በአገሪቱ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ልማት ላይ የሰው ኃይል ትልቁን ሚና የሚጫወት ሲሆን በህንፃ ግንባታ የጥራት ጉድለት ከሚያስከትሉ ምክንያቶች ውስጥ ዋነኛው ባለሙያዎች ኢንዱስትሪው በሚፈልገው የብቃት ደረጃ ላይ ያለመሆናቸው ነው፡፡ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው በፍጥነት እያደገ በመምጣቱ ዘርፉ ከዝቅተኛ እስከ ከፍተኛ ባለሙያዎች በቂ ዕውቀትና ክህሎት ያላቸውን በመፈለጉ ደረጃ ማውጣት የግድ በማለቱ፤ በዲዛይን፤ በግብዓት አጠቃቀምና በግንባታ ወቅት የሚከሰት የገንዘብና የጊዜ ብክነትን መቀነስ በማስፈለጉ እና የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆን በማድረግ ረገድ የመመሪያው መውጣት ለዘርፉ ዕድገት የላቀ ሚና የሚጫወተውን የሰው ኃይል ልማትን ለመምራት የሚኖረው አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደሚሆን በመታመኑ፤
የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር በሕንጻ አዋጅ ቁጥር 624/2001 አንቀጽ 26 እና ይህንን አዋጅ ለማስፈጸም በወጣው የሚኒስትሮች ምክር ቤት የሕንጻ ደንብ ቁጥር 243/2003 አንቀጽ 20 ላይ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ የተሰማራውን የሰው ኃይል ብቃት ከጊዜ ወደ ጊዜ በምዘና መረጋገጥ እንዳለበት ታሳቢ በማድረግ ይህንን መመሪያ አውጥቷል፡፡
በተጨማሪም መመሪያው በአገር አቀፍ ደረጃ በትምህርትና ሥልጠና ዘርፍ ወጥተው እየተሰራባቸው ከሚገኙ መመሪያዎች በተለይም ውጤት ተኮር የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ስርዓቱን ለመተግበር ከወጣው የሙያ ብቃት ምዘና መመሪያ ጋር የተጣጣመ መሆኑ ተረጋግጧጣል፡፡: