2ኛውን አገር አቀፍ የፍልሰት ምርምር ጉባኤ የተለያዩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ ተመራማሪዎችና የሚመከታቸው ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በትላንትናው እለት በይፋ ተጀምሮ በአዲስ አበባ ከተማ በሀያት ሪጀንሲ ሆቴል እየተካሄደ ይገኛል፡፡
ጉባኤውን በንግግር የከፈቱት በኢፌዲሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የመንግሥት ሕግና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ በላይሁን ይርጋ ፍልሰት ከሰው ልጆች ጋር አብሮ የሚዘልቅ ተፈጥሯዊ ኩነት መሆኑን በመጥቀስ በፍልሰት ሂደት ውስጥ የሚፈጸሙ የሰው መነገድና ሰውን በህገ-ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀሎችን በመቀነስ መደበኛ የሆነ ፍልሰትን በማበረታታት ከፍልሰት የሚገኙ ዘርፈ-ብዙ ጥቅሞችን ማሳደግ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው አክለውም ይሔንን ዓላማ ለማሳካት የተሟላና ሁሉን አቀፍ የፍልሰት አስተዳደር ፖሊሲና የሕግ ማዕቀፎ መቅረጽና መተግበር እንዲሁም ቅንጅታዊ አሠራርን መዘርጋትና ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል፡፡ ክቡር አቶ በላይሁን ይርጋ አያይዘውም ሀገራችን የምትፈልገው የተሻለ የፍልሰት አስተዳር እንዲኖር ለማስቻል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና ሌሎች የምርምር ተቋማት ለመንግሥት ፖሊሲ፣ ሕግና ስትራቴጂ ግብዓት የሚሆኑ ችግር ፈቺ ምርምሮችን እንዲያደርጉ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው በንግግር ማጠቃለያቸው ተመላሾችንና ተጎጂዎችን መጠበቅና መልሶ ማቋቋምን ማዕከል በማድርግ የሚካሔደው ይህ ሁለተኛው አገር አቀፍ የፍልሰት ምርምር ጉባዔ ዓላማ የተለያዩ ምርምሮች ቀርበው ውይይት የሚደረግበት እና በቀጣይ በፍልሰት ዙሪያ በአገራችን የተካሄዱ ምርምሮችን በማሰባሰብ ለፖሊሲና ውሳኔ ግብዓት እንዲሆኑ ለማስቻል እንዲሁም ጥናት የሚፈልጉ የፍልሰት ጉዳዮችን በመለየት ለማጥናት በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ለመምከር እንደሆነ አንስተዋል፡፡
በጉባኤው በፍትሕ ሚኒስቴር የብሔራዊ የፍልሰት ትብብር ጥምረት ፅህፈት ቤት ተወካይ ኃላፊ አቶ እያሱ ቀለሜና ከሌሎች የመንግሰት ተቋማት በመጡ ተወካዮች እንዲሁም ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በመጡ በጉዳዩ ላይ ጥናት ባደረጉ ተመራማሪዎችና ምሁራን በኩል ጽሁፎች ቀርበው ውይይት እየተደረገባቸው ይገኛል፡፡
የምርምር ጉባኤው በዛሬው እለትም የቀጠለ ሲሆን ጉባኤው የኢፌዲሪ ፍትሕ ሚኒስቴርና ትምህርት ሚኒስቴር ከጀርመን ተራድኦ ድርጅት (ጂ አይ ዜድ) ቢ ኤም ኤም ፕሮግራም እና ሴቭ ዘ ቺልደረን በተገኘ የፋይናንስ ድጋፍ የተዘጋጀ ነው፡፡