ይህ የክትትል ሪፖርት በግል ድርጅት ሰራተኞች ማህበራዊ ዋስትና አስተዳደር የአስተዳደር ሥነ-ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 1183/2012 አፈጻጸም የሚዳስስ ነው። ይህ አዋጅ የአስተዳደር ተቋማት በሕግ በተሰጣቸው መመሪያ የማውጣትና አስተዳደራዊ ውሳኔ የመስጠት ስልጣን ምክንያት መመሪያ በሚያወጡበት ጊዜ ወይም ውሳኔ በሚሰጡበት ጊዜ የዘፈቀደ አሰራር እንዳይኖር ለመከላከልና የተገልጋዮች መብትና ጥቅም ለማስጠበቅ ያለመ እንደሆነ በአዋጁ መግቢያ ላይ ተመልክቷል።
በመሆኑም የዚህ ክትትል ዓላማ አዋጁ ሊያሳካ ያሰበውን ውጤት ዕውን እንዲሆን የሚያግዝ ቁልፍ ተግባር በመሆኑ አስተዳደሩ መመሪያ ሲያወጣና አስተዳደራዊ ውሳኔ ሲያሳርፍ በአዋጁ የተቀመጡ መስፈርቶችንና መርሆዎችን አክብሮ ከመስራት አንጻር ያለውን አፈጻጸም ለመዳሰስና ለአፈጻጸም ተግዳሮት የሆኑ ምክንያቶች በመለየት የመፍትሄ ሀሳብ ለመስጠት ያለመ ነው።
በመሆኑም ውጤታማ ክትትል ለማድረግ ተገቢ የሆነ መረጃ አሰባሰብ ዘዴ መከተል ያስፈልጋል። በመጀመሪያ አስተዳደሩ መመሪያ እንዲያወጣና ውሳኔ እንዲያሳርፍ ስልጣን ሰጪ የሆኑ ሕጎች ዳሰሳ ተደርጓል። በመቀጠልም ከመመሪያ አወጣጥና አስተዳደራዊ ውሳኔ አሰጣጥ ጋር ቁልፍ መረጃ ሊሰጡ የሚችሉ በየደረጃው ያሉ የአስተዳደሩ የስራ ኃላፊዎች ምክንያታዊ በሆነ መንገድ በመምረጥ ቃለ መጠይቅ ተደርጓል። እንዲሁም ከውሳኔ አሰጣጥ ጋር በተያያዘ የውሳኔ ናሙናዎችን በዘፈቀደ በመምረጥ የተቋሙን አስተዳደራዊ ውሳኔ አሰጣጥ ለማየት ተሞክሯል።
በተደረገው ክትትል የግል ሰራተኞች ማህበራዊ ዋስትና አስተዳደር በአዋጅ ቁጥር 1268/2014 እና በደንብ ቁጥር 523/2015 መሰረት ወደ አምስት የሚደርስ መመሪያዎች ማውጣት የሚጠበቅበት ሲሆን ከእዚህ ውስጥ ሁለት ብቻ ማውጣቱ ታይቷል። አስተዳደሩ በአዋጁ የተቀመጡ የቅድመ-መመሪያ መስፈርቶችን ከመከተል አንጻር እጅግ ደካማ የሚባል አፈጻጸም አሳይቷል። በአንጻራዊነት ከአስተዳደር ውሳኔ አሰጣጥ ጋር በተያያዘ የአስተዳደሩ አሰራር በአዋጁ ከተቀመጡ መርሆዎች ጋር የተቀራረበ በመሆኑ በዚህ ረገድ የተሻለ አፈጻጸም እንዳለው ተወስዷል። ከቅሬታ አፈታት ጋር በተያያዘ ምንም እንኳ አስተዳደሩ ቅሬታን የሚቀበልና የሚያይ ኮሚቴ አደረጃጀት ቢኖረውም ቅሬታውን የሚያዩት ውሳኔውን የሰጡት ባለሙያዎች በመሆኑ በገለልተኝነት ከመመርመርና ውሳኔ ከመስጠት አንጻር አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያሳድር ስለመሆኑ መገንዘብ ተችሏል።
በአጠቃላይ ለአዋጁ አፈጻጸም ተግዳሮት የሆኑት የግንዛቤ ችግርና የትኩረት ማነስ እንደምክንያት የታዩ በመሆኑ የአዋጁን አፈጻጸም ለማሳደግ ለሚመለከተው የስራ ኃላፊና ባለሙያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ቢሰጥና የበላይ አመራሩ ለአዋጁ አፈጻጸም እንደመደበኛ ስራ ትኩረት በመስጠት ድጋፍና ክትትል ቢያደርግ አፈጻጸሙን ማሳደግና የአዋጁን ዓላማ ማሳካት ይቻላል የሚል ምክረ ሀሳብ ተሰጥቷል።