ቀን: 2015 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የደንብ ማስከበር ባለስልጣን
Addis Ababa City Administration Code Enforcement Authority

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የደንብ ማስከበር ባለሥልጣን የፌደራል አስተዳደር ሥነ-ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 1183/2012 አፈፃፀም

በተሻሻለው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቻርተር አዋጅ ቁጥር 361/1996 መሠረት የተቋቋመው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት በቻርተሩ አንቀጽ 13 (1) (ሀ) በተሰጠው ሥልጣን መሠረት የተሻሻለውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስፈጻሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር መወሰኛ አዋጅ ቁጥር 74/2014 አውጥቶ ሥራ ላይ እንዲውል አድርጓል፡፡ በዚሁ አዋጅ ከተቋቋሙት አስፈጻሚ አካላት አንዱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደንብ ማስከበር ባለሥልጣን ሲሆን ሥልጣንና ተግባሩም በአዋጁ በአንቀጽ 47 ላይ ተዘርዝሯል፡፡ ባለሥልጣኑ ዋነኛ ተግባሩ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚፈጸሙ የደንብ መተላለፍችን በመከላከል፣ በመቆጣጠር እና አስተዳደራዊ እርምጃ በመውሰድና በማስወሰድ ከተማዋን ምቹ ከተማ ማድረግ ነው፡፡ ለዚሁ ተግባርም በከተማዋ የደንብ መተላለፍ ድርጊቶችን የሚከለክሉ፣ እርምጃ የሚወስዱና የሚያስወስዱ በእያንዳንዱ ወረዳ ከ35 እስከ 40 የሚደርሱ ክፍት ወታደራዊ ሥልጠና ወስደው ያጠናቀቁ በድምሩ 6048 ደንብ አስከባሪ ኦፊሰር ባለሙያዎችን አሰማርቷል፡፡ ባለሥልጣኑ የደንብ ጥሰት በማስተካከል፤ ከተማዋን ምቹ ከተማ ለማድረግ በተሰጠው ውክልና መሠረት ማስፈጸሚያ መመሪያ ማውጣት አለማውጣቱን፤ የደንብ መተላለፍ ድርጊቶችን ፈጽመዋል በማለት በሚወስደው አስተዳደራዊ እርምጃ ቅሬታ ያለቸው ሰዎች አስተዳደራዊ ውሳኔ የሚጠይቁበት፣ በሚሰጠው አስተዳደራዊ ውሳኔ ላይ ቅሬታ ያለቸው ሰዎች ቅሬታቸውን የሚያቀርቡበትና ውሳኔ የሚያገኙበት ሥርዓት መዘርጋት አለመዘርጋቱን በአጠቃላይም ለፌዴራል አስተዳደር ሥነ ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 1183/2012 እየተገዛ ስለመሆኑ ለማረጋገጥ በባለሥልጣኑ ላይ ይህ ክትትል ሊካሄድ ችሏል፡፡ በዚሁ መሠረት፣ የደንብ ማስከበር ባለሥልጣን በተመረጡ አራት ክፍለ ከተሞችና በዘጠኝ ወረዳ ደንብ ማስከበር ቅ/ጽ/ቤቶች በአካል በመገኘት ለክትትሉ ግብአት ሊሰጡ የሚችሉ የሚመለከታቸውን ኃላፊዎችና ሠራተኞች ቃለ መጠይቅ ተደርጓል፣ የሰነድና የፎቶግራፍ ማስረጃዎች ተሰብስበዋል፣ ምልከታም ተካሂዷል፡፡

