በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙና ለምግብ እጥረት ተጋላጭ የሆኑ ፣ ከድህነት ወለል በታች የሚገኙ እና ለተለያዩ ማኅበራዊ ችግሮች ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን፣ እጅግ አነስተኛ ገቢ ያላቸው ቤተሰቦችን፣ የጎዳና ተዳዳሪዎችን፣ ሴተኛ አዳሪዎችን፣ መሥራት እየቻሉ ወደ ስራ ያልገቡ ስራ ፈላጊ ዜጎችን፣ አካል ጉዳተኞችን፣ ጧሪና ደጋፊ የሌላቸው አረጋውያን እና ህጻናትን ተጠቃሚ ማድረግ በማስፈለጉ፤
ተግባሩ በከፋ ድህነት ውስጥ ከሚገኙ በርካታ ነዋሪዎች ህይወት መለወጥ ጋር በእጅጉ የተቆራኘ እንደመሆኑ እና ከፍተኛ የሆነ ሀብት የሚንቀሳቀስበት በመሆኑ ግልጸኝነትና ተጠያቂነትን ባዘለ ሁኔታ ሊተገበር እንደሚገባው በመታመኑ፤
ተግባሩን ውጤታማ ለማድረግ ከተቀመጡ አቅጣጫዎች መካከል ተጠቃሚዎችን በቤተሰብ ደረጃ ፍትሃዊና አሳታፊ በሆነ መንገድ መለየት ተግባር ጋር በተያያዘም በተጠቃሚዎች ልየታ እና በአጠቃላይ የፕሮጀክቱ ትግበራ ሂደት ሊከሰቱ የሚችሉ ቅሬታዎችን በአግባቡ ተቀብሎ መፍታት በማስፈለጉ፤
ከተጠቃሚዎች ምልመላ ጀምሮ በየደረጃው በሚኖረው የትግበራ ሂደት ሊከሰት የሚችለውን ቅሬታ ለመፍታት የሚያስችል የቅሬታና አቤቱታ ማስተናገጃ የአሠራር ስርዓት መዘርጋት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፣
የስራ፣ ኢንተርፕራይዝ እና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርየአስፈጻሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር አዋጅ ቁጥር 74/2014 አንቀጽ 15 ንዑስ አንቀጽ (2) ፊደል ተራ (ሠ) በተሰጠዉ ሥልጣን መሠረት ይህን መመሪያ አውጥቷል፡፡