ቀን: ጥር 2014 ዓ.ም.
የገንዘብ ሚኒስቴር
Ministry of Finance

የፌዴራል የአስተዳደር ሥነ-ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 1183/2012 ን አተገባበር በተመለከተ በገንዘብ ሚኒስቴር የተደረገ የአፈፃፀም ክትትል ሪፖርት

አስተዳደራዊ ፍትህ የማህበራዊ ፍትህ የማዕዘን ድንጋይ ነው። አስተዳደራዊ ፍትህ ምናልባትም ከወንጀል እና ከፍታብሔር ክርክሮች በላይ በብዙ ሺህዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን የዕለት ተዕለት ኑሮ ወይም እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ጫና የሚያሳድር የፍትህ ዘርፍ ነው ማለት ይቻላል። ዜጎች የመንግስት አሰራር በግልጽ የሚከታተሉበት እና ጥቅማቸውን በሚጎዳ የመንግስት ውሳኔዎች በቀጥታ ተሳታፊ የሚሆኑበት እንዲሁም በሕግ ጥበቃ የተደረገላቸው መብቶቻቸው ላይ ጥሰት የሚፈጽሙ የመንግስት አካላትን እና ውሳኔዎቻቸውን ተቃውመው በፍርድ ሂደት መፍትሄ የሚያገኙበትን የሕግ ስርዓት መፍጠር አንድ አገር ለሰዎች ልጆች ክብር እና እኩልነት የምትሰጠውን ክብደት እና ያላትን ቀና አመልካከት የሚያመለክት ከመሆኑም በላይ መንግስት ለሕግ የበላይነት መከበርም ሆነ ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ያለውን ቁርጠኝነት ለዜጎች የሚያስመሰክርበት ዋነኛ መንገድ ነው። በአንድ አገር ይህ የሕግ ስርዓት ተፈጠረ ማለት የምንችለው ደግሞ የአስተዳደር ስነ-ስርዓት ሕግ ሲኖር ነው።

በዚሁ አግባብ በሀገራችን በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግስት መንግስታዊ አሰራር ለሕዝብ ግልጽ በሆነ መንገድ መከናወን እንዳለበትና ማናቸውም የመንግስት ባለስልጣን ኃላፊነቱን ሲያጓድል ተጠያቂ እንደሚሆን ተመልክቷል። በተጨማሪም የአስተዳደር ተቋማት በሰዎች መብቶችና ጥቅሞች ላይ የሚያስከትለውን ጣልቃ ገብነት በሕግ የሚመራና ለሕግ የሚገዛ መሆኑን ማረጋገጥ ያስፈጋል። የአስተዳደር ተቋማት የውሳኔ አሰጣጥና የመመሪያ አወጣጥ መርሆዎችና ሥነ-ሥርዓት እንዲሁም በአስተዳደራዊ ውሳኔዎችና መመሪያዎች ቅር የተሰኘ ሰው የውሳኔዎቹንና የመመሪያዎቹን ሕጋዊነት በፍርድ ቤት የሚያስመረምርበት ስርዓት በሕግ መደነገግ ያስፈጋል። በዚሁ አግባብ በሀገራችን እነዚህን እና ሌሎች ዓላማዎችን ለማስፈጸም ከመጋቢት 29/2012 ዓ.ም ጀምሮ እንዲተገበር የፌዴራል የአስተዳደር ሥነ-ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 1183/2012 ታውጇል።

በዚሁ አዋጅ መሰረት ማንኛውም የአስተዳደር ተቋም በሕግ በተሰጠው የውክልና ስልጣን መሰረት መመሪያ ማውጣት ይችላል። የአስተዳደር ተቋም መመሪያ የሚያወጣው በዚህ አዋጅ በተደነገገው ሥነ-ሥርዓት መሰረት ብቻ መሆኑም ተገልጿል። ማንኛውም ሰው መብቱን ወይም ጥቅሙን በሚመለከት የአስተዳደር ተቋም መመሪያ ያላወጣ ቢሆንም የአስተዳደር ውሳኔ እንዲሰጠው የመጠየቅ መብት አለው። ማንኛውም የአስተዳደር ተቋም ሊያወጣ የሚገባውን መመሪያ አለማውጣቱ በሕግ በተሰጠው ኃላፊነት ሊሰጥ የሚገባውን አገልግሎት ወይም አስተዳደራዊ ውሳኔ ላለመስጠት ምክንያት ሊሆን አይችልም።

በሌላ በኩል በፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ (የአሁኑ ፍትህ ሚኒስቴር) ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 943/2008 ዓ.ም አንቀፅ 6(6) የፌዴራል ሕጎች መተግበራቸውን፤ አተገባበራቸውም ወጥነት ያለው መሆኑን እንዲሁም አስፈጻሚ የፌዴራል መንግስት መስሪያ ቤቶች ስራዎቻቸውን በሕግ መሰረት መስራታቸውን የማረጋገጥ ኃላፊነት ለፍትህ ሚኒስቴር ከተሰጡ ስልጣን እና ተግባራት መካከል አንዱ መሆኑ ተገልጿል። ተቋሙ ይህንን ተልዕኮ ለመወጣት ከሚያከናውናቸው ስራዎች ውስጥ የአፈጻጸም ክትትል ዳሰሳ ጥናት በማድረግ ሕጎችን በማስፈጸም ረገድ ያሉ ክፍተቶች እና ጥንካሬዎችን በመለየት፤ ሕጎች እየተፈጸሙ ካልሆነ ምክንያታቸውንም ጭምር በማጥናት ማስተካከያ እንዲደረግባቸው ምክረ ሀሳቦች በመስጠት የተሰጡ ምክረ ሀሳቦችም እንዲተገበሩ ክትትል ማድረግ፤ እንዲሁም ሕጎቹ እየተፈጸሙ ከሆነም ለዚሁ እውቅና በመስጠት ተሞክሮዎችን በመቀመር የማስፋት ስራ ይሰራል። በዚህም መሰረት ተቋማችን በ2014 ዓ.ም በጀት ዓመት ሊያከናውናቸው በእቅድ ከያዛቸው ተግባራት መካከል ከላይ የተጠቀሰው የፌዴራል አስተዳደር ስነ-ስርዓት ሕግ አፈጻጸም ላይ ክትትል ማድረግ ሲሆን የገንዘብ ሚኒስቴር ካለው ትልቅ ኃላፊነት እና ሰፊ የሆነ መመሪያ የማውጣት ስልጣን አንጻር ለክትትል ከተመረጡ ተቋማት አንዱ ሆኖ ተመርጧል። በዚህም መሰረት ባለፉት ሶስት ወራት ውስጥ በገንዘብ ሚኒስቴር ውስጥ ክትትል በማድረግ የሚከተለው ሪፖርት ተዘጋጅቷል።

ሪፖርቱን ያውርዱ

ተጨማሪ ሪፖርቶች