ቀን: ሰኔ 2016 ዓ.ም.
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ
National Bank Of Ethiopia

የፌዴራል አስተዳደር ሥነ-ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 1183/2012 አፈፃፀም የክትትል ሪፖርት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ

ይህ የክትትል ሪፖርት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የአስተዳደር ሥነ-ሥርዓት አዋጅ አፈጻጸም የሚዳስስ ነው። እንደሚታወቀው በሀገራችን የአስተዳደር ሥነ-ሥርዓት አዋጅ ጸድቆ በስራ ላይ ከዋለ አመታት ተቆጥረዋል። ይህ አዋጅ የአስተዳደር ተቋማት በሕግ በተሰጣቸው መመሪያ የማውጣት ስልጣን እና ባላቸው ከፊል የዳኝነት ስልጣን መሰረት በዕለት ተዕለት ተግባራቸው ውሳኔ በሚያስተላልፉበት ጊዜ የዘፈቀደ አሰራር እንዳይኖር እና የተገልጋዮች መብት ያለአግባብ እንዳይጣስ ለመከላከል ያለመ ነው።

አስተዳደር ሥነ-ሥርአት አዋጁን አፈጻጸም የመከታተል ዓላማ ተቋማት መመሪያ ሲያወጡም ሆነ አስተዳደራዊ ውሳኔ ሲሰጡ አዋጁ ያስቀመጣቸውን ሂደቶች በማክበር ዜጎች ላይ የሚደርሰውን አላስፈላጊ እንግልት ለመቀነስ እና በቀጣይ ሂደቶቹን አልተከተለም ተብሎ ለሚነሳው የፍርድ ቤት ክርክር መንግስት የሚያወጣቸውን አላስፈላጊ ወጪዎች ለመቀነስ የወጡ መመሪያዎችን ብቻ ሳይሆን በመውጣት በሂደት ላይ ያሉ ረቂቅ መመሪያዎችን ሂደት ጭምር በመፈተሽ የአዋጁን አተገባበር ማዳበር ነው።

ይህንን ክትትል ለማድረግ የመጀመሪያ ደረጃ እና የሁለተኛ ደረጃ የመረጃ ምንጮች ጥቅም ላይ ውለዋል። በዚህም መሰረት የተቋሙ ስልጣን እና ተግባር የሚወስኑ ሕጎች ላይ የተደረገ ዳሰሳ፤ መመሪያዎች እንዲሁም ሰርኩላር የሚባል ስያሜ የተሰጣቸው ነገር ግን የመመሪያ አይነት ሕጋዊ ውጤት ያላቸው የሕግ ሰነዶች ስለመኖራቸው ዳሰሳ ተደርጓል። በተጨማሪም በየደረጃው ያሉ የተቋሙ የስራ ክፍል ኃላፊዎች ጋር የተደረገ ቃለ መጠየቅ እንደ የመጀመሪያ ደረጃ የመረጃ ምንጭ ተወስደዋል። አስተዳደራዊ ውሳኔ አሰጣጥ ጋር በተያያዘ የአቤቱታ ማቅረቢያ እና መቀበያ ቅጾችን፣ የመልስ መስጫ ቅጾች፣ የውሳኔ ናሙናዎችን የታዩ ሲሆን እንደ አጠቃላይ የአስተዳደር ሥነ-ሥርዓት አዋጅ ማብራሪያ ሰነድ ለመረጃ ግብዓት ጥቅም ላይ ውለዋል።

በሁለተኛ ደረጃ መረጃ ምንጮች መመሪያ አወጣጥን በተመለከተ የተቋሙ ድረ-ገጽ ላይ ምልከታ ማድረግ፣ የሚመለከተው የፍትህ ሚኒስቴር ድረ-ገጽ አድራሻ ላይ ዳሰሳ ተደርጓል።

በዚህም መሰረት በተቋሙ ጸድቀው በስራ ላይ ያሉ 166 መመሪያዎች ሲኖሩ ከነዚህም ውስጥ 25 የሚሆኑት አዋጁ ከወጣ በኋላ ወደ ስራ የገቡ ናቸው። ከነዚህ አዳዲስ መመሪያዎች የመመሪያ አወጣጥ ስርዓትን በተመለከተ መዝገብ ማደራጀት፣ መመሪያዎችን ለባለድርሻ አካላት ለአስተያየት ማቅረብ፣ የውይይት መድረክ ማዘጋጀት፣ አስተያየት ተቀብሎ ማካተት(4)፣ ለፍትህ ሚኒስቴር ለአስተያየት መላክ፣ ማብራሪያ ጽሁፍ ማዘጋጀት፣ መመሪያዎችን ከማስመዝገብ ሁሉም መመሪያዎች ተመዝግበዋል እንዲሁም ተደራሽ ከማድረግ አንጻር ከተጠቀሱት 25 መመሪያዎች 15 የሚሆኑት ላይ አንዳንድ የመመሪያ አወጣጥ ስነ ስርዓት ድንጋጌዎችን ለመተግበር የተሞከረ ቢሆንም አዋጁ ከሚጥለው ግዳታ አንጻር አጥጋቢ በተሟላ ሁኔታ እያንዳንዱን የመመሪያ አወጣጥ ስነ ስርዓት ድንጋጌ አሟልቶ የተገኘ መመሪያ የለም ይህም በድክመት የተያዘ ነው።

