የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተለያየ የቤት ልማት ፕሮግራም የተገነቡ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን በተለያየ ጊዜ ለተጠቃሚዎች ሲያስተላልፍ መቆየቱ ይታወቃል፡፡
የቤት ልማት ፕሮግራሙን በተሻለ አሠራር ለማስቀጠል እንዲቻል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስፈጻሚ አካላትን እንደገና ለማደራጀት የወጣ አዋጅ ቁጥር 64/2011 ለቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ በተሰጠው ሥልጣንና ተግባር መሠረት የአዲስ አበባ ቁጠባ ቤቶች ልማት ኢንተርፕረይዝ እና የቤቶች ልማት ፕሮጀክት ጽ/ቤት እንዲዋሀዱ ተደርጎ የቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ሆነዉ በመቋቋሙ አዲስ የአሠራር መመሪያ ማዘጋጀት አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል፡፡
በዚህም መሠረት ቀደም ሲል በነባሩ ተቋማት የተገነቡና ወደፊት በኮርፖሬሽኑ ተገንብተው ለተጠቃሚዎች የሚተላለፉትን ቤቶች የማስተላለፍ ስርዓትንና የቤት እድለኞች በሚቀርቡበት ጊዜ ሊያሟሏቸው የሚገባቸው ቅድመ ሁኔታዎች አስቀድሞ ለማሳወቅና ከሕብረተሰቡ በቤት ማስተላለፍ ወቅት የሚነሱ ቅሬታዎችን በመፍታት ቤቶቹ የሚተላለፉበትን ስርዓት ግልጽ፣ ተአማኒነትና ተጠያቂነት እንዲኖረው ማድረግ አስፈልጓል፡፡
ከቤት ማስተላለፍ እስከ ቤት ርክክብና ብድር አመላለስ ድረስ ባለው ሂደት ባለድርሻ አካላትን የሚያሳትፍና ቅንጅታዊ አሠራር የሚጠይቅ በመሆኑ በዚህ ሂደት የሚሳተፉ አካላትን ተናበው እንዲሰሩና የተሻለ አሠራር በመፍጠር በቤት ማስተላለፍ ሂደት ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ አስፈፃሚና ፈፃሚ አካላትን ኃላፊነት እና ተጠያቂነትን የሚያሰፍን አሠራር እንዲኖር ለማስቻል በአዲስ አበባ ከተማ የቤቶች ልማት አስተዳደር ቢሮ በአዋጅ ቁጥር 64/2011 መሠረት ይህን መመሪያ አውጥቷል፡፡