በክትትሉ የተሰበሰቡ መረጃዎችና ማስረጃዎች ከፌዴራል አስተዳደር ሥነሥርዓት አዋጁ ጋር ተገናዝበው ሲታዩ፤ የሚመለከታቸው የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች በአስተዳደር ሥነ-ሥርዓት አዋጁ ላይ ስልጠና ባለመሰጠቱ በግንዛቤ እጥረት ምክንያት የአፈጻጸም ክፍተቶች ታይተዋል፡፡ ከመመሪያ አወጣጥ አንፃር የባለሥልጣኑን አፈጻጸም ስንገመግም ከአዋጁ መውጣት በኋላ አዲስ ጸድቆ ሥራ ላይ የዋለ መመሪያ የሌለ መሆኑን አይተናል፡፡ ይሁን እንጂ በሂደት ላይ ያለ አንድ መመሪያ እስከአለበት ደረጃ ሊከተላቸው በሚገቡ ሂደቶች ገምግመነዋል፡፡ በዚህም መሠረት በተገቢው ጊዜ መመሪያ ከማውጣት እና ከቅርጽ አንፃር የተሻለ አፈጻጸም ያለ ሲሆን መዝገብ ማደራጀትና ማስታወቂያ ከማውጣት አንፃር ክፍተት ያለ መሆኑን ተመልክተናል፡፡ ባለስልጣኑ በተሰጠው የውክልና ስልጣን መሠረት ለሥራው አስፈላጊ የሆኑ መመሪያዎችን አውጥቶ ሥራ ላይ እንዲውሉ ማድረጉ ጥሩ ቢሆንም ነባር መመሪያዎችን ለፍትሕ ሚኒስትር ልኮ ማስመዝገብ ሲገባው አለማስመዝገቡን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ባለሥልጣኑን ጨምሮ በክፍለ ከተሞችና በወረዳ ደንብ ማስከበር ቅ/ጽ/ቤቶች፤ ተገልጋዮች መብቴ ወይም ጥቅሜ ተነክቷል ብለው በሚያቀርቡት አስተዳደራዊ ውሳኔ ይሰጥልኝ አቤቱታ ላይ በተገቢው ጊዜ አስተዳደራዊ ውሳኔ በመስጠትና በተሰጠ አስተዳደራዊ ውሳኔ ላይ ተገልጋዮች የሚያቀርቡትን ቅሬታ ተቀብሎ በማስተናገድ ረገድ ለናሙናነት የተሰበሰቡ ውሳኔዎች ከአስተዳደር ሥነ-ሥርዓት አዋጁ ጋር የተጣጣሙ ሆነው ተገኝተዋል፡፡ ባለሥልጣኑ ለተገልጋዮች የቅሬታ ማስተናገጃ አካል “ቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ” የሚል መጠሪያ ስያሜ በመስጠት በየደረጃው አቋቁሞ ከመሆኑም በተጨማሪ ይህንኑ ለተገልጋዮች ይፋ ለማድረግ የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ አባላትን ዝርዝር ተገልጋዮች እንዲያውቁ በአንዳንድ ወረዳ እና ክፍለ ከተማ ጽ/ቤቶች የተመለከትን ቢሆንም በተሟላ ሁኔታ ተገልጋዮች እንዲያውቁ ተደርጓል ማለት አይቻልም፡፡

ባለሥልጣኑ በሚወስደው አስተዳደራዊ እርምጃ ግለሰቦች ቅሬታቸውን በቀጥታ ለተቋሙ ሳይሆን ለፍ/ቤት ሁከት ይወገድልኝ ክስ እያቀረቡ የተወሰነላቸውና የተወሰነባቸውን ተመልክተናል፡፡ ባለሥልጣኑ ካለው የተቆጣጣሪነት እና አስተዳደራዊ እርምጃ የመውሰድ ሰፊ ኃላፊነትና ተግባራት እንዲሁም በአጠቃላይ ከሕግ አንፃር በቅርብ ሆኖ ድጋፍ የሚሰጥ የሕግ ባለሙያ የሌለው መሆኑንም ተመልክተናል፡፡ በአጠቃላይ በዚህ የክትትል ሪፖርት ለአዋጁ ከመገዛት አንፃር በደንብ ማስከበር ባለሥልጣን የታዩ ጥንካሬዎች እንዲቀጥሉ የታዩ ክፍተቶች ደግሞ እንዲታረሙ ምክረ ሀሳብ ቀርቦበታል፡፡

ሪፖርቱን ያውርዱ

ተጨማሪ ሪፖርቶች