የከተማ ልማት፣ ቤቶችና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የተጣለበትን ዘርፉን የመምራትና የማስተባበር ድርሻውን በመወጣት ልማትን ለማፋጠን፣ መልካም አስተዳደርን ለማስፈንና ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት የሚያስችሉ የተለያዩ ስትራቴጂያዊ ጉዳዮችን በመለየት ፖሊሲዎችን፣ ፕሮግራሞችን እና ፕሮጀክቶችን በመቅረጽ በመተግበር ላይ ይገኛል፡፡ የስትራቴጂያዊ ጉዳዮችን አፈጻጸም ውጤታማነት እና ቀጣይነት ለማረጋገጥ በሁሉም ደረጃ የሚገኙ የሴክተር ተቋማትን አፈጻጸም ደረጃ በመለየት እውቅና መስጠት ያስፈልጋል፡፡ በመሆኑም በፌዴራል፣ በክልሎች እና በአዲስ አበባና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች በሚገኙ የከተማ ልማት፣ ቤቶችና ኮንስትራክሽን ዘርፍ ተቋማት የእቅድ አፈጻጸም በየወቅቱ መመዘን ተገቢ ሆኖ በመገኘቱ ወጥነት ያለው መመዘኛ መመሪያ ተዘጋጅቶ ከ2003 በጀት ዓመት ጀምሮ ምዘና ሲካሄድ መቆየቱ ይታወቃል፡፡
◆ የሴክተር ተቋማት የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አፈጻጸም ምዘና ግብረ-መልስ ማካሄድ ያስፈለገው፡-
1) በፌዴራል፣ በክልሎች፣ በአዲስ አበባና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች የሚገኙ የከተማ ልማት፣ ቤቶችና ኮንስትራክሽን ዘርፍ ተቋማት የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ከማሳካት አኳያ የአፈጻጸም ደረጃውን ለመረዳት የሚያስችል በመሆኑ፣
2) በሴክተር ተቋማቱ መካከል ጤናማ የውድድር ስሜት በመፍጠር ለተሻለ አፈጻጻም የሚያነሳሳ በመሆኑ፣ እና
3) በሴክተር ተቋማቱ የተሻሉ መልካም ተሞክሮዎችን በመለየት ወደ ሌሎች ተቋማት ለማስፋትና ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ድጋፍ ለመስጠት የሚያስችል በመሆኑ ነው፡፡
ምዘናው ለማካሄድ የተዘጋጀው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አፈጻጸም የምዘናና ግብረ-መልስ መመሪያ በየወቅቱ በምናካሂደው የሴክተር ጉባኤ ላይ በሚሰጡ አስተያየቶች መሠረት እየዳበረ የመጣ ሲሆን የምዘና ሂደቱንም ይበልጥ የተሳለጠ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ለዚህ የዘጠነኛ ዙር ምዘና ሂደትም መመሪያው ከወቅቱ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር በተገናዘበ መልኩ አነስተኛ ማሻሻያ በማድረግ ተዘጋጅቷል፡፡ በዚሁ መሠረት በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያው ዙር የዝግጅት ምዕራፍ እና ጎን ለጎን የተሰሩ የተግባር ምዕራፍ ስራዎችን እንዲሁም በሁለተኛው ዙር የተግባር ምዕራፍ እና የማጠቃለያ ምዕራፍ ስራዎችን የሚመዝን ሆኖ ተዘጋጅቷል፡፡ መመሪያው የፌዴራል ሚኒስቴር መ/ቤቱ ከክልል እና ከተማ አስተዳደር አቻ ቢሮዎች ጋር ስምምነት የደረሰባቸውንና የተፈራረመባቸውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዶች እና የሲቪል ሰርቪስና የሪፎርም ስራዎችን አፈጻጸም ለመመዘን የሚያገለግል ይሆናል::
በዚሁ መነሻነት የከተማ ልማት፣ ቤቶችና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ አስፈጻሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 691/2003 አንቀጽ 10 (1) (ሠ) አንቀጽ 25 እና ንዑስ አንቀጽ (1) በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ይህን መመሪያ አውጥቷል፡፡