የብሮድካስቲንግ አገልግሎት ቴክኖሎጂ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገና እየተሻሻለ በመሆኑ፤ በዚህም ቴክኖሎጂ ተገቢውን ጥቅም ላይ በማዋል የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ያለውን የብሮድካስት አገልግሎት ድርጅታዊ መዋቅርና ሥርዓት ማሻሻል አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል፤
የብሮድካስት አገልግሎት ሚና የሀገሪቱን ዘላቂነት ያለው ልማት፣ ሰላምና ዲሞክራሲ እንዲሁም በእኩልነትና በነፃ ውህደት ላይ የተመሰረተ የህብረተሰብ ዲሞክራሲያዊ አንድነትን የበለጠ ለማጠናከርና ለማረጋገጥ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን በመገንዘብ፤
የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ከመንግስትና ከህዝብ ጋር የሚያገናኝ ድልድይ በመሆን፣ የዜጎች ተሳትፎና የህብረተሰቡን የጋራ ጥቅም በማረጋገጥ፣ በህገ-መንግስቱ ድንጋጌዎች መሰረት በህብረተሰቡ መካከል የሃሳብና የአመለካከት ነፃ አገላለፅን እንዲያበረታታ የሚጠበቅበትን ሚና እንዲወጣ የራሱ የሆነ ተቋማዊና የአሰራር ነፃነት እንዲሁም የተሻለ የህግ ጥበቃ ሊኖረው ይገባል ተብሎ በመታመኑ፤
በመሆኑም የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽንን ማቋቋምና ይበልጥ ውጤታማ፣ ጥራት ያለውና ብቃት ባለው መንገድ አገልግሎቱን እንዲሰጥ ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፤
በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ- መንግሥት አንቀጽ 55(1) መሠረት የሚከተለው ታውጇል፡፡
•
•