የፌደራል መንግሥት አስፈፃሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባርን ለመወሰን በወጣ አዋጅ ቁጥር 1097/2011 አንቀጽ 26 ለሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚንስቴሩ በተሰጠው ሥልጣንና ተግባር መሠረት የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና አዋጅ ቁጥር 954/2008 አንቀጽ 10(3) እንዲሁም አንቀጽ 14(1) እና (2) ለማስፈጸም ሀገር አቀፍ ሙያ ብቃት ምዘና፣ እውቅናና የምስክር ወረቀት አሰጣጥ ሀገር አቀፍ ሙያ ብቃት ምዘና፣ እውቅናና የምስክርወረቀት አሰጣጥ መመሪያ ቁጥር አጽድቆ አዋጁን ሲያስፈጽም ቆይቶአል፡፡ በተሸሻለው የፌደራል መንግሥት አስፈፃሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን በወጣው አዋጅ 1263/2014 መሠረት ከተቋቋሙት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች አንዱ የስራና ክህሎት ሚኒስቴር ሲሆን ለሚኒስቴሩ በተሰጠው ሥልጣንና ተግባር ማዕቀፍ ውስጥ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና አዋጅ ቁጥር 954/2008 እንደሚያስፈጽም በግልጽ ያመላክታል፡፡
በዚህ መሠረት የስራና ክህሎት ሚኒስቴር በሁሉም ደረጃ ተቀባይነት ያለው ውጤትን መሠረት ያደረገ የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና በመደበኛና መደበኛ ባልሆነ ፕሮግራም በጥራና በብዛት በማሰልጠን፤ እንዲሁም በልምድ በተገኘ ዕውቀት፣ ክህሎት እና አመለካከት እውቅና የሚሰጥ ሥርዓት በመዘርጋት፤ የሙያ ብቃትን በምዘና በማረጋገጥ ዕውቅና እና የብቃት ማረጋገጫ ሰርቲፊኬት መስጠት የሚያስችል አሠራር አጠናክሮ መቀጠል አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል፡፡
የምዘና ስርዓቱን አግባብነት፣ ጥራት፣ ተደራሽነትና ፍህታዊነት ለማረጋገጥ እንዲያስችል በሀገር አቀፍ ደረጃ በተጠናው የትምህርትና ሥልጠና ፍኖተ ካርታ በተመላከተው ምክረ ሀሳብ መሠረት ደረጃ በደረጃ ይሰጥ የነበረው ሀገር አቀፍ የሙያ ብቃት ምዘና አሰልችና ሀብት አባካኝ እንድሁም ኢንዱስትሪዎችም ሥልጠና አጠናቃቂዎችን በውጤታቸው አወዳድረው ለመቅጠር ያልተመቸና ውድድርን የሚያበረታታ ሆኖ ባለመገኘቱ የደረጃ ደረጃ ሽግግር በማሰልጠኛ ተቋም የውስጥ ምዘና ማስተግበሪያ መመሪያ ቁጥር 883/2014 እንድ ሸፈን በመደረጉ፤ ሰልጣኞች ወደ ስራ አለም (World of work) ለመሰማሪያ ሲዘጋጁ ብቻ ሀገር አቀፍ የብቃት ምዘና መሰጠቱ የሥልጠና ጥራትና አግባብነት ዙሪያ ከፍተኛ ለውጥ እንደሚያመጣ በተለያዩ ጥናቶችና የውይይት መድረኮች አረጋግጠዋል፡፡
በመሆኑም ሀገር አቀፍ ሙያ ብቃት ምዘና፣ እውቅናና የምስክር ወረቀት አሰጣጥ ሰልጣኞች በሚያጠናቅቁበት ደረጃ እንዲመዘኑ ማድረግ በነባሩ መመሪያ ያጋጥሙ የነበሩ ችግሮችን በመፍታት እና ከተቋም ውስጥ ምዘና ማስተግበሪያ መመሪያ ጋር ማጣጣም ወሳኝ በመሆኑ እንድሁም ከአሁን በፊት የነበረው ሀገር አቀፍ የሙያ ብቃት ምዘና፣ እውቅናና የምስክር ወረቀት አሰጣጥ መመሪያ የመዛኞችንና የሱፐርቫይዘሮችን ተጠያቂነት ያላካተተ በመሆኑ መመሪያውን ማሻሻል አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል፡፡