የመንገድ ትራንስፖርት ለአንድ ሀገር ሁለንተናዊ እድገት የማይተካ ሚና እንዳለው የሚካድ አይደለም፡፡ ሚናውንም ደህንነቱ የተጠበቀ ለማድረግ በቴክኖሎጂ የተደገፈና በሕግ ማዕቀፍ የሚመራ መሆን ይኖርበታል፡፡ ከነዚህም መንገዶች ውስጥ በማንኛውም እንቅስቃሴ የደኅንነት መጠበቂያ መሳሪያዎችን መጠቀም ወሳኝ ነው፡፡ የአለም የጤና ድርጅት እንዳወጣው መረጃ በሕዝብ ትራንስፖርት አማካኝነት የሚንቀሳቀሱ አካላት በጉዞ ወቅት የደኅንነት ቀበቶ በአግባቡ ቢጠቀሙ አደጋ በሚያጋጥማቸው ወቅት አሽከርካሪውንና ከፊት የሚቀመጡ አካላት ከ45% እስከ 50% ለሞት ተጋላጭነታቸውን እንደሚቀንስና ከኃላ የሚቀመጡ ተጓዦችን ደግሞ ከ25% እስከ 35% ከሞት ሊታደጋቸው እንደሚችል ያሳያል፡፡ በሃገራችንም በደኅንነት ቀበቶ አለመጠቀም ምክንያት የደረሱ አደጋዎች ጥናት ተደርጎባቸው የተቀመጡ ባይሆንም ለአደጋዎቹ አስከፊነት የደኅንነት ቀበቶን አለመጠቀም ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው የማይካድ ነው፡፡
በአጠቃላይ የደኅንነት ቀበቶ ማሰር አሽከርካሪው ወይም ተሳፋሪው አደጋዎች በሚከሰቱበት ወቅት በፊተኛው ወይም በጎን ባሉ የተሽከርካሪው መስታወቶች ተስፈንጥረው እንዳይወጡና በዚህ ምክንያት ይደርስ የነበረውን ከፍተኛ አደጋ ለመቀነስ ከማስቻሉም በላይ አሽከርካሪዎች በአደጋ ወቅት ተሽከርካሪውን ለመቆጣጠር እንዲችሉ ያግዛል በተጨማሪም አደጋ በሚከሰትበት ወቅት አሽከርካሪውና ተሳፋሪዎች ተሽከርካሪው ውስጥ ወይም ከተሸከርካሪው ውጪ ካሉ ግዑዝ ነገሮች ጋር ከመጋጨት እንደሚታደግ ይታመናል፡፡
በመሆኑም በመንገድ ትራንስፖርት ትራፊክን ለመቆጣጠር የወጣ የሚኒስትሮችም/ቤት ደንብ ቁጥር 208/2003 አንቀጽ 5 ንዑስ አንቀጽ 3 ከ ሀ እስከ ሐ እንዳስቀመጠው ማንኛውም አሽከርካሪ በፊደል ተራ “ሀ” ከሞተር ብስክሌት በቀር የደኅንነት ቀበቶ ሳያስር በመንገድ ላይ ማንኛውንም ተሽከርካሪ ማሽከርከር እንደሌለበት፤ በፊደል ተራ “ለ” ማንኛውም አሽከርካሪ በሚያሽከረክርበት ወቅት በተሽከርካሪው ውስጥ የተሳፈረው ሰው የደኅንነት ቀበቶ ማሰሩን ማረጋገጥ እንዳለበ እና በፊደል ተራ “ሐ” ድንጋጌው ተፈፃሚ የማይሆንባቸው ተሽከርካሪዎችን በሚመለከት ባለስልጣኑ ይሆናል ይላል፡፡ በደንብ ቁጥር 208/2003 አንቀጽ 5 ንዑስ አንቀጽ 3 ከፊደል ተራ “ሀ – ለ” የተደነገጉትን ሳይተገብር ተሸከርካሪን ያሽከረከረ በመንገድ ትራንስፖርት ትራፊክ መቆጣጠሪያ ደንብን ለማሻሻል በወጣው የሚኒስትሮች ም/ቤት ደንብ ቁጥር 395/2009 ሠንጠረዥ “ለ” 4ኛ እርከን ሰንጠረዥ “ሀ” መሠረት ለጥፋቱ የሚመዘገብ ነጥብ 3 ሆኖ 250 ብር እንደሚቀጣ ተደንግጓል፡፡ ስለሆነም ከላይ የተጠቀሱትን ድንጋጌዎች ተግባሪያዊ ለማድረግና የደኅንነት ቀበቶ ባለማሰር ምክንያት የሚደርሰውን አደጋ ለመከላከልና ለመቀነስ ባለሥልጣን መስሪያቤቱ ይህንን መመሪያ አውጥቷል፡፡