የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የተጣለበትን ዘርፉን የመምራትና የማስተባበር ድርሻውን በመወጣት ልማትን ለማፋጠን፣ መልካም አስተዳደርን ለማስፈንና ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት የሚያስችሉ የተለያዩ ስትራቴጂያዊ ጉዳዮችን በመለየት ፖሊሲዎችን፣ ፕሮግራሞችን እና ፕሮጀክቶችን በመቅረጽ በመተግበር ላይ ይገኛል፡፡ የስትራቴጂያዊ ጉዳዮችን አፈጻጸም ውጤታማነት እና ቀጣይነት ለማረጋገጥ በሁሉም ደረጃ የሚገኙ የሴክተር ተቋማትን አፈጻጸም ደረጃ በመለየት እውቅና መስጠት ያስፈልጋል፡፡
በመሆኑም በፌደራል፣ በክልሎች እና በአዲስ አበባና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች በሚገኙ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ዘርፍ ተቋማት የእቅድ አፈጻጸም በየወቅቱ መመዘን ተገቢ ነው፡፡ በመሆኑም የሴክተር ተቋማት ለዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ትግበራ መሳካት የበኩላቸውን ሚና መወጣት እንዲችሉ የዕቅድ አፈጻጸማቸውን በመመዘንና ብቃታቸውን በመለየት እውቅና ለመስጠት የሚያስችል ወጥነት ያለው መመዘኛ መመሪያ ማውጣት አስፈልጓል።
ከዚህ አኳያ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ አስፈጻሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን በወጣ አዋጅ ቁጥር 691/2003 አንቀጽ 10 (1) (ሠ) አንቀጽ 25 እና ንዑስ አንቀጽ (1) በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ይህን መመሪያ አውጥቷል።