ይህ የክትትል ሪፖርት የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር (ከዚህ በኋላ ተቋሙ እየተባለ የሚጠራው) የአስተዳደር ሥነ-ሥርዓት አዋጅ አፈጻጸም የሚዳስስ ነው። እንደሚታወቀው በሀገራችን የአስተዳደር ሥነ-ሥርዓት አዋጅ ጸድቆ በቅርቡ ሥራ ላይ የዋለ መሆኑ ይታወሳል። ይህ አዋጅ የአስተዳደር ተቋማት በሕግ በተሰጣቸው መመሪያ የማውጣት ስልጣን እና ባላቸው ከፊል የዳኝነት ስልጣን መሰረት በዕለት ተዕለት ተግባራቸው ውሳኔ በሚያስተላልፉበት ጊዜ የዘፈቀደ አሰራር እንዳይኖር እና የተገልጋዮች መብት ያለአግባብ እንዳይጣስ ለመከላከል ያለመ ነው።
አዋጁ ለሀገራችን በአይነቱ የመጀመሪያው እንደመሆኑ ቀደም ብሎ በነበረ አሰራር የተፈተነ ወይም የፍርድ ቤት ውሳኔዎች የጎለበተ አይደለም። በመሆኑም የሕጉ አፈጻጸሙ ምን ይመስላል የሚለውን ክትትል ማድረግ ዓላማ ተቋማት መመሪያ ሲያወጡም ሆነ አስተዳደራዊ ውሳኔ ሲሰጡ አዋጁ ያስቀመጣቸውን ሂደቶች በማክበር ዜጎች ላይ የሚደርሰውን አላስፈላጊ እንግልት ለመቀነስ እና በቀጣይ ሂደቶቹን አልተከተለም ተብሎ ለሚነሳው የፍርድ ቤት ክርክር መንግስት የሚያወጣቸውን አላስፈላጊ ወጪዎች ለመቀነስ የወጡ መመሪያዎችን ብቻ ሳይሆን በመውጣት በሂደት ላይ ያሉ ረቂቅ መመሪያዎችን ሂደት ጭምር በመፈተሽ የአዋጁን አተገባበር ማዳበር ነው።
በተቋሙ ለተሰራው ክትትል መረጃ ጥንቅር ተቋሙ በአዋጅ ቁጥር 1263/2014 እና በሌሎች ሕጎች የተሰጡትን ስልጣንና ተግባራት ለመለየት የሕጎች ዳሰሳ ተደርጓል። በሌላ በኩል ከመመሪያ አወጣጥ ጋር ግንኙነት ያላቸውን የተቋሙን የስራ ክፍሎች በመለየት የየክፍሉን ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች ቃለ መጠይቅና ውይይት እንዲሁም ምልከታዎች አድርገናል።
ተቋሙ የአስፈጻሚ አካላት ስልጣን እና ተግባር መወሰኛ አዋጅ ቁጥር 1263/2014 ላይ በተሰጠው መመሪያ የማውጣት የውክልና ስልጣን መሰረት በመውጣት ላይ ያሉ ረቂቅ መመሪያዎች ህጋዊነት እስከደረሱበት ድረስ መመሪያን በተገቢው ጊዜ ማውጣት፣ መዝገብ ማደራጀት፣ ማስታወቂያ ስለማውጣት፣ ለአስተያየት ማቅረብ፣ የውይይት መድረክ ስለማዘጋጀት፣ ለፍትህ ሚኒስቴር ለአስተያየት ስለማቅረብ፣ አስተያየቶችን ስለመቀበል፣ መመሪያ ስለሚዘጋጅበት ቋንቋ፣ የማብራሪያ ጽሁፍ ከማዘጋጀት አንጻር፤ ነባር መመሪያዎችን ከማስመዝገብ እና መመሪያን ተደራሽ ከማድረግ አንጻር ያለውን ተቋማዊ አሰራር እና ግንዛቤ ለመዳሰስ ተሞክሯል። በዚህ የክትትል ሪፖርት መሰረት ተቋሙ ሶስት ያህል ነባር መመሪያዎች በፍትህ ሚኒስቴር በቀድሞ የሴቶች ሕጻናት እና ወጣቶች ሚኒስቴር መስሪያ ቤት እና በቀድሞ ሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ስር ተመዝግበው የሚገኙትን የሚገለገልባቸው መሆኑን ተገንዝበናል። በሌላ በኩል አራት ያህል አዲስ መመሪያዎችን በማውጣት ሂደት ላይ እንዳለ እና መመሪያዎቹ ተጠናቅቀው ለመውጣት የበላይ አመራር ውሳኔ እየጠበቁ መሆናቸውን ተገንዝበናል።
በዚህም መሰረት በረቂቅ ደረጃ ያሉ መመሪያዎች በእናት ሕጉ በተሰጠው ፈቃድ ስልጣን ስር የተዘጋጁ መሆናቸው፣ ነባር መመሪያዎች ተመዝግበው መገኘታቸው እና አንድ ነባር መመሪያ በተቋሙ ድረ-ገጽ ላይ ተጭኖ ለሕዝብ ተደራሽ መደረጉ በጥንካሬ የሚወሰድ ሆኖ አግኝተነዋል። በሌላ በኩል በረቂቅ ደረጃ የሚገኙ አራቱም መመሪያዎች ላይ መዝገብ አለመደራጀቱ፣ ማስታወቂያ አለመውጣቱ፣ አስተያየቶችን በጽሁፍ አለመቀበል፣ የማብራሪያ ጽሁፍ አለማዘጋጀት እና በሁለት ቋንቋ አለመዘጋጀት በክትትሉ በክፍተት የተወሰዱ ናቸው። በመጨረሻም የተቋሙ አስተዳደር ሥነ-ሥርዓት አዋጅ አፈጻጸም እንዲሻሻል የታዩ መልካም ተሞክሮዎች እንዲዳብሩ ክፍተቶች እንዲታረሙ የሚያስችሉ ምክረ ሀሳቦች ተሰጥተዋል።