በአዲስ አበባ ከተማ ያለውን የመሬት ይዞታ አስተዳደር በተሻለና ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲሁም ውስን የሆነውን የመሬት ሀብት አጠቃቀም በተገቢው ሁኔታ ለማስተዳደርና ህገወጥነትና ለመከላከል እንዲያስችል የከተማው አስተዳደር ልዩ ትኩረት ሰጥቶት በ2002 ዓ.ም መመሪያ ቁጥር 2/2002 ማውጣቱ ይታወሳል። በዚህም መሠረት መመሪያው ከወጣበት ቀን ጀምሮ ወደ ሙሉ ትግበራ በመግባት ከግንቦት 1988 ዓ.ም በፊት በተለያየ መንገድ የተያዙና ህጋዊ የይዞታ ባለመብትነት ማረጋገጫ ሰነድ ላልነበራቸው የመሬት ይዞታዎችና ቤቶች የባለይዞታነትና የቤት ባለቤትነት ማረጋገጫ ሰነድ መስተንግዶ ሲሰጥ ቆይቷል። በዚህ ሂደት በመመሪያው በራሱ ታይተው በነበሩት አንዳንድ ክፍተቶች መመሪያውን ለማስፈፀም እንቅፋት ወይም ማነቆ የሆኑ እና በመመሪያው ያልተዳሰሱ ጉዳዮች በማጋጠማቸው የከተማው አስተዳደር በመመሪያው ላይ የተለያዩ ማሻሻያዎች በማድረግ የመስተንግዶ ስራውን ለማሳካት ርብርብ ሲደረግ ቆይቷል።
ሆኖም በነበረዉ መመሪያ ምላሽ ለመስጠት አስቸጋሪ የሆኑ የተሟላ የመሬት ይዞታ ሰነድ የሌላቸዉ ይዞታዎች በመኖራቸዉ፣ ቀደም ሲል የሕግ እዉቅና አግኝተዉ በቀድሞ መመሪያ ሲስተናገዱ የነበሩት ባልተሟላ ሰነድ የተያዙ ይዞታዎች መስተንግዶ በመመሪያ ቁጥር 2/2002 (እንደተሻሻለዉ) ከሌሎች የይዞታ መስተንግዶ ድንጋጌዎች ጋር በአንድ ላይ ጸድቆ ሲተገበር የነበረ ቢሆንም ሌሎች የይዞታ መስተንግዶ ጉዳዮች እራሱን ችሎ መመሪያ ቁጥር 12/2004 ሆኖ ለብቻዉ ተዘጋጅቶ የጸደቀ ስለሆነ እና ለአጠቃቀም አመቺ እንዲሆን በአዲስ መልክ እራሱን ችሎ መዘጋጀቱ ተገቢ በመሆኑ፣
በዚህም መሠረት በመመሪያ ቁጥር 2/2002 (እንደተሻሻለዉ) መሠረት ያለበቂ ሰነድ ከግንቦት 1988 ዓ.ም በፊት ለተያዙና የይዞታ ማረጋገጫ ሰነድ ጥያቄ መስተንግዶን በሚመለከት በቀድሞ መመሪያ ያልተካተቱት፣ ክፍተት የነበረባቸውንና ከሌሎች ህጎች ጋር ተቃርኖ ያለባቸዉን አንቀጾች በማሻሻልና ሌሎች አንቀጾችን እንዳሉ በማካተት፣ ቀደም ሲል የተጀመረውን የሰነድ አልባ ይዞታዎችን የይዞታ ማረጋገጫ ሰነድ ጥያቄ ምላሽ ሰጥቶ ለማጠናቀቅ እንዲቻል የቀድሞውን መመሪያ በማሻሻል እና እራሱን አስችሎ መመሪያዉን ማውጣት በማስፈለጉ የከተማዉ አስተዳደር ካቢኔ ይህንን መመሪያ እዉጥቷል፡፡