ቀን: የካቲት 2014 ዓ.ም.
የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር
Ministry of Health

የፌዴራል የአስተዳደር ሥነ-ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 1183/2012 ን አተገባበር በተመለከተ በጤና ሚኒስቴር የተደረገ የአፈፃፀም ሪፖርት

አስተዳደራዊ ፍትህ የማህበራዊ ፍትህ የማእዘን ድንጋይ ነው፡፡ አስተዳደራዊ ፍትህ ምናልባትም ከወንጀል እና ከፍትሐ ብሔር ክርክሮች በላይ በብዙ ሺህዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን የእለት ተእለት ኑሮ ወይም እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ጫና የሚያሳድር የፍትህ ዘርፍ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ዜጎች የመንግስት አሰራር በግልጽ የሚከታተሉበት እና ጥቅማቸውን በሚጎዳ የመንግስት ውሳኔዎች በቀጥታ ተሳታፊ የሚሆኑበት እንዲሁም በህግ ጥበቃ የተደረጉላቸው መብቶቻቸው ላይ ጥሰት የሚፈጽሙ የመንግስት አካላትን እና ውሳኔዎቻቸውን ተቃውመው በፍርድ ሂደት መፍትሄ የሚያገኙበትን የህግ ስርዓት መፍጠር አንድ አገር ለሰው ልጆች ክብር እና እኩልነት የምትሰጠውን ክብደት እና ያላትን ቀና አመለካከት የሚያመላክት ከመሆኑም በላይ መንግስት ለሕግ የበላይነት መከበርም ሆነ ለዲሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ ያለውን ቁርጠኝነት ለዜጎች የሚያስመሰክርበት ዋነኛ መንገድ ነው፡፡ በአንድ አገር ይህ የሕግ ስርአት ተፈጠረ ማለት የምንችለው ደግሞ የአስተዳደር ስነ-ስርዓት ህግ ሲኖር ነው፡፡

በዚሁ አግባብ በሃገራችን በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞከራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግስት መንግስታዊ አሰራር ለሕዝብ ግልጽ በሆነ መንገድ መከናወን እንዳለበትና ማናቸውም የመንግስት ባለሥልጣን ኃላፊነቱን ሲያጓድል ተጠያቂ እንደሚሆን ተመልክቷል፡፡ በተጨማሪም የአስተዳደር ተቋማት በሰዎች መብቶችና ጥቅሞች ላይ የሚያስከትሉትን ጣልቃ ገብነት በሕግ የሚመራና ለሕግ የሚገዛ መሆኑን ማረጋገጥ ያስፈሌጋል፡፡ የአስተዳደር ተቋማት የውሳኔ አሰጣጥና የመመሪያ አወጣጥ መርሆዎችና ሥነ-ሥርዓት እንዲሁም በአስተዳደራዊ ውሳኔዎችና መመሪያዎች ቅር የተሰኘ ሰው የውሳኔዎቹንና የመመሪያዎቹን ሕጋዊነት በፍርድ ቤት የሚያስመረምርበት ሥርዓት በህግ መደነገግ ያስፈሌጋል፡፡ በዚሁ አግባብ በሃገራችን እነዚህን እና ሌሎች አላማዎችን ለማስፈጸም ከመጋቢት 29/2012 ዓ.ም ጀምሮ እንዲተገበር የፌዴራል የአስተዳደር ሥነ-ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 1183/2012 ታውጇል፡፡

በዚሁ አዋጅ መሰረት ማንኛውም የአስተዳደር ተቋም በሕግ በተሰጠው የውክልና ሥልጣን መሠረት መመሪያ ማውጣት ይችላል፡፡ የአስተዳደር ተቋም መመሪያ የሚያወጣው በዚህ አዋጅ በተደነገገው ሥነ-ሥርዓት መሠረት ብቻ መሆኑም ተገልጿል፡፡ ማንኛውም ሰው መብቱን ወይም ጥቅሙን በሚመለከት የአስተዳደር ተቋም መመሪያ ያላወጣ ቢሆንም የአስተዳደር ውሳኔ እንዲሰጠው የመጠየቅ መብት አለው፡፡ ማንኛውም የአስተዳደር ተቋም ሊያወጣ የሚገባውን መመሪያ አለማውጣቱ በሕግ በተሰጠው ኃላፊነት ሊሰጥ የሚገባውን አገልግሎት ወይም አስተዳደራዊ ውሳኔ ያለመስጠት ምክንያት ሊሆን አይችልም፡፡

በሌላ በኩል በፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ (የአሁኑ ፍትህ ሚኒስቴር) ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 943/2008 ዓ.ም አንቀጽ 6(6) የፌዴራል ህጎች መተግበራቸውን፤ አተገባበራቸውም ወጥነት ያለው መሆኑን እንዲሁም አስፈጻሚ የፌዴራል መንግስት መስሪያ ቤቶች ስራዎቻቸውን በህግ መሰረት መስራታቸውን የማረጋግጥ ኃላፊነት ለፍትህ ሚኒስቴር ከተሰጡ ስልጣን እና ተግባራት መካከል አንዱ መሆኑ ተገልጿል፡፡ ተቋሙ ይህንን ተልዕኮ ለመወጣት ከሚያከናውናቸው ስራዎች ውስጥ የአፈጻጸም ክትትል ዳሰሳ ጥናት በማድረግ ህጎችን በማስፈጸም ረገድ ያሉ ክፍተቶች እና ጥንካሬዎችን በመለየት፤ ህጎች እየተፈጸሙ ካልሆነ ምክንያታቸውንም ጭምር በማጥናት ማስተካከያ እንዲደረግባቸው ምክረ ሀሳቦች በመስጠት የተሰጡ ምክረ ሀሳቦችም እንዲተገበሩ ክትትል ማድረግ፤ እንዲሁም ህጎቹ እየተፈጸሙ ከሆነም ለዚሁ እውቅና በመስጠት ተሞክሮዎችን በመቀመር የማስፋት ስራ ይሰራል፡፡ በዚህም መሰረት ተቋማችን በ2014 ዓ.ም በጀት ዓመት ሊያከናውናቸው በእቅድ ከያዛቸው ተግባራት መካከል ከላይ የተጠቀሰው የፌዴራል አስተዳደር ስነ-ስርዓት ህግ አፈጻጸም ላይ ክትትል ማድረግ ሲሆን የጤና ሚኒስቴር ካለው ትልቅ ሃላፊነት እና ሰፊ የሆነ መመሪያ የማውጣት ስልጣን አንጻር ለክትትል ከተመረጡ ተቋማት አንዱ ሆኖ ተመርጧል፡፡ በዚህም መሰረት ባለፈት ሶስት ወራት ውስጥ በጤና ሚኒስቴር ውስጥ ክትትል በማድረግ የሚከተለው ሪፖርት ተዘጋጅቷል፡፡

ሪፖርቱን ያውርዱ

ተጨማሪ ሪፖርቶች