በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ትኩረት ከተሰጣቸው ጉዳዮች የጎልማሶች ትምህርት አንዱ ነው። ዕቅዱ በሀገራችን ያለውን ዕድገት ሁሉን አቀፍ ለማድረግ ተግባር ተኮር የጎልማሶች ትምህርትን ተደራሽ በማድረግ ዕድሜያቸው ከ15-60 ዓመት የሚገኙ ወጣቶችና ጎልማሶች ከዕለት ኑሮአቸው ጋር የተገናኘ የህይወት ክህሎት በማስጨበጥ ህይወታቸውን እንዲያሻሽሉ በማድረግ ለአገር ኢኮኖሚ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ማስቻል ነው።
በመሆኑም ይህንን ግብ ለማሳካት የተቀናጀ ተግባር ተኮር የጎልማሶች ትምህርት መርሐ ግብር ተነድፎ በመተግበር ላይ ይገኛል፡፡ ለዚህም ሀገር አቀፍ የጎልማሶች ትምህርት ስትራቴጂ በ2000 ዓ.ም ተቀርፆ የተቀናጀ ተግባር ተኮር የጎልማሶች ትምህርት ፕሮግራም በተጠናከረና በተቀናጀ መልኩ እንዲተገበር ላለፉት ዓመታት ትምህርት ሚኒስቴር ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ሲሰራ ቆይቷል፡፡ ከዚህም ባሻገር የጎልማሶች ትምህርት ስትራቴጂን በሥራ ለመተርጎም የሚያግዙ የተለያዩ የመነሻ ሰነዶች ተዘጋጅተዋል፡፡ ሰነዶቹ ጎልማሶች ዕውቀታቸውንና ክህሎታቸውን አዳብረው በሀገር ልማት በስፋት እንዲሳተፉ ለማስቻል ከክልል ትምህርት ቢሮዎች፣ ከትምህርት ባለሙያዎችና ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር ተዘጋጅተው በመተግበራቸው በተሳታፊ ጎልማሶች ህይወት ላይ ተጨባጭ ለውጦች እየተመዘገቡ ይገኛል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ የፕሮግራሙ ሁለት ዓመት ትግበራ መጠናቀቅን ተከትሎ ከፕሮግራሙ ተሳታፊ ጎልማሶች ፍላጎት በመነሳት፣ ፕሮግራሙን ከዕድሜ ልክ ትምህርት (lifelong learning) ጽንሰ ሀሳብ ጋር ለማስተሳሰር እንዲሁም የፕሮግራሙን ጥራትና ተገቢነት ለማስጠበቅ ከተቀናጀ ተግባር ተኮር የጎልማሶች ትምህርት ወደ ሌሎች የትምህርትና ሥልጠና ፕሮግራሞች የሚደረግ የተሳታፊ ጎልማሶች የሽግግር መመሪያ ማዘጋጀት አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበታል፡፡ በመሆኑም መመሪያውን ለማዘጋጀት ባለድርሻ አካላት ያሳተፈ ግብረ ኃይል ከትምህርት ሚኒስቴር ከጐልማሶችና መደበኛ ያልሆነ ትምህርት ማስተባበሪያ፣ ከሥርዓተ ትምህርት ዝግጅትና ትግበራ ዳይሬክቶሬት፣ ከቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ኤጀንሲና በኘሮግራሙ ዙሪያ በቅርበት ከሚሠሩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በተለይም ከጀርመን የጎልማሶች ትምህርት ማኅበር የምስራቅ አፍሪካ ሪጅናል ጽ/ቤት (D-international) የተውጣጡ ባለሙያዎች ተቋቁሞ ፕሮግራሙ ያለበትን ሁኔታና የተሳታፊ ጎልማሶችን ቀጣይ የትምህርት ፍላጎት አስመልክቶ የዳሰሳ ጥናት ተካሂዷል፡፡ በጥናቱ ግኝትና በተሰጡት የመፍትሔ ሀሳቦች መነሻነት ይህ መመሪያ ተዘጋጅቷል፡፡
በመሆኑም በዚህ ሰነድ ውስጥ የመመሪያው አስፈላጊነት፣ የመመሪያው ዓላማዎች፣ በመመሪያው ውስጥ የተካተቱ ቃላትና ሐረጋት ትርጓሜዎች፣ ምዘናና የምስክር ወረቀት፣ የሽግግር ሂደት እና የባለድርሻ አካላት ተግባርና ኃላፊነት እንዲሁም ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች የሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ተብራርተው ቀርበዋል፡፡