በሌላ በኩል ማስታወቂያ ከማውጣት እና መመሪያዎችን በሁለት ቋንቋ ከማዘጋጀት አንጻር ተቋሙ ምንም ስራዎች አልተሰራበትም ይህም በድክመት የተያዘ ነው። መመሪያዎችን ተደራሽ ከማድረግ እና ድረ-ገጽ ላይ ከመጫን አንጻር ተቋሙ ድረ-ገጽ ላይ የተጫኑት ፍትህ ሚኒስቴር በሰጠው ቁጥር ሳይሆን በራሱ በተቋሙ በተሰጠው ቁጥር በመሆኑ ተገልጋይን የሚያደናግር እና ትክክለኛ ዳታ ለማግኘት የሚያስቸግር ነው ይህም በክትትሉ ግኝት በድክመት የተያዘ ነው።

ባጠቃላይ ከላይ ለተነሱት መመሪያ አወጣጥ ጋር ተያይዞ አዋጁ ላይ የታዩ የአተገባበር ክፍተቶች እንደ ምክንያት በተቋሙ በኩል ያለው የስራ ጫና እና የሰው ኃይል እጥረት ተደጋግሞ የተነሳ ቢሆንም በክትትሉ መረዳት እንደተቻለው ለአዋጁ አፈጻጸም የተሰጠው ትኩረት አናሳ መሆኑ ነው።

አስተዳደራዊ ውሳኔ አሰጣጥ እና ቅሬታ አፈታትን በተመለከተ የአስተዳደር ሥነ-ስርዓት አዋጁ የተለያዩ ድንጋጌዎች ላይ መሰረት በማድረግ ክትትል ተደርጓል። በዚህም መሰረት ተቋሙ ያለበት የአፈጻጸም ደረጃ ለመገምገም 38 የውሳኔ ናሙናዎች ተወስደው የታዩ ሲሆን በዚህም መሰረት የአስተዳደር ጥያቄዎች እና ይዘት አንጻር ወጥ የሆነ አሰራር አለመኖሩ፣ የውሳኔ አሰጣጥ ይዘት እና በተገቢው ጊዜ መስጠት ላይ በከፊል የአዋጁን ድንጋጌዎች ለመተግበር ጅማሬዎች ያሉ መሆኑን ለመረዳት ተችሏል። በሌላ በኩል አስተዳደራዊ ጥያቄን ተቀብሎ ማስረጃ መስጠት፣ ውሳኔን ለተገልጋይ መስጠት፣ የቅሬታ ሰሚ አካል ማቋቋምን በተመለከተ በተቋሙ ምንም ያልተሰራበት በመሆኑ በድክመት የተያዘ ነው።

በተቋሙ በአንጻራዊ ሁኔታ አስተዳደራዊ ውሳኔ እና ቅሬታዎችን ተቀብሎ ከመስማት እና ከመመርመር አንጻር ጥሩ የሚባል አተገባበር ለማየት ተችሏል።

በአስተዳደሩ አዋጁን በተገቢው ሁኔታ ከመፈጸም አኳያ ክፍተት ለታየባቸው ጉዳዮች ምክንያት ዋነኛ የሚባለው አዋጁ እያንዳንዱ ድንጋጌዎች የተካተቱበት በምክንያት መሆኑን ተረድቶ በመፈጸም ረገድ ትኩረት አለመስጠት መሆኑን መገንዘብ ይቻላል።

በመጨረሻም የተቋሙ አስተዳደር ሥነ-ሥርዓት አዋጅ አፈጻጸም እንዲሻሻል የታዩ መልካም ተሞክሮዎች እንዲዳብሩ ክፍተቶች እንዲታረሙ የሚያስችሉ ምክረ ሀሳቦች ተሰጥተዋል።

ሪፖርቱን ያውርዱ

ተጨማሪ ሪፖርቶች