የፌዴራሉ መንግሥት ለክልሎች ለአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ሰመልሶ ማቋቋምና ለልማት ማስፋፊያ እንደዚሁም ለሚያስፈልጋቸው ወጪ የሚያደርገውን ድጐማ በሚመለከት ኦዲትና ቁጥጥር የማድረግ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 94 (2)ሥልጣን የተሰጠው በመሆኑ፣
የፌዴራል መንግሥቱ ኦዲትና ቁጥጥር የማድረግ ሥልጣን በአዋጅ ቁጥር 982/2008 (እንደተሻሻለው 1146/2011 ) አንቀጽ 17 ለፌዴራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት በመሰጠቱ፣
በሌላ በኩል ደግሞ በክልል ደረጃ የየክልሎቹ ዋና ኦዲተ መስሪያ ቤቶች በክልሉ የበጀት አዋጅ የታወጀው ሂሣብ ኦዲት እንዲያደርጉ ማቋቋሚያ አዋጆቻቸው ተመሳሳይ ሥልጣን ኃላፊነት የተሰጣቸው በመሆኑ፣
ይህ በየደረጃው ላሉ የኦዲት መስሪያ ቤቶች የተሰጣቸው ኃላፊነት ደግሞ አንድ ሂሳብ በፌደራልም ሆነ በክልል የዋና ኦዲተር መስሪያ ቤቶች ኦዲት የሚደረግበትን ሁኔታና ድግግሞሽን የሚፈጥር በመሆኑ፣
በአንፃሩ ይህ ድግግሞሽ በኦዲት ተደራጊ መስሪያ ቤቶች ላይ ከፍተኛ የሥራ ጫና ከማስከተሉም በላይ ለተመሳሳይ ሥራ በድጋሚ በሚውለው ጊዜና የሰው ኃይል ምክንያት አላስፈላጊ ወጪ በማድረጉ፣
ስለሆነም ይህንን ችግር ለማስወገድ እንደዚሁም በሀገር አቀፍ ደረጃ የኦዲት አሠራሩንና ሥርዓቱን ወጥ እና ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን፣
በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 55(1) መሠረት ይህ የውጭ ኦዲት ድግግሞሽን የሚያስቀር የነጠላ ኦዲት አዋጅ ታውጇል።