የፍትሕ ሚኒስቴር በአዋጅ ቁጥር 943/2008 በአንቀጽ 6(6) ላይ በፌደራል መንግሥቱ የሚወጡ ሕጎች ወጥነት ባለው መልኩ ተግባራዊ መደረጋቸውንና አስፈፃሚ መስሪያ ቤቶችም ሥራቸውን በሕጉ መሠረት መሥራታቸውን የመከታተል ኃላፊነት ተሰጥቶታል። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ይህን ኃላፊነት ለመወጣት በተመረጡ ሕጎችና ተቋማት ላይ የአፈጻጸም ክትትል ሥራዎችን ያከናውናል። በክትትል የተለዩ የአተገባበር ችግሮች ላይ የሚሰጡ ምክረ-ሐሳቦች ተግባራዊ ስለመደረጋቸው ዳግም ክትትል ያደርጋል።
በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ2001 ዓ.ም አዋጅ ቁጥር 624/2001 ፀድቆ ወደ ሥራ ከገባ በኋላ በ2014 ዓ.ም የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትህ ሚኒስቴር የሕግ የአፈጻጸም ዳሰሳ ጥናት በማድረግ የተገኙ ግኝቶች ላይ ምክረ-ሐሳቦች የተሰጠበት መሆኑ ይታወቃል። የአዋጁ መሠረታዊ ዓላማ ነዋሪዎች ጥራቱና ንጽህናው በጠበቀ፤ አቅርቦትንና ተደራሽነትን ባማከለ መልኩ በተገነባ መኖሪያ አካባቢና ሕዝባዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት እንዲገለገልና እንዲኖሩ ማስቻል እና የግንባታ ደኅንነት የተጠበቀ እንዲሆን ማስቻል ነው። ይህ ሊሆን የሚችለው ደግሞ የሚከናወነው የግንባታ ሥራ የሀገር ኢኮኖሚን፤ የሰው ኃይልና ቴክኖሎጂን ባገናዘበ መልኩ ዓለም አቀፍና ሀገር አቀፍ የግንባታ መርሆችንና ሕግጋትን መሠረት አድርጎ ከቅድመ-ግንባታ ጀምሮ ተጠናቆ አገልግሎት እስከሚሰጥ ድረስ በሕግ መሠረት ቁጥጥር ሲደረግበትና የታሰበውን አገልግሎት ሁሉንም ሕብረተሰብ ባሳተፈና ተጠቃሚ ባደረገ መልኩ ሲሰጥ ነው። በቀድሞው ክትትል የግንባታ ዘርፉ አሁን ባለንበት ደረጃ የውጭ ኢንቨስትመንትን የሚስብ፤ ብዙ ዜጎችን አቅፎ የሚሄድ፤ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ፍሰት ያለበት ቢሆንም በተለያየ ጊዜ በሚወጡ የሚዲያ ዘገባዎች እና ቅሬታዎች አንፃር በሰው ሕይወት፤ ጤናና ንብረት ብሎም በአካባቢ ላይ ጉዳትና ብክለትን የሚያስከትል፤ ለአካል ጉዳተኞች፤ በእድሜ ለገፉ አዛውንቶችና ለመሳሰሉት የማኅበረሰብ ክፍሎች ምቹ አለመሆን እንደሚታይበት በስፋትና በጥልቀት ታይቷል።
በዚህ ዳግም ክትትል በቀድሞ ክትትል ዋና ዋና ግኝቶች መሠረት የተሰጡ ምክረ-ሐሳቦች ተግባራዊነት መፈተሽ አስፈላገ ሆኖ ተገኝቷል። ክትትሉ በዋናነት የሕግ ማዕቀፍ ማሻሻያ፣ የክትትል፣ ድጋፍ እና ቁጥጥር ሥራዎችን ለሚሰሩ ተቋማት የተሰጡ አንኳር ምክረ-ሐሳቦች ላይ የተመሠረተ ነው። በዚህም መሠረት የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለስልጣን፣ አዲስ አበባ ግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን ላይ ተሠርቷል።
