የተሟላ የእንስሳት ጤና አገልግሎት ለመስጠት እንዲቻል ፈዋሽነታቸው፣ ደህንነታቸውና ጥራታቸው የተረጋገጠ መድኃኒቶች በማያቋርጥ ሁኔታ መገኘትና በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል ወሳኝነት አለው፡፡ መንግሥት በሽታን ለመመርመር፣ ለመከላከልና ለማከም የሚያስፈልጉ መድኃኒቶች በአግባቡ እንዲቀርቡ ሁኔታዎችን የማመቻቸትና የመቆጣጠር ግዴታ አለበት።
እንደሚታወቀው ሁሉ የእንስሳት መድኃኒቶች ከእንስሳት ጤንነትና ምርታማነት ጋር በቀጥታ የተሳሰሩ፣ በተፈጥሮአቸው የመርዛማነት ባሕርይ ያላቸውና ከጥሬ ዕቃዎች ዝግጅት ጀምሮ በምርት፣ በክምችት አያያዝ፣ በማከፋፈልና በችርቻሮ ሂደት አስፈላጊውን ጥንቃቄ ካልተደረገበት የጥራት ደረጃቸው፣ የፈዋሽነታቸውና ደህንነታቸው ባህርይን ሊያጡ ወይም ሊለወጡ ስለሚችሉ ከዘርፉ ሊገኝ የሚችለውን ጥቅም እስከ ማሳጣት ሊያደርሱ ይችላሉ፡፡
ስለሆነም የእንስሳት መድኃኒት ዕደላ መካሄድ ያለበት በሙያው ጠለቅ ያለ ዕውቀትና አግባብ ባለው ባለሙያ ነዉ፡፡ በተጨማሪም ጥራታቸው፣ ፈዋሽነታቸውና ደህንነታቸው የተጠበቁ የእንስሳት መድኃኒቶች ለተገልጋዩ ለማዳረስ ለክምችት፣ አያያዝና ዕደላ አመቺ የሆነና የተሟላ ተቋም መኖር አለበት።
በመሆኑም የእንስሳት መድኃኒትና መኖ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን በአዋጅ ቁጥር 728/2004 አንቀጽ 20 ንዑስ አንቀጽ 2 በተሰጠው ሥልጣንና ኃላፊነት መሠረት የእንስሳት መድኃኒቶች ዕደላ ተግባር መመዘኛዎችና የብቃት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት አሰጣጥ ሥርዓት በተገቢው መንገድ እንዲከናወን ይህን መመሪያ አውጥቷል።