በፌደራል መንግሥት ሰራተኞች አዋጅ ቁጥር 1064/2010 አንቀጽ 54 ንዑስ አንቀጽ 1/ለ ድንጋጌ መሠረት ማንኛውም የመንግሥት መ/ቤት የአደጋ መከላከያ መሳሪያዎችና የስራ ቁሳቁሶችን ለሰራተኞች ማቅረብና ስለአጠቃቅማቸውም መመሪያ የመስጠት ኃላፊነት አለበት፡፡ ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ ነሐሴ 14 ቀን 2000 ዓ.ም በቁጥር መ30/ጠ57/20/334 ከፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ሚኒስቴር ለተቋማት በተላለፈ ሰርኩላር የመንግሥት መ/ቤቶች ተቋማት የራሳቸውን የአደጋ መከላከያ መሳሪያዎችንና ቁሳቁሶች በሙያ ደኅንነትና ጤንነት ባለሙያ በማስጠናት ተግባራዊ ማድረግ እንዳለባቸው ተገልጿል፡፡
ከፀሐይ፤ ከዝናብ፤ ከአቧራ እና ከሌሎች ለጉዳት ከሚያጋልጡ ነገሮች ጋር የሥራ ባሕሪያቸው የሚገናኝ ሠራተኞች ስራቸውን በሚያከናውኑበት ጊዜ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ለአጭር ወይም ለረጅም ጊዜ ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል በጤንነታቸዉና በደህንነታቸው ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት ለመከላከል የሚረዱ የስራ ልብሶችን የአደጋ መከላከያ መሣሪያዎችን እና የስራ ቁሳቁሶችን እንዲጠቀሙ ማድረግ የሠራተኞችን ደኅንነትና ጤንነት በመጠበቅ፤ የሥራ ተነሳሽነትን በማሳደግ ሠራተኞች ባሉበት መ/ቤት ተረጋግተው እንዲሰሩ ከማስቻሉም በላይ በየሥራ ገበታቸውም ውጤታማ ሥራ ሊያስመዘግቡ እንደሚችሉ ግልጽ ነው፡፡
ኤጀንሲው የሰራተኞችን ደኅንነትና ጤንነት በመጠበቅ ሊደርሱ ከሚችሉ አደጋዎችና በሽታዎች አስቀድሞ በመከላከል ሰራተኞች የተሰማሩበትን የሥራ መስክ በአግባቡ መወጣት እንዲችሉና አመርቂ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ለማድረግ ይህ በስራ ላይ ለሚደርሱ መሳሪያዎች፣ የስራ ቁሳቁሶችና የደንብ ልብስ መመሪያ ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