም ረገድ የተሻሉ አፈጻጸሞችን ማስመዝገብ ችላለች ሲሉም አክለዋል፡፡
በዚሁ መሠረትም በብሔራዊ የፍልሰት ትብብር ጥምረት አማካኝነት የስምምነቱን አገር አቀፍ የአፈጻጸም ሪፖርት በ2020 ለተመድ ያቀረበች ሲሆን፤ በየጊዜው በሚደረጉ የአፈጻጸም ግምገማ መድረኮች ላይም የነቃ ተሳትፎ ስታደርግ እንደቆየች የገለጹት ክቡር ሚኒስትር ይህ ተግባሯም በምስራቅ አፍሪካ የመጀመሪዋ ሻምፒዮን ሀገር በመሆን የስምምነቱን አተገባበር ውጤታማ በማድረግ ተጠቃሽ እንድትሆን አድርጓቷል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ የፍልሰት መነሻ፣ መተላለፊያ ብሎም መዳረሻ ሀገር መሆኗን የጠቀሱት ክቡር ሚኒስትር መንግሥት ቁርጠኛ አቋም ያለው መሆኑንና ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት በክቡር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ አገር አቀፍ የትብብር ጥምረት ካውንስል በማቋቋም ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን አውስተዋል።
በመጨረሻም ይህን ዓለም ዓቀፍ የፍልሰት ስምምነት አህጉር አቀፍ ስብሰባን እንደ መልካም እድል በመጠቀም ተሳታፊዎች በጉዳዩ ላይ ያላቸውን ልምድ የሚካፈሉበት እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ገልፀው ስብሰባው የተሳካ እንዲሆን ድጋፍ ላደረጉ በተመድ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን እና በዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት (IOM) ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ስብሰባው መስከረም 29 እና 30/2017 ዓ.ም ለሁለት ቀናት የሚዘልቅ ሲሆን በፍልሰት ዙሪያ የተለያዩ ጉዳዮች ተነስተው የሚዳሰሱበት ይሆናል።