የፍትሕ ሚኒስቴር የ5 ዓመት ስትራቴጂ

ጥቅምት፥ 2018 ዓ.ም

Annual Fiscal Plans & Reports

የፍትሕ ሚኒስቴር የአምስት ዓመት ስትራቴጂያዊ ዕቅድ ከ2018 ዓ.ም. እስከ 2022 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ተቋሙ ዓላማውንና ተልዕኮውን እንዲያሳካ ስትራቴጂያዊ አቅጣጫዎችንና ዋና ግቦችን ያስቀምጣል፡፡ የስትራቴጂክ ዕቅዱ ፍትሕ ሚኒስቴር የሕግ የበላይነት ያስጠበቀ፣ ሰብዓዊ ክብር ያረጋገጠና በሕዝብ ተዓማኒ የሆነ ተቋም ለመገንባት የያዘውን ርዕይ ለማሳካት አቅጣጫ አመላካች ፍኖተ ካርታ ሆኖ የሚያገለግል ሲሆን፤ የተቋሙን የትኩረት አድማስ በመለየት ከዕለት ተዕለት ጉዳዮች ባለፈ ዋና የሚባሉ ምሰሶዎች ላይ አተኩሮ እንዲሰራ የሚያግዝ፣ የተቋሙ አመራርና ባለሙያ ለተቋሙ ርዕይና ተልዕኮ መሳካት በተባባረ ክንድ ርብርብ እንዲያደርጉ የሚያስችል ቃል ኪዳን ነው፡፡

የስትራቴጂያዊ ዕቅዱ ዝግጅት ቀድሞ ከነበሩ ዕቅዶች በተሻለ አሳታፊና አካታች የነበረ ሲሆን፣ ከቁልፍ ባለድርሻ አካላት፣ ከፍትሕ ሚኒስቴር ባለሙያዎችና ተገልጋዮች ግብዓት በመሰብሰብና ተደጋጋሚ ውይይቶች በማድረግ የዳበረ ነው። ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ተግባርና ኃላፊነት የሚሰጡ ሕጎች ዳሰሳ፣ በተለያዩ ጊዜ ተቋሙን በተመለከተ የተጠኑ ጥናቶች ለዕቅዱ ዝግጅት ግብዓት ሆነዋል። የተለያዩ ሀገራዊ፣ አህጉራዊ እና ዓለም-አቀፋዊ እቅዶች፣ ሪፖርቶች፣ የሕግና ፖሊሲ ሰነዶች፣ የተቋሙ የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርቶችና ሌሎች ሰነዶች ተዳሰዋል።

የፍትሕ ሥርዓቱ በርካታ ስትራቴጂያዊ ተግዳሮቶች ያሉበት ሲሆን፤ የሕግ ሥርዓቱ ውስብስብነትና ግልፅነት እጥረት፣ የሙያዊ ሥነ-ምግባርና ተጠያቂነት ማነስ፣ የፍትሕ አገልግሎት ተደራሽነት ውስንነት፣ የሕግ ግንዛቤ ደካማነት፣ የሕዝብ፣ የሲቪል ማኅበረሰብ እና የግሉ ዘርፍ በፍትሕ ሥርዓቱ ያለው ተሳትፎ ዝቅተኛ መሆን፣ የሕግ የበላይነት አፈጻጸም ዝቅተኛነት፣ የሙስና መኖርና ተጠያቂነት ማነስ፣ የወንጀል መከላከል አፈጻጸም ደካማ መሆን፣ የራስ ተነሳሽነት ምርመራ አለመኖር፣ የምርመራ አቅም ውሱንነት፣ የማረምና ማነፅ ሥራዎች ደካማነት፣ ፍትሐብሔራዊ የሕዝብና መንግሥት ጥቅም በውጤታማነት ለማስጠበቅ የሚያስችል አሠራር አለመኖር፣ በተቋማት መካከል የቅንጅት እጥረት፣ የዓለም ዓቀፍ ተሳትፎ እና ትብብር ውሱንነት፣ የአጋር፣ ባለድርሻና ተባባሪ አካላት ቅንጅትና ትብብር ዝቅተኛ መሆን፣ የመሰረተ ማኅበረሰብ ፍትሕ አተገባበር ጅምር ላይ መሆን እንዲሁም የተቋም ግንባታ ሥራዎች ውሱንነትና የቴክኖሎጂ ልማትና አጠቃቀም ደካማ መሆን ይገኙበታል።

እነዚህን ስትራቴጂያዊ ችግሮች ለመፍታት የሕግ ሥርዓቱን ቀላልና ግልጽ ማድረግ፣ ሙያዊና ተቋማዊ ተጠያቂነትን ማጠንከር፣ የፍትሕ አገልግሎትን ማዘመንና ተደራሽ ማድረግ፣ ጥራቱ የተሻሻለ ሕግ ማውጣት፣ የማኅበረሰብ ፍትሕና ነጻ የሕግ ድጋፍን ማስፋፋት፣ አማራጭ የሙግት መፍቻ ዘዴዎችን ማጠንከር፣ የሕዝብ፣ የሲቪል ማኅበረሰብ እና የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ማሳደግ፣ የሕግ ተፈፃሚነትና ተገዢነትን ማሳደግ፣ የወንጀል አስተዳደርን ውጤታማ ማድረግ፣ የሕዝብና መንግሥት ፍትሐብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ የሚያስችል ሥርዓት መፍጠር፣ የሙስናና ብልሹ አሠራር ተጠያቂነትን ማረጋገጥ፣ የሰብዓዊ መብት ጥበቃን ማረጋገጥና ጥሰት ፈጻሚዎችን ተጠያቂ ማድረግ፣ የማረምና ማነጽ ሥራዎችን ውጤታማ ማድረግ፣ ከፌዴራልና ክልል ባለድርሻ አካላት፣ ተባባሪና አጋር አካላት ጠንካራ ቅንጅታዊ አሠራር መፍጠር፣ የዓለም ዓቀፍ ተሳትፎና ትብብርን ማሳደግ፣ የተቋም ግንባታ ሥራዎችን ማጎልበት እና የቴክኖሎጂ ልማትና አጠቃቀምን ማሳደግ ይጠበቃል። ይህ አጠቃላይ ስትራቴጂ የፍትሕ ዘርፉን ከተለመደው ያልዘመነ ሁኔታ ወደ ተደራጀና ውጤታማ አመራር ያሸጋግረዋል።

