ቀን: ጥር 2014 ዓ.ም.
የገቢዎች ሚኒስቴር
Ministry of Revenues

የአስተዳደር ሥነ-ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 1183/2012 የአፈጻፀም ክትትል ሪፖርት በገቢዎች ሚኒስቴር •

በሀገራችን የአስተዳደር ሥነ-ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 1183/2012 (ከዚህ በኋላ በጽሁፉ ውስጥ አዋጁ እየተባለ የሚጠራው) መጋቢት 29 ቀን 2012 ዓ/ም የወጣ መሆኑ ይታወቃል። የፍትህ ሚኒስቴር (በቀድሞ ስያሜው ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ) ከዩኤስኤይድ ኢትዮጵያ የፍትህ አክቲቪቲ ፕሮጀክት ጋር በመተባበር ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችና የፌዴራል መንግስቱ አስተዳደር ተቋማት የበላይ አመራሮች በስልጠና መልክ አዋጁን የማስተዋወቅ ተግባር አከናውኗል።

የአዋጁን መውጣት አስፈላጊነት በመግቢያው ላይ እንደሚከተለው ተዘርዝሯል። ይህም፦

  • በሕገ መንግስቱ ላይ የተቀመጠውን መንግስታዊ አሰራር ለህዝብ ግልጽ በሆነ መንገድ መከናወን እንዳለበት የተደነገገውን ለማስፈጸም ይረዳ ዘንድ፤
  • ማናቸውም የመንግስት ባለስልጣን ኃላፊነቱን ሲያጓድል ተጠያቂ እንደሚሆን በሕገ መንግስቱ የተደነገገውን ለማስፈጸም ይረዳ ዘንድ፤
  • የአስተዳደር ተቋማት በሰዎች መብትና ጥቅም ላይ የሚያስከትለውን ጣልቃ ገብነት በሕግ የሚመራና ለሕግ የሚገዛ መሆኑን ለማረጋገጥ፤
  • የአስተዳደር ተቋማት የውሳኔ አሰጣጥና የመመሪያ አወጣጥ መርሆዎችንና ሥነ-ሥርዓት እንዲሁም በአስተዳደራዊ ውሳኔዎችና መመሪያዎች ቅር የተሰኘ ሰው በፍርድ ቤት የሚያስመረምርበት ስርዓት በመደንገግ አስተዳደራዊ ፍትህ ማስፈን የሚሉት ናቸው።

የፍትሕ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት በአዋጅ ቁጥር 943/2008 ከተሰጠው ስልጣን መካከል በአዋጁ አንቀፅ 6(6) ላይ በፌዴራል መንግስቱ የሚወጡ ሕጎች ወጥነት ባለው መልኩ ተግባራዊ መደረጋቸውንና አስፈፃሚ መስሪያ ቤቶችም ስራቸውን በህጉ መሰረት መስራታቸውን የመቆጣጠርና የማረጋገጥ ኃላፊነት አንደኛው ነው። በዚህ መሰረት የፍትህ ሚኒስቴር በተመረጡ ተቋማትና ሕጎች ላይ የተለያዩ የአፈጻጸም ጥናቶችን በመስራት ሪፖርት ሲያቀርብ መቆየቱ ይታወሳል። ይህም ስራ ከዚህ የቀጠለ የተቋሙ የ2014 በጀት ዓመት መደበኛ ስራ አካል ነው። በዚህ ጥናት በገቢዎች ሚኒስቴር የአዋጁ አፈጻጸም ላይ በተለይም ከመመሪያ አወጣጥና ከአስተዳደራዊ ውሳኔ አሰጣጥ ጋር በተያያዘ የዳሰሳ ጥናት ተደርጓል።

ሪፖርቱን ያውርዱ

ተጨማሪ ሪፖርቶች