በከተማችን አዲስ አበባ ከሚመነጨውን ደረቅ ቆሻሻ ውስጥ 75 ፐርሰንት የሚሆነው ከመኖሪያ ቤት ይመነጫል፡፡ ይህ ከመኖሪያ ቤት የሚመነጨውን ደረቅ ቆሻሻ በአካባቢና በህብረተሰቡ ጤና ላይ ጉዳት ሳያደርስ በአግባቡ ሰብስቦ ለማጓጓዝ የከተማው አስተዳደር ከ6,000 በላይ ዜጎችን በጥቃቅንና አነስተኛ የጽዳት ማህበራት በማደራጀት ከቤት ለቤት የደረቅ ቆሻሻ የማሰባሰብ ስርዓት ከ15 ዓመት በፊት ከተማው ዘርግቶ ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል፡፡
በተለይ በ2010 ዓ.ም የጥቃቅንና አነስተኛ የጽዳት ማህበራትን አቅም ለማሳደግና የደረቅ ቆሻሻ ከመኖሪያ ቤት አሰባሰብ ስርዓቱን በተሻለ ቴክኖልጂ በማገዝ የደረቅ ቆሻሻ አሰባሰብ ስርዓቱን ለማዘመን ሲባል በጥቃቅንና አነስተኛ የጽዳት ማህበራት የተደራጁትን ማህበራት በአቅራቢያቸው በሚመች ሁኔታ በማዋሃድ ወደ 74 የሽርክና ማህበራት እንዲያድጉ በማድረግ የተሻለ አሠራር እንዲፈጠር ተድርጓል፡፡
እነዚህን የህብረት ሽርክና የጽዳት ማህበራት ለማስተዳደር የሚያስችልና ከተማዋ አሁን ካሉት የእድገት ደረጃ ጋር ሊመጥን የሚችል የተቀናጀ የደረቅ ቆሻሻ አስተዳደር ስርዓት ለመዘርጋት የሚያስችል የህብረት ሽርክና የጽዳት ማህበራት የአሠራር መመሪያ የነበረ ሲሆን ካለው ሁኔታ በማቃኘት አሻሽሎ ማዘጋጀት አስፈላጊ ሆኗል፡፡ በመሆኑም አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተሻሻለ የተቀናጀ የደረቅ ቆሻሻ አስተዳደር ደንብ ቁጥር ፻/፪ሺ፲ አንቀጽ ፴፫ መመሪያ የማውጣት ሥልጣን በተመለከተ ለኤጀንሲው በከተማው ካቢኔ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት በማድረግ ይህንን የህብረት ሽርክና የጽዳት ማህበራት የደረቅ ቆሻሻ አሰባሰብ፤ የዞን ጽዳት አጠባበቅና የስታንዳርድ አፈጻጸም የአሠራር መመሪያ አውጥቷሌ፡፡