ቀን: ግንቦት 2016 ዓ.ም.
የባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር
Ministry of Culture and Sport

የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የአስተዳደር ሥነ-ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 1183/2012 አፈጻጸም የክትትል ሪፖርት

የአስተዳደር ሥነ-ሥርዓት አዋጅ ተቋማት በሕግ በተሰጣቸው መመሪያ የማውጣት ስልጣንና የአስተዳደራዊ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ በዕለት ተዕለት ተግባሮቻቸው ውሳኔ በሚያስተላልፉበት ጊዜ የዘፈቀደ አሰራር እንዳይኖር ለመከላከልና የተገልጋዮች መብት ያለአግባብ እንዳይጣስ ለመከላከል በማለም የወጣ መሆኑ ይታወቃል። ከዚህ አንጻር የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር እንደአስተዳደር ተቋም በአስተዳደር ሥነ-ሥርዓት አዋጅ የተመለከቱ የመመሪያ አወጣጥ ሂደቶችንና የአስተዳደራዊ ውሳኔ አሰጣጥ መርሆዎችን ተግባራዊ ከማድረግ አንጻር ክትትል በማድረግ የቀረበ ሪፖርት ነው።

ለዚህ ክትትል ጥቅም ላይ የዋለው የመረጃ ምንጭ ለተቋሙ በአዋጅ 1263/2014 እና በሌሎች ሕጎች ስልጣንና ተግባራት የሚሰጡ የሕጎች ዳሰሳ፣ ከመመሪያ አወጣጥና አስተዳደራዊ ውሳኔ አሰጣጥ ጋር ግንኙነት ያላቸውን የተቋሙን የስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ቃለ-መጠይቅ በማድረግ እና በተቋሙ የሚሰጡ የአስተዳደራዊ ውሳኔ ናሙናዎችንና ሌሎች ተያያዥ ሰነዶች ናቸው።

  • ከመመሪያ አወጣጥና አመዘጋገብ ጋር በተያያዘ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አዋጁ ከወጣ በኋላ ማሻሻያ ያደረገበትን አንድ መመሪያ ጨምሮ 12 የሚደርሱ መመሪያዎችን በፍትህ ሚኒስቴር ማስመዝገቡ በአዎንታዊነት የሚወሰድ ነው። ይሁን እንጂ ለመስሪያ ቤቱ ስልጣን ሰጪ ሕጎች ሲቀየሩ ተከታትሎ በተገቢው ጊዜ መመሪያን ከማውጣትና ማሻሻል አንጻር፣ የመመሪያዎች አወጣጥ መዝገብ አለመኖር፣ በረቂቅ መመሪያዎቹ ላይ ከህብረተሰቡ አስተያየት ለመሰብሰብ እንዲያስችል በጋዜጣ ወይም በተቋሙ ድረ-ገጽ ማስታወቂያ አለማውጣት፣ ለባለድርሻ አካላትና ለሚመለከታቸው የመንግስት ተቋማት ረቂቅ መመሪያው ለአስተያየት አለመላክ፤ ከባለድርሻ አካላት በስተቀር ለማንኛውም አካል ክፍት የሆነ የውይይት መድረክ አለማዘጋጀት፣ የመመሪያዎችን ማብራሪያ አለማዘጋጀት እና የወጡ መመሪያዎችን በድረ-ገጽ ላይ ተደራሽ አለማድረግ የመሳሰሉ ሰፊ ክፍተቶች ታይተዋል። ከአስተዳደራዊ ውሳኔ አሰጣጥና ቅሬታ አፈታት ጋር በተያያዘ የአስተዳደር ውሳኔ ይሰጠኝ አቤቱታ በጽሁፍ እንዲቀርብ ከማድረግ አንጻር በአንዳንድ ክፍሎች የተዘጋጁ ቅጾች መኖራቸው፣ የሚቀርብ አቤቱታ በመ/ቤት ገቢ ስለመደረጉ የሚመዘገብና ስለመቀበሉ በቀሪው ላይ የሚፈረም መሆኑ፣ ተገልጋዮች የሚያቀርቡት የሰነድ ማስረጃ የሚታይ መሆኑ እና የአስተዳደር ውሳኔ በጽሁፍ ለተገልጋዩ የሚሰጥ አንጻር ያለው አሰራር የአስተዳደር ሥነ-ሥርዓት አዋጁ መርሆዎች ጋር የሚጣጣም ሆኖ በመገኘቱ በጥንካሬ የሚወሰድ ነው። ይሁን እንጂ ከአስተዳደር ውሳኔ ይዘት አንጻር ውሳኔው ያረፈበትን የሕግ ድንጋጌ አለመጥቀስ እና የቀረበ ማስረጃ በውሳኔው ውስጥ ከማስፈርና ከመተንተን አንጻር፣ በተቋሙ የተቋቋመ የቅሬታ ማስተናገጃ አካል አለመኖር እና በተቋሙ ግልጽ እና ወጥ የሆነ የቅሬታ አቀራረብ ሥነ-ሥርዓት ይፋ አለማድረግ በክፍተት የታዩ ናቸው። በዚሁ መነሻ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የበላይ አመራር ለአዋጁ አፈጻጸም ተገቢውን ትኩረት በመስጠት ክትትል እንዲያደርግ፣ የሕግ አገልግሎት ክፍል የመመሪያ አወጣጥ ሂደቶችንና የአስተዳደራዊ ውሳኔ አሰጣጥ መርሆዎችን ሁሉም የስራ ክፍሎች አካተው ተግባራዊ እንዲያደርጉ እንዲያስተባብርና ክትትል እንዲያደርግ፣ አዋጁ በሚያዘው መሰረት ወጥ የሆነ የቅሬታ ሰሚ ወይም ማስተናገጃ አካል ማቋቋም እና የቅሬታ አቀራረብ ስርዓት ይፋ ማድረግ እንደሚገባ ምክረ-ሀሳብ ተሰጥቷል።

ሪፖርቱን ያውርዱ

ተጨማሪ ሪፖርቶች