የሕግ የበላይነትና ሰብዓዊ ክብርን መሠረት ያደረገ ማኅበረሰብ ተኮር፣ ተደራሽና ተዓማኒ የፍትሕ ሥርዓት መገንባት የተቋሙ ርዕይ ሲሆን፤ ሕጎች እንዲተገበሩና ጥራት ያላቸው ሕጎች እንዲወጡ በማድረግ፤ አካታች፣ ውጤታማና ቀልጣፋ የወንጀል፣ የፍትሐብሔርና የአስተዳደር ፍትሕ ሥርዓት በመገንባት፤ የመንግሥትና ሕዝብ ጥቅም ማስጠበቅ ነው። እነዚህ ተልዕኮዎች በአገልጋይነት የመሥራት፣ በቅንነት የመፈጸም፣ ለልሕቀት የመትጋት፣ ለለውጥ የመበርታት እና በሕብረት የመፍጠር እሴቶችን ተግባራዊ በማድረግ የሚሳኩ ናቸው።

ስትራቴጂያዊ ዕቅዱ 5 ስትራቴጂያዊ አምዶች፣ 24 ግቦች፣ 101 የቅርብ ውጤቶች፣ ዋና ዋና ተግባራት፣ የአፈጻጸም አመልካቾች እና በአምስት ዓመት የተሸነሸነ ዒላማ በመያዝ የተዋቀረ ነው፡፡ የፍትሕ አገልግሎት አምድ ስምንት ግቦችን በመያዝ የተማከለ ዲጂታላይዝድ አገልግሎት አሠጣጥን፣ የመሠረተ ማኅበረሰብ ፍትሕን፣ አማራጭ የሙግት መፍቻ ሥርዓትን፣ የተጋላጭ ማኅበረሰብ አካታችነትን፣ የፍትሕ አገልግሎት ተደራሽነትን፣ የተገልጋይ እርካታን፣ እና የሕዝብና ሲቪል ማህበረሰብ ተሳትፎንና ተጠቃሚነትን ያሳድጋል። የሕግ የበላይነት አምድ ስድስት ግቦችን በማካተት የሕግ ማርቀቅና ምክር ጥራትን፣ የወንጀልና ፍትሐብሔር አስተዳደር ውጤታማነትና ቅልጥፍናን፣ የሕግ ተገዢነትና ተፈፃሚነትን፣ የሰብዓዊ መብት ጥበቃና ጥሰት ተጠያቂነትን፣ እና የመብቶች ዋስትናን ያጠናክራል። የማረምና ማነጽ አምድ የወንጀለኝነት ባሕሪ ማረምና ማነጽ ውጤታማነትን ያጠናክራል፡፡ የተቋም ግንባታ አምድ ስድስት ግቦች ያሉት ሲሆን የሰው ሀብት፣ የቴክኖሎጂ ልማትና አጠቃቀም፣ የሀብት አስተዳደር፣ የክትትልና ግምገማ ሥርዓት፣ የሕዝብ ግንኙነት እና የሪፎርም ሥራዎችን ያጠናክራል። የቅንጅትና ትብብር አምድ ሶስት ግቦች በመያዝ የፍትሕ አካላት ቅንጅት፣ ባለድርሻ አካላት አጋርነት፣ እና የዓለም ዓቀፍ ተሳትፎና ትብብርን ያሳድጋል። እነዚህ ግቦች በዕቅዱ ዘመን የፍትሕ ሥርዓቱን በማሻሻል የሕግ የበላይነትን በማስጠበቅ እና ውጤታማ፣ አካታች እና ቀልጣፋ የፍትሕ አገልግሎት ተደራሽ በማድረግ የሕዝብ እርካታን ለማሳደግ ተቀናጅተው ተግባራዊ ይደረጋሉ።

ይህ ስትራቴጂ የፍትሕ ዘርፉን ከተለመደው ያልዘመነ ሁኔታ ወደ ተደራጀና የተቀናጀ ውጤታማ አመራር እንዲሸጋገር ፍትሕ ሚኒስቴር የመሪነትና የፈፃሚነት፣ የአስተባባሪነት ሚናውን እንዲወጣና በፍትሕ ሥርዓቱና አገራዊ ትልሞች በጎ ተፅአኖውን ለማሳረፍ ያስችለዋል።

ተጨማሪ ዕቅዶችና ሪፖርቶች

ጥቅምት፥ 2018 ዓ.ም

Annual Fiscal Plans & Reports
መጋቢት 2015

Annual Fiscal Plans & Reports