ክትትሉ አካታች እንዲሆን ከህንጻ አዋጁ ጋር ተያያዥ ከሆኑ የተቋማት የሕግ ማዕቀፍ ዳሰሳና ከእነዚሁ ተቋማት የተሰበሰቡ መረጃዎች በክትትሉ እንዲካተቱ ተደርጓል። በመሆኑም በህንጻ አዋጅ ዙሪያ ያሉ የሕግ ማዕቀፎችን እንዲሁም በቃለ መጠይቅና በሰነድ የተሰበሰቡ መረጃዎችን ከሕግ ማዕቀፎች ጋር በማገናዘብ የህንጻ አዋጅ ዙሪያ ያለበትን የሕግና የአተገባበር ችግሮችን በዝርዝር በመለየት የተሰራ ሲሆን በዚሁ መሠረት ለችግሮቹ መፍትሔ የሚሆኑ ምክረ-ሐሳቦች ተካትተዋል።
የዚህ የምክረ-ሐሳብ ክትትል ዓላማ በቀድሞ ጥናት ላይ የተሰጡ ምክረ-ሐሳቦች ተግባራዊ ስለመደረጋቸው ወይም አለመደረጋቸው እንዲሁም የአተገባበር ሁኔታቸው ያለበትን ደረጃ ለመለየት ነው። በሌላ በኩል ተግባራዊ ያልተደረጉ ምክረ-ሐሳቦች ካሉ ምክንያታቸውንና በዚህ ረገድ ተቋሙ የወሰደውን አቋም ወይም እርምጃ ለማየት ነው።
የተሰጡ ምክረ-ሐሳቦች ተግባራዊ ስለመደረጋቸው ወይም አለመደረጋቸው ከተቋማቱ ጋር አግባብነትና ተቀባይነት ያለው መረጃ ሊሰጥ ከሚችል የበላይ ኃላፊን ጭምር ያካተተ በተሰጠው እያንዳንዱ ምክረ-ሐሳብ ላይ ውይይት ተደርጓል። በዚህም መሠረት ማሻሻያ ሕግ ከማውጣት፣ ግንባታ ፈቃድ ከመስጠት እና ከመከታተል ጋር ግንኙነት ያላቸው የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር፣የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለስልጣን እና አዲስ አበባ ግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን የሚመለከታቸውን 14 የስራ ክፍል ኃላፊዎች እና የሚመለከታቸው ባለሙያዎች በተገኙበት መድረክ ላይ በምክረ-ሐሳቦች አተገባበር ላይ ተቋሙን በመወከል የሰጡት ሐሳብና አስተያየት እንደ ተቋሙ ሐሳብ ተወስዷል። እንዲሁም ክትትሉ ከተደረገ ወዲህ በተሰጠው ምክረ-ሐሳብ መሠረት ይሁን በሌላ ምክንያት የተከናወኑ የሕግ እና የአሠራር ማሻሻያ ሥራዎች የሚያሳዩ የሰነድ ማስረጃዎች በአስረጂነት እንዲቀርቡ ተደርጓል። ከዚህ በተጨማሪ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሪፖርቶች፣ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን በአዲስ አበባ የሚገኙ ሕንጻዎች ለአካል ጉዳተኞች ባላቸው ተደራሽነት ሁኔታ የተዘጋጀ ግልጽ አቤቱታ መቀበያ መድረክ እና የሚዲያ ዳሰሳ በማድረግ መረጃዎች ተሰባስበዋል።
የዚህ የምክረ-ሐሳብ ክትትል ሪፖርት እንደሚከተለው በሰንጠረዥ ቀርቧል። ሰንጠረዡም የተሰጡ ምክረ-ሐሳቦች ዝርዝር፣ የምክረ-ሐሳቦች አተገባበር ሁኔታ ማለትም ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ የተደረጉ፣ በከፊል ተግባራዊ የተደረጉ እና ምንም ተግባራዊ ያልተደረጉ ምክረ-ሐሳቦችና ምክንያቶቻቸውን ያካተተ መረጃ እንዲይዝ ተደርጓል። በመጨረሻም ሪፖርቱ ማጠቃለያ ሐሳብ እንዲኖረው ተደርጓል።