የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት በድሬዳዋ አስተዳደር ቻርተር አዋጅ ቁጥር 416/1996፣ አንቀጽ 12(1/ሀ) በተሰጠው ስልጣን መሰረት የድሬዳዋ አስተዳደር አስፈጻሚና የማዘጋጃ ቤት አገልግሎት አካላትን እንደገና ለማቋቋም ተግባርና ኃላፊነታቸውን ለመወሰን አዋጅ ቁጥር 81/2016 አውጥቶ ሥራ ላይ እንዲውል አድርጓል። በዚሁ አዋጅ ከተቋቋሙት የከተማው አስፈጻሚ አካላት አንዱ የድሬዳዋ አስተዳደር ገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ሲሆን ቢሮው በአዋጁ አንቀጽ 5(2) መሰረት የተቋቋመ ሲሆን ስልጣንና ተግባሩም በአዋጁ አንቀጽ 12 (የወል ስልጣንና ተግባር) እንዲሁም በአንቀጽ 31 ላይ ተዘርዝሯል።
የአስተዳደር ተቋማት የፌዴራል አስተዳደር ሥነ-ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 1183/2012ን እንዴት እየተገበሩት እንደሆነ በክትትል ለማረጋገጥ ከተመረጡት ተቋማት አንዱ የድሬዳዋ አስተዳደር ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ሲሆን በተቋሙ ላይ ይህ ክትትል ሊካሄድ ችሏል። በዚሁ መሰረት በድሬዳዋ አስተዳደር ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ በአካል በመገኘት ለክትትሉ ግብአት ሊሰጡ የሚችሉ የሚመለከታቸውን ኃላፊዎችና ሰራተኞች ቃለ መጠይቅ ተደርገዋል፣ የሰነድ ማስረጃዎችም ተሰብስበዋል፣ ምልከታም ተካሂዷል።
በክትትሉ የተሰበሰቡ ማስረጃዎች ከፌዴራል አስተዳደር ሥነ-ሥርዓት አዋጁ ጋር ተገናዝበው ሲታዩ፤ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ በተሰጠው የውክልና ሥልጣን መሰረት ለስራው አስፈላጊ የሆኑ መመሪያዎችን አውጥቶ ሥራ ላይ እንዲውሉ ማድረጉን ማረጋገጥ የተቻለ ሲሆን ነባር መመሪያዎችን ለፍትሕ ሚኒስቴር ልኮ ማስመዝገብ ሲገባው አለማስመዝገቡን ለማወቅ ተችሏል። በመጨረሻም የታዩ ጥንካሬዎች እንዲቀጥሉ የታዩ ክፍተቶች ደግሞ እንዲታረሙ ምክረ ሀሳብ ቀርቦበታል።